>

ኢትዮጵያችን የሰርግና የለቅሶ ድንኳን የተጣሉባት ሰፈር ሆናለች! (ዘውድአለም ታደሰ)

ያኔ በቀውጢው ግዜ ኦሮሚያ ላይ በመንግስት ታጣቂዎች ህዝቡ ላይ የደረሰውን በደል ሳልደክም የተቃወምኩት ኦሮሞ ስለሆንኩ አልነበረም። ቲም ለማን በምችለው አቅም የደገፍኩት ኦሮሞ ስለሆንኩ አልነበረም። ዶክተር አብይ ወደስልጣን ሲመጣ ደስ ያለኝ ኦሮሞ ስለሆንኩ አልነበረም። ኢትዮጵያዊ ስለሆንኩ እንጂ!!

አሁን ግን ኢትዮጵያ የሰርግና የለቅሶ ድንኳን የተጣሉባት ሰፈር ሆናለች! ኦሮሚያ ነፃነቷን ተቀናጅታ ወደተረጋጋ ሁኔታ ስትመለስ አማራው ግን ከኦሮሚያ ጭምር እየተፈናቀለ እየተገደለ በሀገሩ ባይተዋር ሆኗል! አሁን ከ መጋቢት ወር ጀምሮ ራሱ ከሶስት ሺ አማሮች በላይ ከኢልባቦር ክልል ተፈናቅለው በየቦታው ተበትነዋል።
ጌታቸው ሽፈራው በገጹ ላይ ይህን አስፍሯል
“..አዲሶቹ ተፈናቃዮች ኢሉ አባቦራ፣ በደሌ-77 ከሚባል ቦታ የተፈናቀሉት አማራዎች ባህርዳር የሚገኙት 64 ግለሰቦች ብቻ ናቸው። ቤተሰቦቻቸው ተበትነዋል! ቤታቸው ተቃጥሎባቸዋል። ንብረታቸው ተወርሷል። ወድሟል።
– የተገደለ፣ እጁን የተቆረጠ እና ቤቱ ውስጥ የተቃጠለም እንዳለ ተፈናቃዮቹ ገልፀዋል
~ከአካባቢው የተፈናቃሉት በሺዎች የሚቆጠሩ ሲሆኑ የአካባቢው የመንግስት አስተዳደር ምንም አይነት ጥበቃ ወይንም እገዛ አላደረገላቸውም። እንዲያውም እንዲፈናቀሉ እያደረገ ያለው የአካባቢው የመንግስት/ኦህዴድ መዋቅር እንደሆነ ገልፀዋል።
~ባህርዳር የገቡት ዛሬ 13/2010 ዓም ሲሆን ብአዴን የባህርዳር ጎዳናዎች ላይም እንዳያድሩ በፖሊስ እያስነሳቸው ነው። በማለት ነው ሁኔታውን ከብዙ በጥቂቱ የገለጸው።

ኢትዮጵያ ሱሴ ምናምን ሲል የነበረው ለማ ምንም ያለው ነገር የለም። ጠቅላይ ሚኒስትሩም አሁን ያለውን አንገብጋቢ ጉዳይ ችላ ብሎ የታክሲ ሰልፍ ላይ ለሴቶች ቅድሚያ ስለመስጠት እየደሰኮረ ነው!!
አማራ ኢትዮጵያ እያለ እንደበግ የታረደ፣ ምስኪን ህዝብ ነው። ሌላው ዘረኝነትን ከጡጦ ጋር እየጋተ ልጆቹን ሲያሳድግ እሱ ግን ባንዲራውን እንደሸማ አልብሶ ባህልና ታሪኩን ለልጆቹ እያስተማረና ኢትዮጵያ የሚሏትን (አሁን እንደጤዛ ተንና የጠፋች ሐገር) በልቡ ውስጥ እየሳለ ያሳደገ የመታረጃውን ቀን እያወቀ ፀጥ ብሎ የጠበቀ ህዝብ ነው።

ልክ እንደትናንቱ ዛሬም ይሄ ህዝብ ጨቋኝ ፣ በዝባዥ ፣ ነፍጠኛ ፣ እየተባለ ሁን ተብሎ በሃብት እንዳይደረጅ ፣ በእውቀት እንዳያድግ፣ በህዝብ ቁጥር እንዳይበዛ፣ በመልክአምድር እንዳይሰፋ፣ ሲዶለትበት ኖሯል!! ለዚህ ሁሉ በደል ግን አማራው ከዝምታ ውጪ መልስ አልሰጠም። በተለይ በከተማ የሚኖረው ከአማራው አብራክ የወጣው ወጣት ከኢትዮጵያዊነት ከፍታ ላለመውረድ ሲፍገመገም ከርሟል።
አማራ እኛ እንጂ እኔ የሚል ነገር አይገባውም ነበር። ለዚህ ነው ኦሮሚያ ከሜጫና ቱለማ ጀምሮ ብሄር ላይ የተደራጁ ልጆች ስታፈራ፣ ኤርትራ እነጀብሃን ከጥንት ስትመሰርት፣ ትግራይ ህውሃትን ስታቋቁም፣ አማራው ግን በብሄር መደራጀትን ተፀይፎ ቁጭ ብሎ ይታዘብ ነበር። (ብአዴን እንኳ የተቋቋመው ጦርነቱ ካበቃ ወዲህ መሆኑን ልብ ይሏል)

አሁን ግን አማራው አይን ላይ የታሰረው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያለው ሸማ ቀስ በቀስ እየተፈታ ነው። አማራው ብሔርተኝነትን አማራጭ እንደሌለው የህልውና ማስቀጠያ መንገድ ማየት ጀምሯል። ሁሉም በጎጥ ውስጥ ተደራጅቶ አማራው ኢትዮጵያ እያለ የሚገደልበት ዘመን እያበቃ ነው። ከዚህ በኋላ የሚታይና የሚጨበጥ ለውጥ ካልመጣ በስተቀር አማራው ከያዘው ራስን የማዳን ጉዞ ወደኋላ መመለስ አይኖርበትም። ኢትዮጵያ የሚሏት ሐገር ከአባቶቻችን ጋር እንደተነነች ከዚህ ዘመን በላይ ማረጋገጫ የለም። አዲሱ የለማ ቲምም ሆነ ዶክተሩ በጅላንፎው ብአዴን ላይ ተንጠልጥለው ከተሳካላቸው ወዲህ ሳይውሉ ሳያድሩ አማራውን ከንብረቱ እያፈናቀሉና እያባረሩ ያባቶቻቸውን ራእይ እያስፈፀሙ ይገኛሉ!! (አሁን ላይ በኦሮሚያ ክልል ለሚፈፀም የማፈናቀል ስራ መቼም ከሁለቱ ውጪ ማንንም ተጠያቂ አናደርግም)

አማራው ከዚህ በዃላ አንድ ምርጫ አለው!! መደራጀትና አንድ በመሆን ከተቃጣበት ጥቃት ራሱን ማዳን ብቻ!!! ለዚህ ደግሞ እኔን ጨምሮ ብዙ ወጣቶች ከቻልን ኖረን ፣ ካልቻልን ደግሞ ሞተን የነፃነቱን መንገድ በደማችን ለማጠብ ዝግጁ ነን!!!

በቃ!!

Filed in: Amharic