>

ጋሽ ታደሰ ኃይሌ- የአማራ ህዝብ ደግነት ምሳሌ  (አፈንዲ ሙተቂ) 

“ጂንኒ ጀቡቲ” የሚለውን አባባል ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማሁበትን ሁኔታና ጊዜ ከዚህ በፊት አውግቼአችሁ ነበር። እነሆ ዛሬም መድገሙ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የገለምሶ ከተማን የተቆጣጠረው ግንቦት 22/1983 ነበር። ኦነጎች ለሶስት ቀናት አካባቢውን ሲያረጋጉ ከቆዩ በኋላ እሁድ ግንቦት 25/1983 በፖለቲካ ፕሮግራማቸው እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመስጠት ህዝቡን በገለምሶ ስቴድየም ጠሩት። “ጎቶምሳ” የሚባለው የኦነግ የብርጌድ አዛዥ ለህዝቡ ሰፊ ማብራሪያ ከሰጠ በኋላም የሀገሩ ሽማግሌዎች አስተያየት መስጠት እንደሚችሉ ተናገረ። በቅድሚያ አቶ ተስፋዬ ገብረኪዳን የሚባለው የገለምሶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ምክትል ዳይሬክተር የጎቶምሳን ንግግር አጠር አድርጎ በአማርኛ አቀረበው። ከዚያም የገለምሶው ቶታል አቶ ታደሰ ሃይሌ የሚባሉት ታዋቂ የከተማችን ነጋዴ ሊናገሩ ወደ መድረኩ ወጡ። እናም እንዲህ አሉ።
“ጓድ ጎተምሳ የተናገሩት በእውነቱ ደስ የሚያሰኝ ነገር ነው፤ ደርግ “ሰርጎ ገብ፣ ወንበዴዎች፣ ዓላማ የሌላቸው” ይላችሁ ስለነበረ በእውነትም ተራ ሽፍታ ቡድን ትመስሉን ነበረ። ዛሬ ግን ዓላማቸውን እንዲህ ማብራራት የሚችሉ ሰዎች መሆናችሁን በማረጋገጣችን ተመስገን እንላለን። ትግላችሁ ለኦሮሞ ህዝብ መብት መከበር የሚደረግ ከሆነ ይህ የኛም ጉዳይ በመሆኑ ከልባችን እንደግፈዋለን”። አቶ ታደሰ ይህንን ካሉ በኋላ ንግግራቸውን እንዲህ ሲሉ ቀጠሉ።
“ከእንግዲህ አማራ ኦሮሞ ጂንኒ ጀቡቲ እያሉ ማምታታት የለም። እኛ አማራ ብንሆንና አማርኛ ብንናገርም ከኦሮሞ ጋር ስለኖርን ኦሮሞ ጭምር ነን፤ ሁላችንም አንድ ነን”
በስቴድየም የነበረው ህዝብ በአነጋገራቸው በሳቅ ፍርስ አለ። ጓድ “ጎቶምሳ” በወንበሩ ላይ መቀመጥ እስኪያቅተው ድረስ ነበር የሳቀው። ታዲያ የተሳቀው በአነጋገራቸው እንጂ በንግግሩ ይዘት አለመሆኑን ልብ በሉ። በተለይም “ጂንኒ ጀቡቲ” የሚለው አገላለጽ እርሳቸውን ከመሰሉ የሀገር ሽማግሌ አንደበት በመሰማቱ ነው ህዝቡ የሳቀው።
እንግዲህ እኛ አፈንዲ ሙተቂ ወልደ-ገለምሶ የምንባለው ጀማሪ ጸሐፊ “ጂንኒ ጀቡቲ”ን ለመጀመሪያ ጊዜ የሰማነው በዚያች እለት ነው። ስለዚህ የኛ ፈጠራ አድርጋችሁ አትመልከቱት።
—-
አንድ ዓመት አለፈ። ኦነግ ከተማውን ለኢህአዴግ አስረክቦ ወደ ሽምቅ ውጊያ ገባ። ኢህአዴጎችም ከተማውን በያዙ በአስራ አምስተኛ ቀናቸው ህዝቡን በገለምሶ ሁለገብ አዳራሽ ሰበሰቡትና ስለአዲሷ ኢትዮጵያ የወደፊት አቅጣጫ ማብራሪያ ሰጡ። ከዚያም መድረኩ ለህዝብ ውይይት ክፍት ሆነ። በዚህኛው ዙርም አቶ ታደሰ ሃይሌ ሊናገሩ ተነሱ። “ጥሩ ትምህርት ነው የሰጣችሁን፤ ከእንግዲህ አማራ ኦሮሞ ጂንኒ ጀቡቲ እያሉ ማወናበድ የለም፤ ሁላችንም የአንድ ሀገር ልጆች ነን፤ ድሮም ተዋድደን የኖርን ሰዎች ነበርን፤ አሁንም እንኖራለን” አሉ።
ታዲያ በዚህኛው ዙር ሳቅ ሳይሆን ሞቅ ያለ ጭበጨባ ነበር በአዳራሹ ያስተጋባው። በተለይ ከኦሮሞዎች መካከል ብዙዎቹ ቆመው ነበር ያጨበጨቡላቸው። ምክንያት አለው።
ኢህአዴግ ኦነግ የነበረባቸውን ስፍራዎች ሲቆጣጠር ድርጅቱን ከመንገድ የተቀላቀሉት አንዳንድ ካድሬዎችና በተለያዩ ምክንያቶች በኦነግ ላይ የግል ቂም የያዙ ሰዎች “ኦነግ አማራውን ጭፍጭፏል፤ አሁንም ሊጨፈጭፍ ተዘጋጅቷል፣ ነቅተህ ተደራጅ፤ ተነሳ” የሚል ዓይነት ቅስቀሳ ማካሄድ ጀምረው ነበር። እነዚያ ካድሬዎችና ቂመኛ ግለሰቦች የሀረርጌ አማራ በቅስቀሳቸው ተነሳስቶ በኦሮሞ ወገኑ ላይ የሚዘምት መስሎአቸው ኖሯል። ነገር ግን የሀረርጌው አማራ ለእንደዚያ ዓይነቱ ቅስቀሳ ምቹ አልነበረም። በፖለቲካ ወጀብ ተዘናግቶ ለኦሮሞ ህዝብ ያለውን አመለካከት አልቀየረም። እነ ጋሽ ታደሰን የመሰሉ አርቆ አሳቢዎች ፊት መሪ ሆነው በመቆም “እኛ አንድ ነን” በማለት ቅሰቀሳውን አፈረሱት (በነገራችን ላይ በዚያ መድረክ ላይ እነ መምሬ ሙላቱ እና እነ ሼኽ ሙክታርም ንግግር አድርገው ነበር)።
ይህንን ስል ግን ኢህአዴግ ውስጥ ጥሩ ሰዎች አልነበሩም ማለት እንዳልሆነ ልብ በሉ። በተለይ በጦር ሰራዊቱ ውስጥ የነበሩት ቀደምት የኢህአዴግ ታጋዮች በጣም ጥሩ ሰዎች ነበሩ። እነ ኮማንደር አርኣያ፣ እነ አታኽልቲ፣ እነ ካሳ ሸሪፎ፣ እነ ካሕሱ ሐለፎም፣ እነ ወዲ መቐለ፣ እነ ወዲ ቀሽ እና ሌሎችም በጥሩ ምግባራቸው እስከ አሁን ድረስ ይጠቀሳሉ። መጥፎዎቹ ካድሬዎቹና ደህንነቶቹ ናቸው። እነዚህ ግፈኞች በአብዛኛው ኢህአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ወደ ድርጅቱ የተቀላቀሉ የድል አጥቢያ አርበኞች ነበሩ።
—–
እንዲህ የአማራ ህዝብ!! በተለይም በሀረርጌ ምድር ሀገር ከኛ ጋር ሲኖር የነበረው አማራ እንዲህ ዓይነት በአርኣያነት የሚጠቀስ ታሪክ ያስመዘገበ ህዝብ ነው። በደስታና በሐዘንም ወቅት አብረን ነው የኖርነው።
በአማራው ላይ የሚደርስ ጥቃት የሁላችንም ጥቃት ነው። በሌሎች ብሄረሰቦቻችንና ህዝቦቻችንም ላይ ጥቃት ሲደርስ በጋራ እንቆማለን።
ፈጣሪ በካማሺ ዞን የተገደሉትን ንፁሃን ነፍስ ይማርልን። ለቤተሰቦቻቸውም ፅናቱን ይስጥልን። መንግስት ደግሞ ጥቃቱን የፈፀሙትን በአስቸኳይ ለፍርድ ያቅርባቸው።
Filed in: Amharic