>

ጠ/ምኒስትሩ እናታቸው የተነበዩላቸውን መናገራቸው ክፋቱ ምኑ ላይ ይሆን?? (ግርማ ሰይፉ )

ጠቅላይ ሚኒትር አብይ አህመድ ለሹማምንቶች የሰጡት የአንድ ቀን ሥልጣና ወይም በቲዎሪ የተደገፈ የሥራ መመሪያ አንድ አንዶች አቃቂር እያወጡ ጉዳዩን ለማሳነስ የሚሄዱበት መሰመር አሰገራሚ ሆኖብኛል፡፡ ከእነዚህ ጉዳዮች አንዱ እናቴ ሰባተኛ ንጉሥ ትሆናለ አለችኝ፣ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስራዬ እና አንቅስቃሴዬ በዚያው መስመር ሆነ በሚል የገለፁትን ጉዳይ ለምን እንዳነሱት አቃቂረኞች የገባቸው አልመሰለኝም፡፡
  እኔ እንደገባኝ፤ ይህ ምሣሌ በተሰጠበት አውድ ተመችቶኛል፡፡ በእብዮታዊ ዴሞክራሲ ቅንብብ ውስጥ ያሉ ሹሞችን፣ ትልቅ ሃሣብ ሰንቁ፣ ራዕይ ይኑራቸሁ፣ በተመደባችሁበት ቦታ አሻራችሁን አኑሩ፣ ነፃነት ይሰማቸሁ መሆን የምትፈልጉትን ተናገሩ አትፍሩ፣ ወዘተ የሚል ነበር፡፡ የጠቅላይ ሚኒሰትሩ እናት ባለቸው የእውቀት ደረጃ ከሀይለስላሴ ጀምሮ ቆጠረው፣ ተፈሪ በንቲን ቢፈልጉ ነጋሶን፣ ግርማ ወልደጊዮርጊስን ጨምረው፣ በፈለጉት መንገድ ቆጥረው ልጃቸው ላይ ትልቅ የመሆን መንፈስ ዘሩባቸው፡፡ ይህ ልጅም ዘመኑ በሚፈቅድለት መስመር ትልቁን ቦታ ፈለገ እንደፈለገውም አገኘው፡፡
መፈለግ ብቻ አይደለም፤ የሕይወት ዋጋ ሊያስከፍል የሚችል ስጋቶችን ተጋፈጠ፤ ለዚህ የሚመጥን ዝግጅት አድርጎ አሁን የደረሰበትን ደረጃ አገኘ፡፡ ይህን የህይወት ልምድ ማካፈል ሰህተት ሆኖ በዚህ አቃቂር ሲወጣ ጉዳዩ አስገራሚ ነው፡፡ ወይም ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማለት የነበረባቸው፤ ንጉሦቹን በደንብ ቆጥሮ እናቱ ያላሉትን አሰረኛ አስራ አንደኛ ወዘተ ማለት ነበር፡፡ ሌላው ደግሞ በሰባት ዓመት እናቱ ንጉሥ ትሆናለህ ሲሉት ከማን ቀጥዬ? መቼ ? ብሎ አናቱን በጥያቄ ማፋጠጥ ነበረበት ማለት ከሆነ አልገባኝም፡፡ በእውነት አልገባኝም፡፡
ለማንኛውም ሚኒስትሮች እና ሌሎች ሹሞች ቀጣይ ጠቅላይ ሚኒሰትር ለመሆን መፈለግ አያስቀስፈም፤ በቅድሚያ በየመስሪያ ቤታችሁ ያለው በአግባቡ በመምራት ለውጥ ማምጣት ግዴታ ነው፡፡ በየመስሪያ ቤታችሁ አሻራችሁን አኑሮ፡፡ የመለስ ራዕይ ከሚባል አባዜ ተገላገሉ፡፡ የራሳችሁ ራዕይ ይኑራችሁ፡፡ በሥልጣናችሁ ወስኑ፡፡ በውሳኔ የሚመጣውን ተጠያቂነት ብቻ ሳይሆን ጥሩ ከሆነ ሽልማትና ሙገሳም አለ ተብሏል፡፡ እኔ የገባኝ ይህ ነው፡፡
Filed in: Amharic