>

በአንድ ወቅት የኦነግ ብሬይን የነበሩ ሰዎች ወደፊንፊኔ እየሄዱ ነው!?! (ፍቃዱ ሞረዳ)

አቶ ሌንጮ ለታ (የኦነግ  ዋና ፀሀፊ የነበሩ)
ዶ/ር ዲማ ናጎ (የኦነግ ሊቀመንበር የነበሩ)
ዶ/ር በያን አሶባ (የኦነግ ቃል አቀባይ የነበሩ)
ዶ/ር ሀሰን ሁሴን (የኦነግ አመራር አባል የነበሩ)
አቶ ሌንጮ ባቲ ( የኦነግ ቃል አቀባይ የነበሩ)
  እነዚህ ሰዎች ፈረንጅ ሀገር ሊያኖራቸዉና እንጀራ ሊያበላቸዉ የሚችል እዉቀት የላቸዉም፤ ለኢትዮጵያ ፖለቲካም ሆነ ለኦሮሞ ጥያቄ አላዋቂዎች ናቸዉ፤ ሕዝቡን ሸጠዉ የተቀማጠለ ኑሮ ለመኖር ነዉ ወደሀገር ቤት የሚገቡት… ሊባሉ ይችላሉ፡፡ እየተባሉም ናቸዉ በአንዳንዶች፡፡ ‹‹ ሆድ ሲያዉቅ ዱሮ ማታ…›› እንዲሉ፡፡
    ወዲህም አለ፡፡ የኢሕአዴግ አገዛዝ ‹‹ምን የተለየ ነገር በተግባር አሳይቶ፣ ምን ለዉጥ መጥቶ ነዉ ዘልሎ የተገባዉ? ›› የሚሉ ገራገር መሳይ ጥያቄዎችም አሉ፡፡
    አባዜዬ እንደሚነግረኝ፣በእብዶች አዋጅ በአሸባሪነት ከተፈረጁት በኦቦ ዳዉድ ኢብሳ ከሚመራዉ ኦነግና ከአርበኞች ግንቦት ሰባት በስተቀር ወይም በፍርድ ቤት የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዉ የመያዣ ትዕዛዝ ከወጣባቸዉ በስተቀር  ስም ጎዝጉዞ በየስደቱ ዓለም መንቀሽረር ላይ ያለዉ ሁሉ ወደሀገሩ ቢገባና ቢታገል ምን አለበት? ባይታገልስ? የሰላም ኑሮን በሀገሬ ልኑር ቢልስ? ማን ነን እኛ በግለሰቦችና በቡድኖች የግል ዉሳኔ ላይ ጣት ለመቀሰር የሞራል ሥልጣን ያለን?
 እነዳዉድም ሆኑ እነብርሃኑ የጦርነት ሱስ ኖሮባቸዉ ወይም መሞት አምሯቸዉ ጫካ /በረሃ አልገቡ፡፡ በሰላማዊ መንገድ ፍላጎታቸዉ መሰማት፣ ጥያቄያቸዉ መደመጥ ባለመቻሉ ነዉ ሌላ አማራጭ (ምናልባትም አደገኛ አማራጭ) ዉስጥ የገቡትና መከራቸዉን የሚያዩት፡፡
   ሌላዉ ግን ከዉጪ ምን ይሠራል?   ትንሽ ቀዳዳ ከተገኘች በዚያች ሸልኮ በመግባት ዕድሎችን ማስፋት፣ የተገለሉትም ወደክብ ጠረጴዛ የመጋበዝ ዕድል በሚያገኙበት ጉዳይ ላይ መደራደር፣ መሟገት… ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነመረራ ጉዲና የትኛዉ ምቹ ነገር ተዘጋጅቶላቸዉ ነዉ ዋጋ ሲከፍሉ የኖሩት? አሁንም ለመክፈል የተዘጋጁት? ወጣት የሕዝብ ልጆች ደረታቸዉንና ግንባራቸዉን ለጥይት፣ እጃቸዉንና እግራቸዉን ለእስራት እየሰጡ ያሉት ‹‹ምቹ ሁኔታ›› እስኪፈጠርላቸዉ መጠበቅ ጠፍቷቸዉ ነዉ?  ያለትግል የሚገኝ ምቹ ሁቤታ አለመኖሩን፣ ትርጉም ያለዉ ትግል ማድረግ ደግሞ በሕዝብ ዉስጥ ሆኖ መሆኑን በማመናቸዉ እንጂ፡፡
ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ሆኖ፣ መንግሥት በየፈረንጁ ሀገር እየዞረ በተቃዋሚዉ እግር ላይ እየወደቀ ለምኖ፣ በሀገሪቱ ዉስጥ ከሰማይ የወረደ ነፃነትና ዲሞክራሲ ሰፍኖ፣ ከቦሌ እስከ ቤተመንግሥት ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎ… አቀባበል እስኪደረግላቸዉ የሚጠብቁ ካሉ እነርሱ ፖለቲከኞች ሳይሆኑ ቴአትረኞች ናቸዉ፡፡
  ይልቅስ አቃቂር ማዉጣቱን፣ ሰበብም መደረቱን ትተን ወደሕዝባችን እንሂድ፡፡ ትግሉ ሀገር ቤት ይግባ፡፡ ሀገር ቤት ዋጋ እየከፈሉ ያሉትን በአቅማችን ሄደን እናግዝ፡፡
   የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባርን ተከትለዉ፣ በጄኔራል ኃይሉ ጎንፋ፣ በጀኔራል ከማል ገልቹ ፣ በአቶ ገላሳ ድልቦ የሚመሩ የኦሮሞ ድርጅቶችም በቅርቡ ወደሀገር ገብተዉ ከእነመረራ ጉዲናና ለማ መገርሳ ጋር ተቀምጠዉ ቡና እንደሚጠጡ ተስፋ ይደረጋል፡፡
  በትጥቅ ትግል ጎራ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉ ወንድሞቼና እህቶቼም ለሠላማዊ ትግል ከቤተሰቦቻቸዉ ጋር በሠላም የሚገናኙት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተስፋ እያደረግን፣ እስከዚያዉ ግን ሀገር ቤት ካሉት ጋር ግንኙነትን በመፍጠር ወይም የተፈጠረዉን በማጠንከር እንደሚሰሩ እናስባለን፡፡ ሁላችንም የምንናፍቀዉን ቀን፣ የምንናፍቃትን ሠላምና ነፃነት የሰፈነባትን ሀገር የምናይበት ጊዜ ሩቅ አለመሆኑን ብናስብ ምን ይለናል? ከመወነጃጀሉና ከአቃቂሩ ይልቅ፡፡ ወደሀገራቸዉ
እየገቡ ላሉት የሠላም መንገድ ይሁን፡፡ ውጭ ለቀሩትም ሆነ ለአገዛዙ ሥርዓት ሰዎች ድፍረትንና ቅን ልቦናን ይስጥ፡፡እስቲ በጎ በጎዉን እናስብ፡፡ አይጎዳንም፡፡ለዛሬዉ አሜን!
Filed in: Amharic