>
5:18 pm - Monday June 14, 5277

ይድረስ ለ OMN እና ለ ESAT (አፈንዲ ሙተቂ)

ሀረርጌን ተራ በተራ እየቦጠቦጡ ስላሉት የቀንና የማታ ጅቦች አልሰማችሁም እንዴ? መረጃው አልደረሳችሁም እንበል? ወይንስ እናንተም እንደ ፋና እና ዋልታ ቲቪ የመንግስትን ነውር እየደበቃችሁለት ነው?
ሄ ማጅራት መቺ መንግስትናእንግዴ ልጆቹ ሀረርጌን በመሳሪያ ጦርነት ብቻ አይደለም እየገደሉ ያሉት። ከመሳሪያው ጦርነት ጎን ለጎን ከባድ የሆነ የኢኮኖሚ ጦርነት በህዝባችን ላይ ከፍተው እንዳናድግ ቀን ከሌሊት እየዘመቱብን ነው። በዚህ ሰዓት አብዲ ኢሌ የመሳሪያ ጦርነቱን በውክልና እያካሄደው ነው። የፌዴራል ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን እና የፌዴራል ፖሊስ የሚባሉት ተቋማት ደግሞ የኦኮኖሚ ጦርነቱን እያፋፋሙት ነው።
ለምሳሌ ኮንትሮባንድን ለመቆጣጠር በሚል በተተከሉት ኬላዎች አማካኝነት የሚካሄደውን ውንብድና ተመልከቱ። አዋሽ፣ አርበረከቴ፣ ቦምባስ እና ደንገጎ በሚባሉት ከተሞች የተተከሉት ኬላዎች የጉምሩክና የፖሊስ ጅቦች ኪስ ማደለቢያ እና የሀረርጌ ህዝብ እምባ ማፍሰሻ ከመሆን ውጪ የሚከላከሉት ኮንትሮባንድ የለም። ደግሞም ኬላዎቹ የተቋቋሙበት ሁኔታ ራሱ ህገ ወጥ ነው። ምክንያቱም ኮንትሮባንድን መከላከል አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የቁጥጥር ኬላ የሚቋቋመው በድንበር ላይ ነው እንጂ በሀገር ውስጥ አይደለምና። በጣም የሚገርመው ነገር በነዚህ ኬላዎች ላይ “ኮንትሮባንድ ነው” እየተባለ ከሚዘረፈው እቃ የሚበዛው እጅ ከሀረርና ከጅጅጋ ከተሞች በህጋዊ መንገድ ከሚነግዱ ሱቆች የሚገዛ መሆኑ ነው። እነዚህ እቃዎች ናቸው ኮንትሮባንድ እየተባሉ የሚዘረፉት።
በመሠረቱ ሀረርጌ ለጅቡቲና ለበርበራ ወደቦች የቀረበ በመሆኑ ከውጪ ሀገራት የሚገባ እቃ በዋጋው ቅናሽ እንዳለው የታወቀ ነው። በህጋዊ መንገድ የሚገቡ እቃዎች እንዳሉት ሁሉ በኮንትሮባንድ የሚገቡ እቃዎችም አሉ። እነርሱን በድንበር ላይ ማስቆም፣ አሊያም በግመል ተጭነው ወደ ሀገር ውስጥ በሚጓጓዙበት ወቅት መውረስ ተገቢ ነው። እንደዚሁም ደግሞ ህብረተሰቡን ከመጉዳት በስተቀር ለህዝቡ አንዳች ዓይነት ጥቅም የማይሰጡትን እንደ ሺሻ፣ ሲጋራ፣ ጥራታቸው ያልተረጋገጠ መድሃኒቶች ወዘተ መቆጣጠር አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ኬላዎችን አቋቁሞ መፈተሽ ተገቢ ነው። ከሱቅ የተገዛ ጨርቅና ቅባት በምን ስሌት ነው ኮንትሮባንድ ሆኖ የሚዘረፈው?
ከእቃዎቹ መዘረፍ በላይ የሚያንገበግበው ደግሞ ፖሊሶቹ በህዝብ ላይ የሚያደርሱት መከራ ነው። ለፍተሻ ስራ በሚል የተመደቡት የፌዴራል ፖሊሶች ኮንትሮባንድ ተገኝቶበታል በሚሉት ሰው ላይ የሚያሳርፉት ዱላ አይነገርም። አባቶች፣ እናቶች፣ ወጣቶች፣ ጎልማሶች ሁሉም ይቀጠቀጣሉ።
በሌላ በኩል ፖሊሶቹ በአዋሽ አርባ፣ በኤረር ጎታ እና በሌሎችም ከተሞች ህዝብን የሚያሰቃዩባቸው እስር ቤቶች አሏቸው። በነዚህ እስር ቤቶች የታሰረ ሰው ፍርድ ቤት ሳይቀርብ እስከ ሰባት አመት ድረስ ይበሰብሳል። ከዚያ ለመውጣት የሚፈልግ ሰው እስከ መቶ ሺህ ብር ጉቦ ይጠየቃል።
በሀረርጌ የጎምሩክ ሰራተኛ እና የፍተሻ ፖሊስ ሆኖ የተመደበ ሰው በአሜሪካው የማንሃታን ሰፈር ሱቅ እንደ ከፈተ ነጋዴ “እልል” ይባልለታል። እዚህ ሰርተው ህዝቡን እየገረፉና እየዘረፉ ሚሊዮነር ለመሆን አንድ ዓመት ብቻ ነው የሚያስፈልገው።
ታዲያ እነዚህ የጉምሩክ ሰራተኞችና ፖሊሶች ህዝቡን የሚዘርፉት ብቻቸውን አይደለም። ኬላው ካለበት ስፍራ እስከ ፌዴራሉ መንግስት ድረስ የተደራጀ ኔትወርክ አላቸው። በያንዳንዱ ኬላና ለፓትሮል በሚወጡት መኪናዎች የሚዘረፈው የህዝብ ገንዘብ በተዋረድ ላሉት ሁሉ እየተከፋፈለ እስከ ላይኛው ባለስልጣን ድረስ ይደርሳል።
—-
ኦህዴድ በዘንድሮው ዓመት “ጥልቅ ተሃድሶ” ምናምን ብሎ ሩጫውን ሲጀምር የስርዓታችን አደጋዎች ብሎ የፈረጃቸው ኮንትሮባንዲስት የሚባሉት ሃይሎች፣ ጄኔራሎች እና ቱባ ነጋዴዎች በዚህ ፍተጋ እና ግርፊያ ውስጥ የሉበትም። እነርሱ የሚነግዱት “የማይፈተሹ” ተብለው ዋስትና በተሰጣቸው መኪናዎች ነው። እቃው አይን ውስጥ የሚገባ ዓይነት ከሆነ ደግሞ ህጋዊ ሽፋን በተሰጣቸው ነጋዴዎች በኩል ያስገቡታል። ወይንም ደግሞ ከአንዱ የፌዴራል መስሪያ ቤት ደብዳቤ አስጽፈው የመንግስት እቃ ነው በሚል ያስገቡታል። እነርሱን ጫፋቸውን የሚነካቸው የለም። ነጠላ ጫማ፣ ጨሌ፣ ነድ፣ እጣን፣ ካናቴራ፣ ፎጣ ወዘተ ከሀረር ከተማ ነጋዴዎች በደርዘን ቆጥሮ እየገዛ ወደ መሰላ፣ መቻራ እና መተሃራ እየወሰደ በመሸጥ በሚያገኘው ትርፍ የልጆቹን ጉሮሮ ለመዝጋት የሚፍጨረጨር የሀረርጌ አባወራ (እመወራ) ግን ኮንትሮባንዲስት እየተባለ መከራውን ያያል።
—-
ስለዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ ጊዜ ጽፈናል። በአካልም ለመንግስታችን አሳውቀናል። ነገር ግን ምንም መፍትሔ አልተገኘለትም።
ስለዚህ እናንተ የ ESAT እና የ OMN ጋዜጠኞች ጩኸታችንን በዓለም ዙሪያ በማሰማት የህዝባችን አጋር እንድትሆኑ በትህትና እንለምናችኋለን።
አፈንዲ ሙተቂ
Filed in: Amharic