>

ነፃነት ለአንዳርጋቸው! ነፃነት ለ ኢ/ር መስፍን! (ውብሸት ታዬ)

 ዛሬ በማሕበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ከሰማሁዋቸው አስደሳች ዜናዎች አንዱ የወንድሜ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ የፍች ዜና ነው። ከጥቂት ቀናት በፊት ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ፍችው ተምሳሌታዊ በመሆኑ ውጤታዊ ፋይዳውም የላቀ ነው። ድሉም ሁሉም ወገን የሚጋራው ነው።
   ይህን ካልኩ በሁዋላ ግን በመሰል ሁኔታ ላይ የተወሰነ ሃሳብ ማከል እፈልጋለሁ። በተመሳሳይ የክስ ባህሪ(የተከሳሾቹ መስመር ሊለያይ ቢችልም) በእስር ላይ ለረዥም ዓመታት የቆዩ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችንም የነፃነትን አየር እንዲተነፍሱ፣ ቤተሰቦቻቸው ከሃሳብ ሰቆቃ አረፍ እንዲሉና ቀጣይ አጀንዳዎቻችን ከዚህ አዙሪት ወጥተው በአገራችን ቀጣይ የልዕልና ጉዞ ላይ በጋራ እንዴት እናድርግ? ወደሚለው እንዲያተኩር ነው።
    በእስር ቆይታዬ የማስታውሰውን ያህል ከላይ በጠቀስነው የፖለቲካ ጦስ የገቡ አብዛኞቹ ዜጎች የአገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ በቅጡ የተረዱ፤ ብሩህ አዕምሮ የታደሉ፣ የራሳቸውን አቋም ጠብቀው የሌሎችን የሚያከብሩ በዚህም ምናገባኝ? ከማለት ይልቅ ትክክል ነው ብለው ባመኑበት ጎዳና የቻሉትን ያህል ገፍተው አሁን ያሉበት ድረስ የተጓዙ ናቸው።
    የዛሬውን ሃሳቤን ከመቋጨቴ በፊት ግን እንደ አቶ አንዳርጋቸው ሁሉ የትጥቅ ትግል የሚያራምድ ድርጅት አመራር ነው በሚል ከአገር ውጪ (ኬንያ)ተይዞ ከመጣ በሁዋላ ላለፉት 12 ዓመታት በእስር ላይ ስለሚገኘው ኢንጂነር መስፍን አበበ በጣም ጥቂት ልበል።
   ኢ/ር መስፍንን ያገኘሁት ቃሊቲ ልዩ ጥበቃ ዞን “ዋይታ” ተብሎ በሚታወቀው የጨለማ ቤት ገብቼ በነበረበት አጭር ጊዜ ነው። በወቅቱ ይህ ምስኪን እስረኛ ለሁለት ዓመት ከሶስት ወር ቤት ተዘግቶበት ፀጉርና ጥፍሩን ሳይቆረጥ እንዲሁም ከንፅህና መጠበቂያዎች ተቆራርጦ የከረመበት፤ ይህም አላንስ ብሎ በመንፈሰ ጠንካራነቱ የሚታወቀው የትግል አጋሩና አባሪው ኢንጂነር ተስፋሁን ጨመዳ “ራሱን ሰቅሎ ገደለ” የተባለበት ወቅት ስለነበር ጥልቅ ሐዘኑ እስካሁን አይረሳኝም።
የኢንጂነር መስፍን አበበ የፖለቲካ ሕይወት የሚጀምረው በአምስት ኪሎ ሲቪል ኢንጂነሪንግ ያጠና ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ ሲሆን በአቋሙ የተነሳ ከነጓደኞቹ ትምህርታቸውን እንዲያቋርጡ የተገደዱበት ሁኔታ ነበር፤ ጫናዎቹ ግን በመጨረሻ ዋንጫ ተሸልሞ ከመመረቅ አላገዱትም። በሥራው ዓለም የኦሮሚያ ገጠር መንገዶች ባላስልጣንን ጨምሮ ብዙ ቦታዎች ሰርቷል።
    “ኢንጅነር መስፍን አበበ የተመደበው ምስራቅ ወለጋ ስሬ-ኖኖ-አርጆ መንገድ ሥራ ፕሮጄክት ነው። የኮንስትራክሽኑ ኃላፊ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ነገር ነበር። ሹፌር ነው። የከባድ ማሽን ኦፕረተር ነው። ሰርቬየር ነው። ዶዘር አስነስተው ተራራን ይቆርጣል። ግረደር አስነስቶ የመንገድ ቅርጽ ያወጣል። ሎደር አስነስቶ ይጭናል። ሹፌር ከሌለ የተጫነውን ጠጠር ይሁን አፈር ወስዶ ይደፋል። ቢሮ ገብቶ ዲዛይን ይሠራል። እቅድ ያወጣል። አፈጻጸሙን ይቆጣጠራል። ከዚህ ሁሉ ሥራ ቦኃላ ሌሊቱን ደግሞ ያለ እንቅልፍ ያድራል። ወገኖቹ ላይ የሚደረገው ጭቆና እንቅልፍ አይሰጠውም።” እሱን በቅርብ ለሚያውቅ ሰው እነዚህ ቃላቶች እውነተኞች ናቸው። የራሴን ምልከታ ግን ልጨምር።
    ኢ/ር መስፍን በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በብስለትና በሆደሰፊነት መነጋገር የሚፈልግ፤ በተለያዩ ውይይቶቻችን እንዳስተዋልኩት የራሱን አቋም ገልፆ ለሌሎች አመለካከት ክብርና እውቅና የሚሰጥ የእናት ኢትዮጵያ ልጅ ነው። ለዚህም ነው ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ይፈቱ የሚለው ጉትጎታ የወቅቱ ክቡርና አንገብጋቢ አጀንዳ የሆነው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic