>

የፖለቲካ ሴንተር ከመቀሌ ወደ ባህርዳር (ሚኪ አምሀራ)

የፖለቲካ ሴንተር ከመቀሌ ወደ ባህርዳር (Bahirdar the next political melting point) 
ሚኪ አምሀራ
በባለፉት 27 አመታት አዲስ አበባ የኢኮኖሚ ሴንተር መቀሌ ደግሞ የፖለቲካ ሴንተር ሁነዉ ቆይተዋል፡፡ትልልቅ የፖለቲካ ዉሳኔዎች መቀሌ ላይ ነበር የሚወሰኑት፡፡አሁን ባለዉ የፖለቲካ ዳይናሚክስ ባህርዳር ለሚቀጥሉት አመታቶች ከፍተኛ የፖለቲካ ትንቅንቅ የሚካሄድባት ከተማ ነች፡፡ ባጠቃላይ ኦሮሚያ አካባቢ የከራረመዉ ፖለቲካ በመቀዝቀዝ ነገር ግን የአማራ ፖለቲካ ካለበትም በላይ እየጦዘ ይሄዳል ማለት ነዉ፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይሄን ያዉቃሉ፡፡ ለዚህም ነዉ የአማራ ጉዳይ ራስ ምታት የሆነባቸዉ፡፡ ባህርዳር የፖለቲካ አዉድማ ለመሆኗ የሚከተሉት ምክንያቶች አሉ፡፡
አንደኛ ብአዴን እርስ በርሱ በሚያደርገዉ ፍትጊያ እዚህ ከተማ ላይ መከራረሙ አይቀርም፡፡ በዚህ አመት ብቻ አንኳን ከ 10 ጊዜ በላይ ተሰባስበዋል፡፡ በየጊዜዉ በቡድን እየተከፈሉ በሚያደርጉት እሰጣ እገባ ለእነሱ ብቻ ሳይሆን ለህወሃትም ራስ ምታት ሁኖታል፡፡ ህወሃት ብአዴን ዉስጥ ያለዉን ፓወር አጣ ማለት ከፍተኛ የፖለቲካ ቀዉስ ይገጥመዋል፡፡ ህወሃት ያን ያህል ጠንካራ ሁኖ አይደለም የኢትዮጵያን ፖለቲካ የሚዘዉረዉ፡፡ ነገር ግን ብአዴን ዉስጥ ባለዉ ስር የሰደደ ድርሻ እንጅ፡፡ ከዛም ባለፈ እራሱን ለኢትዮጵያ ህዝብ ደርግን የጣለ ጦረኛ አድርጎ ፍሬም አድርጎ ስሏል፡፡ ደርግን ግን የጣለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን ኢትዮጵያዊያን እራሱ የረሱት ይመስሉኛል፡፡ ስለ ረሱትም ሙሉ ለሙሉ ለትግራይ ህዝብና ለህወሃት ዉጤቱን አሸክመዉታል፡፡ ከዚህም በመነሳት ህወሃቶች ነገር ከረር ሲልባቸዉ እኛ ደርግንም የጣልን ነን ማንም አይነካንም ፉከራ ያሰማሉ፡፡ ያላወቁት ነገር ደርግን የጣለዉ የኢትዮጵያ ህዝብ መሆኑን ነዉ፡፡ አቅማቸዉ ጭንቅላታቸዉ ላይ እንደሳሉት አለመሆኑን ያወቁ አልመሰለኝም፡፡ ለፕሮፖጋንዳነት ግን እየተጠቀሙበት ነዉ፡፡
ሁለተኛ አዲሱ የአማራ ፓርቲም መቀላቀሉ ባህርዳርን ሌላኛዉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ጡዘት የሚካሄድባት ከተማ ያደርጋታል፡፡ አዲሱ ፓርቲ ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ ይኖረዋል፡፡ ብዙዉ ወጣትና ሙሁር ይሄን ፓርቲ ይቀላቀላል፡፡ ይህ ፓርቲ ትልቁ ተግዳሮት ሊሆን የሚችለዉ ይህን የሰዉ ሃይል እንዴት ሃንድል ያደርገዋል የሚለዉ ነዉ፡፡ በአቅም ክፍተት፤ በልምድ እጥረት እና በተደራሽነት ጉዳዮች ይሄን ሁሉ ህዝብ ማስተናገድ ሊከብደዉ ችላል፡፡ በዚህ ዉስጥ ከብአዴን ጋር ፍትጊያዉ ይቀጥላል፡፡ ባህርዳር በዚህ ፍትጊያ ዉስጥ ዘንባባወቿ ሊሰባበሩ ይችላሉ፡፡ ብአዴን እስካሁን እንደምንሰማዉ በሁለት ጎራ የተከፈለ ነዉ፡፡ ህወሃትን የሚደግፍና የማይደግፍ ቡድን፡፡ በሚቀጥለዉ ደግሞ ይህ አዲሱ የአማራ ፓርቲ ፖለቲካዉን ሲቀላቀል እንዴት ባለ መንገድ እናስተናግዳቸዉ በሚል ሌላ ንትርክ ዉስጥ መግባቱ አይቀርም፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ኦህዴድ አሁን ባለዉ አቅም ብቻዉን አገር ሊመራ አይችልም፡፡ ፖለቲካዉንም፤ ሚሊታሪዉን፤ ደህንነቱን እና መሰል አካባቢዎችን እንደ ህወሃት ተቆጣጥሮ ሊያስኬደዉ አይችልም፡፡ የልምድ ማነስ እና የአቅም እጥረት ያጋጥመዋል፡፡ ይህን የልምድ ማነስና የአቅም እጥረት ክፍተት ህወሃት ለመጠቀም ስለሚሞክር ኦህዴድ አጋር ያስፈልገዋል፡፡ አሁን አጋሬ ብሎ ብአዴንን ለይቶ ይዟል፡፡ ኦህዴድም ከብአዴን ወስዶ የሾማቸዉ ሰወች ህወሃትን የማይደግፉ ብሎ ገምግሞ ነዉ፡፡ ለምሳሌ እነ ዶ/ር አምባቸዉን ጃንጥራርንና ሌሎችንም ሲወስድ በዚህ ቀመር ነዉ፡፡ ባንጻሩ የህወሃት ደጋፊ ያላቸዉን እነ ጌታቸዉ አምባየን አንስቷል፡፡ አለምነዉን በየአመቱ ግንቦት 20 በመጣ ቁጥር የመለስ ራእይ የሚል የመወያያ ሃሳብ ትምክህትና ጠባብነት የስራአቱ አደጋወች ናቸዉ የሚል ብቻ እየጻፈ እንዲያቀርብ የሆነ ቢሮ ዉስጥ ነዉ የገባዉ፡፡ ሰሞኑንም ይህን ጽፎ አቅርቧል፡፡ ስለዚህም ኦህዴድ እራሱ ወደ ባህርዳር መመላለሱ አይቀርም፡፡ አንደኛ ፖለቲካዊ ዉሳኔዎችን ለመወሰን ሁለተኛ በብአዴን ዉስጥ ችግር ሲፈጠር እንደ ሽማግሌ ሆኖ ለማስማማት፡፡
አራተኛ ህወሃትም በተደጋጋሚ ከመቀሌ ወደ ባህርዳር መመላለሱ አይቀርም፡፡ አንደኛ ብአዴን ዉስጥ ያለዉን ፓዎር እንዳያጣ ሽማግሌ በመምሰል በየስብሰባወቹ መገኘቱ አይቀርም፡፡ ሁለተኛ ኦህዴድ ሀገራዊ የፓለቲካ ጉዳዮችን መቀሌ ሄዶ ከመወሰን ባህርዳር ሄዶ መወሰን ይቀለዋል፡፡ ባህርዳር ላይ ቢያስወስን ሌጅትማሲ ያገኛል፡፡ ህዝቡ መቀሌ የሚል ሰም ሲሰማ ስለሚያንገሸግሸዉ ትክክል የሆነ የፖለቲካ ዉሳኔ እኳን መቀሌ ላይ ተወሰነ ቢባል  ተቀባይነት የለዉም፡፡ጠቅላይ ሚኒስትሩ በራሱ በተደጋጋሚ መቀሌ አካባቢ ከታየ ህዝቡ በጥርጣሬ እንደሚያየዉና አሁን ያለዉን መጠነኛ ድጋፍ ሊያጣ ይችላል፡፡ ስለዚህም ዶ/ር አብይ ባህርዳር በተደጋጋሚ መታየቱ አይቀርም፡፡
አምስተኛ የአማራ ብሄርተኝነት ነዉ፡፡ የአማራ ብሄርተኝነት አሁን ባለዉ ሁኔታ ባሀርዳርን እየናጣት ነዉ፡፡ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ደግሞ እጅግ ከብዶ እና ገዝፎ የሚቀርብ ይሆናል፡፡ እየተስፋፋ የመጣዉ የአማራ ብሄርተኝነት የባህርዳርን ፖለቲካ ሴንተር የሚያቀጣጥል ይሆናል ማለት ነዉ፡፡ በእርግጥ ከዚህ በፊት እንዳልኩት የአማራ ብሄርተኝነት ወደ አዲስ አበባ ቢሻገር የተሻለ ይሆናል፡፡ ከሚታሰበዉ በላይ በፍጥነት የሚፈለገዉን ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ለዉጥ ማምጣት ከተፈለገ የአማራ ብሄርተኝነት ቁልፉ እና ቆጣሪዉ አዲስ አበባ ላይ መተከል አለበት፡፡
አዲስ አበባ የኢኮኖሚ ሴንተር አንደሆነች ትቀጥላለች፡፡ ባህርዳር ግን የፖለቲካ ማእከል ሁና መከራረሟ አይቀሬ ነዉ፡፡
Filed in: Amharic