>
5:16 pm - Thursday May 24, 0457

የኦሕዴድና የብአዴን ልዩነት  (አቻምየለህ ታምሩ)

1. ኦሕዴድ ለተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች  ጊዜያዊ መጠለያ ከመስራት  ጀምሮ የተፈናቃዮችን ደህንነት በተቻለ መጠን ለመጠበቅ ሲሞክር፤ ነውረኛው ብአዴን ግን ለተፈናቃይ አማሮች ጊዜያዊ መጠለያ መስራት ይቅርና ያስጠለላቸው ቤተ ክርስቲያን እንኳን ማረፊያ እንዲነሳቸውና  ከግቢው እንዲያስወጣቸው ትዕዛዝ በማስተላለፍ  ሕጻናት፣ሴቶችና አረጋውያን  ሜዳ ላይ እንዲወድቁ ያደርጋል።
2. ኦሕዴድ ለተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች  የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ  አትሌቶች፣ ድምጻውያንና ባለሐብቶት የተካተቱበት የእርዳታ ማሰባሰቢያ ዝግጅት ሲያደርግ፤  ነውረኛው ብአዴን ግን በደብረ ብርሃን ከተማ ተቆርቋሪ የአማራ ልጆች የጀመሩትን የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅት እንዳይካሄድ ያግዳል።
3. ኦሕዴድ በጅግጅጋ የሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች እያለ ሲዘግብ ነውረኛው ብአዴን ግን ከጎጃም መተከል የተፈናቀሉ፤ እዚያው ተወልደው የኖሩ አማሮችን «በቤንሻንጉል ጉሙዝ የሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች» እያለ ይጠራቸዋል።
4. ኦሕዴድ የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን  ለማነጋገርና ተስፋ ለመስጠት «የክልሉ አስተዳደር» መደበኛ ስራ አቁሞ ከለማ መገርሳ እስከ ታች  ድረስ ያሉ  ሹመኞች፤ ከአባ ገዳዎች እስከ ተቃዋሚ የፖለቲካ መሪዎች ድረስ  ተንቀሳቅሰው   መቶ ኪሎሜትሮችን  እየተጓዙ ተፈናቃዮች የሚገኙነትን ሁኔታ  በተዘጋጀላቸው ጊዜያዊ መጠለያ ውስጥ ኑሯቸው እንዴት እንደሚመስል እንዲያዩ  ሲያደርግ፤ ነውረኛው ብአዴን ግን  ከጽሕፈት ቤቱ   500 ሜትር፣ እንደራሴ ከሚገኝበት  ቢሮ  ደግሞ 1 ኪ.ሜ ርቀር ላይ  ብርድና ፀሐይ፣ ዝናብና  አቧራ  እየተፈራረቀባቸው  ሜዳ ላይ ተጥለው የሚገኙ  የአማራ እናቶችን፣ ሕጻናትንና አዛውንቶችን   ለመጎብኘት  አይደለም  ሌላ ሰው እንኳን እንዳይጠይቃቸው  በማገድ  ቀድመው ባህር ዳር የደረሱ ተፈናቃዮችን  በእቃ ማጓጓዣ ጭነው  የት እንዳደረሷቸው እስካሁን አይታወቅም፤  ያልተረጋገጡ መረጃዎች እስር ቤት እንዳጋዟቸው ያሳያሉ።
5.  ኦሕዴድን የኦሮሞ ተወላጆችን  መፈናቀል ከተፈናቃዮች በስልክ እንደደረሰው በብርሃን ፍጥነት ሙሉ ኃይሉን አንቀሳቅሶ ለተፈናቃዮች ሲደርስና ተስፋ ሲሆን፤ ነውረኛው ብአዴን ግን  ከመተከል ጀምሮ በየመንገዱ መከራን እየተቀበሉ ባሕር ዳር  ድረስ ተጉዘው   ችግራቸውን  ለማስረዳት ብአዴን ጽሕፈት ቤት የተገኙ  የተፈናቃይ ወኪሎች  የሆኑ አራት ግለሰቦችን «ለምን ለአቤቱታ መጣችሁ» በማለት  ባህር ዳር በሚገኘው ሁለተኛ ፓሊስ ጣቢያ አስሮ አሳድሮ   ባህር ዳርን ለቀው እንዲወጡ በማዘዝ በጊዜ ገደብ ይለቃል።
6. ኦሕዴድ በወያኔ አገዛዝ የኦሮሞ ሕዝብ እንደተገፋና የበይ ተመልካች እንደሆነና ለወደፊቱ ለተሻለ ለውጥ እንደሚታገል  ተስፋ ሲሰጥ፤ ነውረኛው ብአዴን ግን  «በክልሉ»  83 % የአንደኛና 80% የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  በድንጋይ ላይ  ትምህርት የሚሰጥባቸው፣ የዛፍ ስር መማሪያ ክፍል የሆነባቸው፣ ለከብት ማጎሪያ በረት እንኳ የማይበቁ በረቶች የሆኑ፣ ጫካና ዳስ ትምህርት ቤት የሆነባቸው፣ የፈራረሱና የወላቀቁ ጭቃ ቤቶች መማሪያ ክፍሎች ያሉባቸው፣ ለመውደቅ ቀናት የቀራቸው ክፍሎችና  መሬት ላይ በባዶ ሜዳ ትምህርት እየተሰጠ የሚገኝበትን «ክልል» እየገዘገዘ  «የአማራ ክልል ትምህርት ቤቶች የመምህራንና ቁሳቁስ አቅርቦት ተሟልቶላቸዉ የመማር ማስተማር ተግባራቸውን በተሳካ ሁኔታ በማከናወን ላይ ይገኛሉ» በማለት የአማራን ልጆች የወደፊት  ተስፋ ያጨልማል።
7. ኦሕዴድ  የትግራይ ወታደሮችና ፖሊሶች በናዝሬትና ልዩ ልዩ ከተሞች አቅደውት የነበረውን ግድያና አፈና ሲያከሽፍ፤ ነውረኛው ብአዴን ግን  የትግራይ  ፖሊሶች የክልላቸውን  መታወቂያ  ይዘው  ተከዜን  በመሻገር  ጎንደር ከተማ  ውስጥ ሰላማዊ ዜጎችን  ሲያፍኑና ሲገድሉ ትንፋሽ  እንኳን ሳይወጣው  እንዴውም አበጃችሁ በማለት  የትግራይ ፖሊሶች የአማራ ልጆችን ያፈኑበትን  መኪና እስከ  አባይ ድረስ  አጅቦ  አማራ ወደሚኮላሽበት  ወደ ማዕከላዊ ይሸኛል።
8. ኦሕዴድ  በደህንነት ሰዎቹ የኦነግን አርማና መታወቂያ  የያዙ የወያኔ ሰላዮች  በሕዝብ መካከል ያካሂዱት የነበረውን የጥላቻ ዘመቻና ቅስቀሳ እጅ ከፈንጂ በመያዝ በሜዲያ  ጭምር ለሕዝብ ይፋ ሲያደርግ፤ ነውረኛው ብአዴን ግን  «አማራ ተወላጆች ለሆናችሁ በሙሉ እስከ መጋቢት 30/7/2010 ዓ.ም. ድረስ ወይም እስከ ሚያዝያ 10/8/2010 ዓ.ም. ሀብታችሁን ሆነ ንብረታችሁን ሽጣችሁ ሆነ አርዳችሁ የማትወጡ ከሆነ ግን በሕግ ተገዳችሁ እየታሰራችሁ ወዳችሁ ሳይሆን በግድ ተገዳችሁ በሕግ የምትወ ጡ መሆኑን እስከተሰጠው ጊዜ ገደብ ካልወጣችሁ በሚደርስባችሁ ችግር የቀበሌው መስተዳደር ተጠያቂ አለመሆኑን በዚህ ደብዳቤ መግለፃችን እናስታውቃለን።» የሚልና  የበሎ ዴዴሣ ቀበሌ መስተዳደር በማህተም ያሰራጨውን  ኦፊሻላዊ የአማራ ግድያ ማዘዣ  ደብዳቤ በቴሌቭዥኑ እንዳይተላለፍ ያግዳል።
 _______________________________
የሕወሓቱ ነውረኛ ድርጅት  ብአዴን፣ ኦሕዴድ «የኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል» ከተባለው አካባቢ  ለተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆች የሰጠውን አይነት ትኩረት ሲሰጥ ያየነው ሰሜን ወሎ ውስጥ የትግራይ ተወላጆች ተጠቁ የሚል የውሸት ወሬ በተሰራጨበት ወቅት ለትግራይ ተወላጆች ብቻ  ነው።  ባለፈው ጥር ወር   በወልድያና ቆቦ «የትግራይ ተወላጆች ተጎዱ» የሚል የሀሰት ወሬ በተሰራጨበት ወቅት   እንደራሴው ገዱ አንዳርጋቸው፣ ቃል አቀባዩ ንጉሡ ጥላሁን፣ የፖሊስ ኮሚሽነሩ ሰኢድ አሕመድ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት የሚባለው አካል፣ ወዘተ  ተጎዱ ስላሏቸው የትግራይ ተወላጆች መግለጫና ቃለ መጠይቅ ከመስጠት አልፈው አማራውን አውግዘው  ነበር።  ነውረኞቹ ብአዴኖች «የክልሉ አስተዳደር» መደበኛ ስራ አቁመው  ከገዱ አንዳርጋቸው  እስከ ምክር ቤት አባላት  ድረስ ጉባኤ የተቀመጡት  የትግራይ ተወላጆች ተጎዱብ ብለው ነበር። ሆኖም ግን  በቤተ ብአዴን ይህ ሁሉ  የትግራይ መቆርቆር ሲፈስ  አንዳች እንኳን ሰው አልሞተም፤ የአካልም ጉዳትም  አልደረሰበት።
በመተከል ዞን ግን በርካታ አማራ አሁንም ድረስ  በግፍ እየተገደለ፤ በሺዎች የሚቆጠር  እየተፈናቀለና  ሜዳ ላይ እየወደቀ ነው።  ለትግራይ ተወላጆች ያንን ያህል መቆርቆር ያሳዩት የአማራ ወኪሎች  ነን የሚሉን ብአዴኖች  ግን  አማራው በመተከል  በግፍ ሲገደል፣ ብልቱ ሲሰለብ፣ ሲፈናቀል፣ ሜዳ ላይ ሲወድቅና  አሞራ ሲበላው  ለይስሙላ እንኳ  ቅንጣት ታህል መቆርቆር አላሳዩትም። ለትግራይ ተወላጆች እንዳደረጉት  «የክልሉን አስተዳደር» መደበኛ ስራ አቁመው  ከእንደራሴው ገዱ አንዳርጋቸው እስከ  ቃል አቀባዩ ንጉሡ ጥላሁን፤ ከፖሊስ ኮሚሽነሩ ሰኢድ አሕመድ እስከ የአማራ ክልል ምክር ቤት  እስከሚባለው በድን አካል  ድረስ አማራ በመሆኑ ብቻ  የተሰለበ የ14 ዓመት ሕጻን  እያዩ እንኳን መግለጫና ቃለ መጠይቅ መስጠቱ፤ አልፎም ድርጊቱን  ማውገዙ ይቅርና ሰብአዊ ርሕራሔ እንኳ ማሳየት አልቻሉም። ለዚህ ነው ሁልጊዜ  ብአዴን የሕወሓት ነውረኛ ድርጅት እንጂ የአማራ ሕዝብ አካል አይደለም፤ ብአዴን በአማራ መካከል የሚገኝ የትግራይ እንደራሴ  እንጂ የአማራ ወኪል አይደለም የምንለው።  ለዚህም ነው  የጸረ ወያኔው ትግል ቀጣይ እድገት ብአዴን የሚባለውን ነውረኛ የሕወሓት ድርጅት በማስወገድ ፋሽስት ወያኔ በአማራ ላይ ምርኩዝ እንዳይኖረው ማድረግ  አለብን የምንለው።
Filed in: Amharic