በዚህ ዝግጅት ላይ ሁለት ግለሰቦችን በእጅጉ ታዝቤያለሁ፡፡ ዶ/ር ምሕረት ደበበንና ከያኔ ስለሽ ደምሴን፡፡ እነኝህ ግለሰቦች የተሻለ ማሰብ የሚችሉ ናቸው ብየ አስብ ስለነበረ የወያኔ መሣሪያ ወይም መጠቀሚያ ሆነው ሕዝብን በመደለል በማግባባት የወያኔ ምርኮ እንዲሆን ይሠራሉ ብየ አልጠብቅም ነበረ፡፡ ለካ እነሱ የተሻለ ማሰብ የማይችሉ ሰዎች ኖረው ዙሪያ ገባውን ቢቃኙ በቀላሉ ሊደርሱበት ይችሉ የነበረውን እየሆነ ያለውን የወያኔን ሐሰተኛ የለውጥ እንቅስቃሴ ሐሰተኛነት መለየት ስላልቻሉና እንደ “ተራው” ዜጋ ሁሉ በቀላሉ ስለተሸውዱ ወይም ስለተታለሉ በምታዩት ፍጥነት ከወያኔው ጭምብል ከሐሰተኛው የለውጥ አሥተዳደር ጋር ሊጣበቁ ችለዋል፡፡
ይሄንን የምለው ነገሩን በቀና እናስበው ካልን ነው፡፡ ካልሆነ ግን የሥነልቡና ሐኪሙና የልኅቀት ሰባኪው ዶ/ር (ሊ.ማ.) ምሕረት ደበበ ሐኪም ሳይሆን እሱ ራሱ መታከም ያለበት ሞያውን ከሕዝብና ከሀገር ጥቅም በተጻራሪ ለርካሽ ጥቅሙ መጠቀሚያ የሚያደርግ የቢዝነስ (የጥቅም) ሰው እንዲሁም የሐሳብ ልኅቀት ባለቤት ሳይሆን የሐሳብ ዝቅጠት ባለቤት መሆኑ እርግጥ ነው ማለት ነው፡፡
ሰውየው እንደሰማቹህት በተደጋጋሚ “በቡድን፣ በደቦ አታስቡ! በማንም አትነዱ…!” እያለ የሕዝቡን አንድነት ለማፈራረስና ሕዝባዊ ትግሉ በሚቀጥሉት ጊዜያት እንደቀደመው ጊዜ ሁሉ በሐሳብ አንድነትና በኅብረት እንዳይደረግ መለያየትን ለመፍጠር በማሴር በስብከቱ ጥረት ሲያደርግ ውሏል፡፡ አቶ ምሕረት የአንድ ሀገር ሕዝብ በአንድ ሐሳብ ተስማምቶ በወል በጋራ ማሰብ ሲችል ያለው ፋይዳ ጠፍቶት አይደለም በወል በጋራ ማሰብን እየነቀፈ እየተቸ እያብጠለጠለ ለማግባባት ጥረት ሲያደርግ የነበረው፡፡ እንዳልኩት ትግል ላይ ያለውን የሕዝባችንን አንድነት፣ ኅብረትና ስምምነት ለማፍረስ በማሰብ እንጅ፡፡ ይሄንን የአቶ ምሕረትን ሸፍጠኛ አድራጎቱን ስንመለከት ሰውየው ወያኔን የተቀላቀለው “ለውጥ መጥቷል!” ብሎ በማመኑ ሳይሆን በጥቅም ተገዝቶ እንደሆነ እንረዳለን፡፡ በመሆኑም ዶ/ር ምሕረት ቅጥረኛ እንጅ ባለሙያ አይደለም!
እንደምሳሌ ያህል ዶ/ር (ሊ.ማ.) ምሕረትን ካየን ይበቃናን፡፡ አቶ ስለሽንም ሆነ ሌሎች የዐቢይ አሥተዳደር አጋር ሆነው በቀጣይ የሚወጡ የማንጠብቃቸውን ግለሰቦች በዚሁ ዓይን ልታዩዋቸው ትችላላቹህ፡፡
በብዙኃን መገናኛዎች እየሰማቹህት እንዳላቹህት ሰሞኑን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የአገዛዙ የአሥተዳደር አካላት በቀጥታና በግልጽ የተሳተፉበት በአማራ ተወላጆች ላይ እንደአዲስ በተያዘው የጥቃት ዘመቻ ከመተከል እስከ ናዝሬት፣ ከጅማ እስከ ምዕራብ ሸዋ፣ ከበሎ ደዴሳ እስከ ደቡብ ድረስ አማራ
* እንደበግ እየታረደ፡፡
* ዕድሜ ዘመኑን የደከመበትን ቤት ንብረቱን ተነጥቆ ተዘርፎ ባዶ እጁን ተፈናቅሎ እየተባረረ፡፡
* ሕገመንግሥታቸው “ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በነጻ የመዘዋወር፣ ኑሮን የመመስረትና ንብረት የማፍራት ሙሉ መብት አለው!” የሚል ሆኖ እያለ እና ሕጋዊነቱን የሚያረጋግጥ ሰነድ በእጁ እያለ ለዘመናት ከኖረበት ቀየ “ሕገወጥ ነህ!” እየተባለ በዛሬ ዘመን ሰው ያለ ሀገሩ እንኳ በአውሮፓና አሜሪካ ተሰዶ ሰብአዊ መብቱ ተከብሮለት በነጻነት ሠርቶ ከዜጎቹ ጋር ዕኩል መኖር በሚችልበት በ21ኛው መቶ ክ/ዘ ስንትና ስንት መራራ መሥዋዕትነት ከፍሎ በነጻነት ባቆያት በገዛ ሀገሩ የመኖር መብት ተነፍጎት በአስቸኳይ ለቆ እንዲወጣ ከቀበሌ አሥተዳደሮች በባለማኅተም የማስጠንቀቂያ ወረቀቶች እንዲደርሰው እየተደረገ ይገኛል፡፡
እነኝህ አሁን ግልጽ የወጡት ግለሰቦችና ሌሎቹ ግልጽ ያልወጡት ከዚህ አገዛዝ ጋር የተሰለፉ ግለሰቦች ጥቅም በልጦባቸው ተለጠፉ እንጅ ይሄንን ዜና ሳይሰሙ ቀርተውና አገዛዙ ለውጥ ማድረጉን አምነው፣ የዚህ በአማራ ላይ እየተፈጸመ ያለው ዘግናኝ ጥቃት እንድምታም ጠፍቷቸው አይደለም፡፡ እነኝህ ግለሰቦች አንድ ፈጽሞ መርሳት የሌለባቸው ነገር ግን ይሄንን ጥቃት እየፈጸመ ካለው ከዚህ አረመኔ አገዛዝ ጋር ሲሠሩ በወንጀሉ ሁሉ እነሱም ተጠያቂዎች መሆናቸውንና የሚጠየቁበት ቀንም ሩቅ አለመሆኑን ነው፡፡
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!