>

ኢትዮጵያ በጅግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት ትንስኤዋን ታረጋግጣለች!!! [ከኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ መስራች ጉባኤ የተሰጠ መግለጫ]

(ከኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ ንቅናቄ መስራች ጉባኤ የተሰጠ መግለጫ)
ሕወሐት/ኢሕአዴግ ስልጣኑን ከተቆጣጠረ ጀምሮ የዘረጋው ኢትዮጵያን ከፋፍሎና አዳክሞ የመግዛት ፖሊሲ ምክንያት  የኢትዮጵያ ህዝብ በገዥዎቹ  ለጆሮም ሆነ ለአይን የሚከብድ ግፍና በደል እየተፈፀመበት ነው። ይህንን ግፍና በደል ለመቋቋም አንድነቱን ለመጠበቅና ህዝባዊ አስተዳደር ለመገንባት የኢትዮጵያ ህዝብ በተደራጀና ባልተደራጀ መንገድ እጅግ መራራ ትግል ሲያደርግ ቆይቷል።
በተለይ በአለፉት ሶስት አመታት አገዛዙ እያረጀና እየበሰበሰ በመምጣቱ የኢትዮጵያም ህዝብ የለውጥ ፍላጎትና የነፃነት ትግል ተጠናክሮ በመቀጠሉ አገዛዙ በወሰደው ተስፋ የመቁረጥ እርምጃ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ለሃገራቸው ነፃነትና እኩልነት ሲሉ እጅግ ውድ የሆነውን የህይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል። በዚህ በአራቱም አቅጣጫ የተቀጣጠለ የለውጥ ፍላጎት የተረበሸው አገዛዝ የህዝብን ቁጣ ለማብረድ በሁለት ዓመት ከግማሽ ጊዜ ውስጥ ሶስት ካቢኔ ፈርሶ ተሰርቷል፤ሁለት ጠቅላይ ሚንስቴር ተለውጧል ፤ ሁለት ጊዜ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ በለየለት ወታደራዊ አገዛዝ ስር ወድቀናል።
በዚህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በጠቅላይ ሚንስትሮች መለዋወጥ ውስጥ አገዛዙን ወጥሮት የነበረው የህዝብ ተቃውሞ ለጊዜው ጋብ ያለ ቢመስልም አገዛዙ በሚከተለው ኢትዮጵያን ዘልዝሎና አዳክሞ የመግዛት ፖሊሲ ዜጎችን በጠላትነት እንዲተያዩ አድርጎ የዜጎች መፈናቀልና የእርስ በእርስ ጥላቻ ኢትዮጵያን ወደ መፍረስ ጫፍ አድርሷታል።
 ይህ ጥላቻና የዘር መድሎ በ27 ዓመታት በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች ብዙ የኢትዮጵያ ልጆችን ህይወት በልቷል፣ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል። ለአብነት ያህል ብንጠቅስ ከኦሮሚያና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ በተፈጠረው ግጭት ብዙ ህይወት ጠፍቷል፤ንብረት ወድሟል ፣በጌዲዮና በጉጅ መካከል በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ብዙ ንብረት ወድሟል፣ በጋምቤላ በአኝዋክና ኑዌር መካከል በተለያዩ ጊዚያት በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ከፍተኛ የንብረት ውድመት ደርሷል፣ ሕወሐት በትግራይ ህዝብ ላይ በሰራው ተከታታይ ፕሮፓጋንዳ በተፈጠረው የመነጠል ስሜት ሕወሐት እራሱን ከትግራይ ህዝብ ጋር የማይለያዩ የአንድ ሳንቲም ገፅታዎች አድርጎ በመሳሉ የኢትዮጵያ ህዝብም የትግራይ ተወላጆችን በስጋትና በጥርጣሬ ማየት በመጀመሩ ከተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ተፈናቅለዋል ንብረታቸው ወድሟል።  ከዚህም በተጨማሪ ሕወሐት/ኢሕአዴግ ኢትዮጵያዊ ነኝ የሚለውንና በተለይ አማራውን ጨቋኝ አድርጎ በመሳልና ይህንንም አመለካከት ህገ መንግስታዊ ቅርፅ በመስጠት የአማራን ህዝብ ላይ መጨረሻው የማይታወቅ ግድያ ማፈናቀል እና ስደት ዳርጎታል። ከማፈናቀሉ በተጨማሪ አማራን በስነ ልቦና ባይታዋርና ሀገር አልባ አድርጎታል።
እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው ውስብስብ የግጭት አውዶች ሃገራችንን እና ህዝቧን ከባድ አጣብቂኝ ውስጥ ጥሎታል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ህዝብ በአሁኑ ሰዓት ሁለት ከፍተኛ ተደራራቢ ሃላፊነቶች ተደቅነውበታል። አንደኛ ከአንዣበበብን የዘር ፍጅትና የሃገር መፍረስ አደጋ ወጥተን ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እንድትቀጥል ማድረግ ሁለተኛ ለዚህ ሁሉ ውጥንቅጥ መንስኤ የሆነውን የከፋፍለህ ግዛው አገዛዝና ህገ መንግስት ከመሰረቱ በመቀየር በህዝባዊ አስተዳደር መተካትና የኢትዮጵያን ህዝብ የሃገሩና የስልጣን ባለቤት ማድረግ ናቸው።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ በአገዛዙ ጊዚያዊ ማደናገሪያዎች ሳይዘናጋ አሁን ያለው የተረጋጋ የሚመስል  ነገር  ከማዕበሉ በፊት ያለ ፀጥታ(the calm before the storm)  በመሆኑ የትግሉ እድገት ደረጃ የፈጠረው  ሂደት እንጅ ውጤት አለመሆኑን ተገንዝቦ ትግሉን አጠናክሮ እንዱቀጥል ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
በመጨረሻም እኛ የኢትዮጵያውያን ሃገር አቀፍ (ኢሃን) መስራቾች የኢትዮጵያ ህዝብ በፓርቲዎች ተደጋጋሚ መፍረና መሰራት የልብ ስብራት እንደደረሰበት እንገነዘባለን። ይሁን እንጅ ባለፉ ስህተቶች ቁዘማና በከንቱ ምኞት የሚለወጥ ነገር እንደሌለና የሚመጣ ቁም ነገር እንደሌለ እንገነዘባለን።ካለንበት አዙሩት መውጣት የሚቻለው እየወደቁ እየተነሱም ቢሆን ለሃገራችን የእኩልነትና የነፃነት ጥያቄ የሚቻለውን አስተዋፆ ማድረግ ነው ብለን እናምናለን። ኢሃንን ስንመሰርት ለራሳችን የገባነው ቃል ኪዳንና የወሰድነው ኃላፊነት እጅግ ከባድ መሆኑን እንገነዘባለን።በመሆኑም ኢትዮጵያ እንደ ሃገር እንድትቀጥልና ህዝባችንም የሃገሩና የስልጣን ባለቤት እንዲሆን ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ለሚደረገው መራራ ትግል ሃገራችን የምትጥይቀንን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን።
የኢትዮጵያ ትንሳኤ በጀግኖች ልጆቿ መስዋዕትነት እውን ይሆናል!!!
Filed in: Amharic