>

ከአክሱም ሀውልት የረዘመ፣ ከፋሲል ግንብ የሰፋ ብረት ያላሰረው ክቡድ-መንፈስ (ከጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

    …በመሀል አዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ፊት-ለፊት ባለው የደህንነት ዋና መስሪያ ቤት ህንፃ ላይ የሚገኘውና ሙሉ የክፍሉ ግድግዳ ዘመን-አፈራሽ ቴክኖሎጂ በተገጠመላቸው ኮምፒዩተሮች የተገጠገጠው፣ ከሃያ የዘለሉ እንደ አገልግሎታቸው በተለያየ ቀለም የተሽሞኖሞኑ የስልክ መስመሮች በተደረደሩበት ቁንጮ-ሹም ጌታቸው አሰፋ ቢሮ ውስጥ ጥቂት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ለአስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጠዋል፤ የአጀንዳቸው ጭብጥም ለጊዜው ስሙን ከማልገልፀው ከአንድ ሀያል አገር የስለላ ተቋማ የደረሳቸውን መረጃ በመጠቀም በመስሪያ ቤቱ ታሪክ “ታላቅ” በሆነው ተልዕኮ ላይ እንዴት፣ በምን መልኩ፣ እነማን ይሰማሩ? የሚሉ ጥያቄዎችን ለመመለስ ነበር።
      የስብሰባውን ውሳኔ  ተከትሎም ከባህር  ዳር አየር ምድብ በመነሳት ደብረዘይት ያረፈው አንቶኖቭ አዎሮፕላን ለዓለም አቀፍ በረራ መሰናዶውን አጠናቅቆ ተጓዦቹን እየጠበቀ ነው፤ የደህንነቱ መስሪያ ቤት ምክትል ዳይሬክተር  ኢሳያስ ወልደ ጊዮርጊስ እና የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊው መኮንንን (በቅፅል ስሙ ወዲ ኮበል) ጨምሮ በኮድ ለተሰየመው ለዚህ ኦፕሬሽን  “ብቁ” የተባሉ አስር ሲኒየር አባላቱ በሰዓቱ ደርሰው ተሳፈሩ፤ አንቶኖቩም ሞተሩን ቆስቁሶ መንደርደሪያውን ጨርሶ፣ አፍንጫውን ወደ ሰማይ ቀስሮ  ሽቅብ ተመዘገዘገ፤ የሀገሪቱን ሰሜናዊ ድንበር አቆርጦ ቀይ ባህርን ተሻግሮ በሰንዓ ሰማይ ላይ ለጥቂት ደቂቃዎች ያህል ካንዣበበ በኋላ አንድ የአየር ኃይል ሜዳ ላይ ማረፉን ጉዳዩን ከሚያውቁ የየመን የፀጥታ መኮንኖች በስተቀር ያስተዋለው አልነበርም፤ በከፍተኛ ሚስጢር የተያዘው ተልዕኮም ያለአንዳች እንቅፋት ተከናውኖ፣ የመልስ ጉዞውንም  ኮሽታ ሳያሰማ በመጣበት አኳኋን ጀምሮል፤ የዘመቻው ዋና መሪ ኢሳያስም ሆነ ሰላዮቹ በድል አድራጊነት ስሜት ተኮፍሰዋል። በግልባጩ ቀን ፊቷን ያዞረችበት ምርኮኛ ሁለት እጆቹን በካቴና እንደታሰረ ጥልቅ ዝምታ ውጦታል፤ መቼም በርካታ ጉዳዮች በአዕምሮው እየተመላለሱ ሳይረብሹት አልቀረም። በተለይም ከምስራታው  አንስቶ በዳገት-ቁልቁለቱ የለፋበት ድርጅትን መፃኢ-እድል ሲያስበው ብርቱ ሀዘን አጥንቱ ደረስ ዘልቆ ይመዘምዘዋል፤  ያገጠመውን ክፉ ዕጣ ጓዶቹ አለመስማታቸውም  ሆነ ለጠላቶቹ አሳልፎ የሰጠውን ይሁዳ አለማወቁ ተጨማሪ ራስ-ምታት ሆኖበታል፤  ተወልዶ ያደገበት፣ ፖለቲካን “ሀሁ… ” ብሎ የቆጠረበት፣ “መሬት ላራሹ” እያለ በጩኸት የናጣት፣ የኢሕአፓን ወረቀት የበተነባት፣ “ሕዝባዊ መንግስት አሁኑኑ”ን ያቀነቀነባት፣ “ሶሻሊዝም ወይም ሞት” ያለባት፣ “ትግሉ ህይወቴ ነው”ን የዘመረባት፣ በቀይ ቀለም መፈክር ያሸበረቃት፣ የመገናኛ ኮድ የተቀበለባት-ያስተለለፈባት፣ እስኳድ ሆኖ በኮልት ሽጉጥ ደርግን ያሸበረባት፣ ህቡዑ ገብቶ ከጥይት የተረፈባት፣ በውድቅት  ሌሊት ሾልኮ የጠፋባት፣ ገዥዋ ሆኖ ያገለገላት፣ እንደገና ጥሎት የኮበለለባት፣ ተመልሶ በምርጫ ፖለቲካ የነቀነቃት፣ ተገርፎ-የታሰረባት፣ ሌላ ህልም ሰንቆ ለሌላ ቀን ቀጠሮ ይዞ የተሰናበታት ውቧ ሸገር ቅስም-ሰባሪ መርዶዋን ገና አልሰማችም፣ አዬ ጉድሽ አዲስ አበባዬ!!!
ካለፉት ሶስትና አራት አመታት  ወዲህ የደህንነት  መ/ቤ የግንቦት ሰባት ዋና ፀሀፊ አንዳርጋችው ፅጌን ቁጥር አንድ የተፈላጊ ማዕረግ ሰጥቶ በጥብቅ መከታተሉ የአደባባይ እውነታ ቢሆንም፤ ከእነ ህይወቱ በቁጥጥር ስር አውለዋለሁ ብሎ ግን ጭራሽ አላሰበም። መስሪያ ቤቱም ለእንዲህ አይነቱ ረቀቅ-ያለ ኦፕሬሽን የራሱን አልቦ-ብቃት ጠንቅቆ ያውቀዋል፤ ሌላው ቀርቶ ቢሮውን እንደ ግል እልፍኙ ይምነሸነሽበት የነበረው ወዲ ዜናዊ ተቋሙ ፍጡነ-ረድኤት እንዳልሆነ ከተረዳ ውሎ-አድሯል፤  ተሞክሮውም በጣት የሚቆጠሩ ሽምቅ-ተዋጊዎችን ከሱዳን እና ኬንያ የፀጥታ ሠራተኞች በ”ግዥ” አፍኖ ከማምጣት ያለፈ አይደለም። አንዳርጋቸውን በተመለከተም ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው በሰርጎ ገብ አሊያም የገዛ አባለቱን በገንዘብ በመደለል ድንገት ባልጠበቀውና ባልጠረጠረበት ክፉ ቀን የጥይት-ራት ማድረግ እንደነበር የመረጃው መስሪያ ቤት የቅርብ ሰዎች ይናገራሉ፤ ህወሓት-መራሹን መንግስት እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰው ገፊ-ምክንያት በ2001 ዓ.ም ወርሀ ሚያዚያ “ግንባት ሰባት” ከጦር ሰራዊቱ መኮንኖች እና ሲቪሎች ጋር በመተባበር የመፈንቅለ መንግስት ሞከራ ማድረጉ የፈጠረበት አቅል-አሳች ድንጋጤ እንደሆነም ይገመታል።
     ንቅናቄው ምስረታውን ባበሰረበት ወቅት የሚከተለውን የትግል ስልት “ሁለ-ገብ” ብሎ ቢገልፅም፣  ቀዳሚው ከጠብ-መንጃ ጋር መያያዙና የአመራር አባላቱ ነዋሪነት አሜሪካና አውሮፓ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በገዥው-ፓርቲ ሰፈር “ቀልደኞች” ተደርገው መወሰዳቸውን አስታውሳለሁ፤ በዚህች አገር ሰማይ ስር ዳግም “ተራሮችን ሊያንቀጠቅጥ” የሚችል በረት-ነካሽ ትውልድ  እንደማይፈጠር የታበዩት መለስ ዜናዊና ጓዶቹ የግንባት ሰባት መስራቾችን ‘የማክዶናልድ ታጋይ’፣  ‘የኋይታ ሀውስ ሰልፈኛ’፣ የትርፍ ሰዓት ፖለቲከኛ’ እያሉ መሳለቃቸውም በከተማው የናኘ ወሬ ነበር፤ ግና ይህ ድምዳሜ እብሪት የወለደው ስሁት መሆኑን ለመረዳት ከአንድ አመት የገፋ አላስጠበቃቸውም። የጉብዝናውን ወራት ኢህአፓ ከከተማ እስከ በረሃ በዘረጋችው የትግል ስልት ተፈትኖ ማለፉ የካበተ-ልምድ ያስጨበጠው አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ከጄነራሎቹ፣ ከኮሎኔሎቹ እና የሰቪሉ ተወካይ ጋር በአለማችን ቅንጡ ከተሞች:- ሮምና ዱባይ ደጋግሞ ከመከረ በኋላ ምንም እንኳ ከክሽፈት ባይድንም መጪውን ጊዜ ጠቁሞ ያለፈው መፈንቅለ-መንግስት እውን እንዲሆን አበርክቶውን ተውጥቷል።
   …አንቶኖቩ ከሁለት ሰዓት የበረራ ቆይታ በኃላ የሰነዓ ምርኮኛውን ደብረ-ዘይት አየር ኃይል ግቢ አድርሶ ወደ መጣበት ባህር ዳር ቢመለስም፣ ሰውየው ላይ የተፈፀመበት ስቅየት እጅግ ከባድና የከፋ እንደነበር ከምንጮቼ አረጋግጫለሁ፤ የህወሓት የሲቪልና ወታደራዊ ከፍተኛ  ባለሥልጣናት  በጓጉንቸር የተቆለፈበት ክፍል ድርስ እየሄዱ በስድብ ከማዋረዳቸውና ከማሸማቀቃቸውም በዘለለ ኤታ-ማዦር ሹሙ ጀነራል ሳሞራ የኑስ “አንተነህ አብዮታችንን የምትቀለብሰው?!”፣ “እናንተ መቼም ልታሸንፉን አትችሉም!”… በሚል ፉከራ የታጀበ የቦክስና የእርግጫ መዓት እጆቹ እግረ -ሙቅ ባጠለቁበት ሁነት እንዳወረደበት ሰምቻለሁ (በነገራችን ላይ ጌታቸው አሰፋም ቢሮ ለምርመራ ያስመጣውን ሰው በእርግጫ የመምታት ልምድ አለው፤ በዚሁ ፍንቀላ ከተሳተፉት መካከል ሻለቃ መኮንን ወርቁ “ፀበሉ” እንደደረሰው እጫውቶኛል። አወይ የስለላ መሪነት¡)
       የሆነው ሆኖ አንዳርጋቸው ፅጌ በነዛ ስቃይ በበዛባቸው የምርምራ ወራት በመንግስታዊ መዋቅር፣ በመከላከያው፣ በደህንነቱ፣ በሲቪሉ… የሰረጉ አባሎችህን ስም ስጠን? ከሚሉ ረብ-የለሽ ንዝንዞች በስተቀር፣ የጠየቁትን በሙሉ በድፍረት ተጋፍጧቸዋል ብዬ አምናለሁ። እነሱ ኢትዮጵያን መቀመቅ ሲከቷት እሱ ለመታደግ እየሞከረ እንደነበረ አስረግጦ ይነግራቸዋል፤ የሕግ-የበላይነት ማስከበር እንደተሳናቸው፣ መሰረታዊ ሕዝባዊ አገልግሎት ማሟላት እንዳዳገታቸው፣ የዜጎችን ደህንነት ከጥቃት እንዳልጠበቁ፣ የገዛ አገራቸውን በጠራራ ፀህይ እንደዘረፉ፣ ሕዝቡን በዘውግ ከፋፍለው ጥላቻ እንደዘሩበት፣ ጠርዝ-የረገጠ ዘረኝነት እንዳቀነቀኑ… ይሞግታቸዋል፤ መንግስታዊ ልፍስፍስነት፣ ስርዓታዊ ክሽፈት፣ ተቋማዊ ውድቀት… በቀፈቀፉት ቅሬታና ቅራኔ በጉርምስና የተመላለሰበትን በረሃ በእርጅናም  እንዲያ ማትር መገደዱን በኩራት ያስረዳቸዋል፤ ኢትዮጵያንም አስፈሪ አደጋ ውስጥ የተነከረች ከርታታ-ሀገር እንዳደረጓት ያስታውሳቸዋል፤ በልበ-ሙሉነቱም አብግኗቸዋል። …ግን እኮ ሁሉም እውነት አይደለምን?!
    እኔም እንዲህ እላለሁ፡- መልካሙ ሰው ሆይ አንተም ከአራት አስርታት በላይ ስለፍትሕ፣ ዕኩልነት፣ ወንድማማችነት… በምደረ-በዳ መጮኽ መሬት የተተከለ ሀቅ ብቻ ሳይሆን  ዕዳም ነው። ከአሬና እስከ ዲሲ፣ ከለንደን እስከ ዱባይ…ብትኳትንም ቅንጣት ድካም እንዳልተሰማህ አውቃለሁ፤ ነፃነቱም፣ ነፃ-አውጪነቱም ገብቶሀልና። ኢትዮጵያንም ከነባሩ የትውልዱውርስ ቀኖና አሻግረ ሁሉን አካታች ለማድረግ  መታተርህም አልመከንም፤ ከኦብነግ እስከ ኦነግ፣ ከቤሕነን እስከ ጋሕነን፣ ከሲአን እስከ አዲኃን ባሉ ጓዶች መታመንን አትርፎልሀልና። በመጨረሻም ከመቃብር በጠበበ ክፍል ውስጥ ቢዘጉብህም አንደ አክሱም ሀውልት ረዝመህ፣ እንደ ጎንደር ግንብ ሰፍተህ ከመታየትም አልፈህ፣ ብረት ያላሰረው ክቡድ-መንፈስህ ከተማዬን ከርቤና ሉባንጃን ባስናቀ ማዓዛ እንዳጠናት ልነግርህ ወደድኩ!!!
(መጋቢት 2007 ዓ.ም ዝዋይ ማጎሪያ)
Filed in: Amharic