>

የአዳማ ነጋዴዎች በማስታወቂያ ሰሌዳዎች ላይ የተወሰደውን እርምጃ ተቃወሙ (ኣዲስ ኣድማስ)

ማስታወቂያዎቹ በአንድ ሳምንት ውስጥ ካልተስተካከሉ ሰሌዳ መንቀል ይጀመራል

“አማርኛን ከክልሉና ከከተማው ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት ነው” ነጋዴዎች

“ብሔሮችን እርስ በርስ ለማጋጨት ሆን ተብሎ የሚነዛ አሉባልታ ነው” የከተማዋ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ

ለንግድ ድርጅቶቻቸው በሰቀሏቸው ማስታወቂያዎች ላይ የተወሰደው በቀይ ቀለም የማበላሸት እርምጃ ህገወጥ ነው ያሉት የአዳማ ከተማ ነጋዴዎች፤ በማስታወቂያዎቹ ላይ “ኦሮምኛ ፊደላት አነሱ” በሚል ሰበብ አማርኛን ከክልሉና ከከተማው ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ እርምጃውን ተቃወሙ፡፡ የአዳማ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በበኩሉ፤ አብዛኛዎቹ ማስታወቂያዎች ያለባቸው እግር እንዲስተካከል በተለያየ መንገድ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁሞ፣ ነጋዴዎቹ እርማት ለማድረግ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በ900 ማስታወቂያዎች ላይ በቀይ ቀለም የ“X” ምልክት ማድረጉን ለአዲስ አድማስ ገልጿል፡፡ ማስታወቂያዎቹ በአንድ ሳምንት ውስጥ ካልተስተካከሉ ሰሌዳዎችን የመንቀል እርምጃ ይወስዳል ብሏል ቢሮው፡፡ “ለረጅም አመት የተጠቀምንበትን ማስታወቂያ ዛሬ ምን አዲስ ነገር ተገኝቶ ነው ብልሽትሽቱን የሚያወጡት” ያለው አንድ ወጣት ነጋዴ፤ እርምጃው አማርኛን ከክልሉና ከከተማው ለማጥፋት የሚደረግ ጥረት ነው ሲል ነቅፏል፡፡

ከዚህ ቀደምም ቢሮው ከዘጠኝ ሺህ በላይ የማስታወቂያ ሰሌዳዎችን ከየንግድ ቤቱ ነቅሎ ወስዶ የት እንዳደረሰው አይታወቅም ብለዋል ሌላው የአዳማ ነጋዴ፡፡ “ነጋዴው ህግና ስርዓትን ተከትሎ እየሰራ ለመንግስት ተገቢውን ግብር እየከፈለ ነው” ያሉት አንድ አስመጪና ላኪ በበኩላቸው፤ “የአማርኛ ፊደል በዛ፣ የኦሮምኛው ደቀቀ እያሉ መጥፎ መንፈስ የሚዘራ ስራ ከመስራት ህገ ወጥ ንግድንና ነጋዴን ስርዓት በማስያዝ፣ ለምን ጤናማ የንግድ ውድድር እንዲፈጠር አያደርጉም?” ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ “ነጋዴው የማስታወቂያ ሰሌዳውን በውድ ዋጋ አሰርቶ እንደሚያቆመው እየታወቀ ያለማስጠንቀቂያ በቀይ ቀለም ማበላሸት ነጋዴውን ለመጉዳትና ሞራሉን ለመንካት ሆን ተብሎ የተወሰደ እርምጃ ነው” ያሉት ሌላ ነጋዴ፤ ማስታወቂያውን ለማበላሸት የወጣው ቀይ ቀለም ለመንግስትም ቢሆን ኪሳራ ነው ብለዋል፡፡

ላለፉት 28 ዓመታት በንግድ ስራ ላይ እንደቆዩ የጠቆሙ አንድ ነጋዴ እስከዛሬ፣ ከማስታወቂያ ጋር በተያያዘ ያየሁት አንድም ችግር የለም በማለት የአሁኑ ፖለቲካዊ ዓላማ ሊኖረው ይችላል ሲሉ ግንታቸውብ ሰንዝረዋል፡፡ “ጉዳዩ በቅርቡ ከተነሳው የተማሪዎች አመፅ ጋር የተያያዘና አንዳንድ ወገኖች ለአማርኛ ቋንቋ ያላቸውን ጥላቻ ለማሳየት የተጠቀሙበት አጋጣሚ ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል – ነጋዴው፡፡ የአዳማ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘውዴ የሺጥላ በበኩላቸው፤ በየንግድ ቤቱ በር ላይ የተሰቀሉት ማስታወቂያዎች መሰረታዊ ችግር እንዳለባቸው ጠቅሰው ከእነዚህም ውስጥ የመጀመሪያው በኦሮምኛ ቋንቋ የተፃፉት ሁሉም ማስታወቂያዎች በጣም ደቃቃና ለማንበብ አስቸጋሪ መሆናቸው ነው ብለዋል፡፡ ሁለተኛው ችግር የአማርኛውን ቃል ወደ ኦሮምኛ አስተርጉመው ሲፅፉ የትርጉም መፋለስ ማስከተሉ የክልሉ የስራ ቋንቋ ኦሮምኛ በመሆኑ የተፋለሰውን እንዲያስተካክሉ እርምጃው መወሰዱን ተናግረዋል፡፡

ከሚያዚያ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ባህልና ቱሪዝም ቢሮው የማስታወቂያ ፅሁፋቸውን እንዲያስተካክሉ በኦሮሚያ ቴሌቪዥንና በተለያዩ መንገዶች ጥሪ ሲያደርግ መቆየቱን የጠቆሙት አቶ ዘውዴ፤ ነጋዴዎች ይህን የማስተካከያ እርምጃ ለመውሰድ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ከዘጠኝ መቶ በላይ በሆኑ ማስታወቂያዎች ላይ በቀይ ቀለም የ “X” ምልክት መደረጉን ተናግረዋል፡፡ “ነጋዴዎቹ በአንድ ሳምንት ውስጥ የተጠቀሱትን ችግሮች ለማስተካከል ካልቻሉ ቀጣዩ እርምጃ ማስታወቂያዎቹን መንቀል ይሆናል” ያሉት የቢሮው ሃላፊ፤ ባለፈው ዓመትም ማስታወቂያዎችን በተደጋጋሚ አስተካክሉ ብለን ፈቃደኛ ባለመሆናቸው፣ ቢሮው ከ10 ሺህ በላይ ማስታወቂያዎችን ነቅሎ ከወሰደ በኋላ፣ አስተካክለው እንዲወስዱ ጥሪ ቢያደርግም የመጣ ባለመኖሩ የማስታወቂያ ሰሌዳዎቹ ለመንግስት ገቢ ተደርገዋል ብለዋል፡፡ አማርኛን ከክልሉ ለማጥፋት ጥረት እየተደረገ ነው የሚለውን የነጋዴዎች ቅሬታ በተመለከተም፤ “የክልሉ የስራ ቋንቋ ኦሮምኛ በመሆኑ በአግባቡ ተጠቀሙ አልን እንጂ አማርኛን አትጠቀሙ አላልንም” ያሉት አቶ ዘውዱ፤ ይሄ ሆነ ተብሎ ብሄሮችን እርስ በእርስ ለማጋጨት የሚነዛ አሉባልታ ነው ሲሉ አጣጥለውታል፡፡

“ ጉዳዩን ከሰሞኑ የተማሪዎች ብጥብጥ ጋር ለማገናኘት መሞከሩም ብዙ ርቀት የማያስኬድ የፅንፈኞች አሉባልታ ነው” ብለዋል – ሃላፊው፡፡ የአዳማ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በአዋጅ ከተሰጠው ስልጣን አንዱ የክልሉን ባህል፣ ቋንቋና ትውፊት ሳይበረዝና ሳይበላሽ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሆነ የጠቆሙት አቶ ዘውዱ፤ አሁን እየተደረገ ያለው ግን ቋንቋና ባህልን ማበላሸት ነው ብለዋል፡፡ ‹ሚኒ ማርኬት› የሚለውን ማስታወቂያ በኦሮምኛ የላቲን ቁቤ ‘ሚኒ ማርኬት’ ብለው ሲያስቀምጡት ‘ሚኒ’ የሚለው ቃል በኦሮምኛ አስነዋሪ ቃል ስለሆነ፣ ‹ይህን አስተካክሉ› ብሎ መንገር ወደ ሌላ ነገር መተርጎም የለበትም ያሉት ሃላፊው፤ እስካሁን ምልክት ከተደረገባቸው ከዘጠኝ መቶ ማስታወቂያዎች ውስጥ 300 ያህሉ ማስተካከያውን እንዳደረጉ ጠቁመው፤ ሌሎቹም እንዲያስተካክሉ እየተጠበቁ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ከአንድ ሳምንት በኋላ ሰሌዳ የመንቀል እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቀቀዋል – የቢሮው ሃላፊ፡፡

Filed in: Amharic