>
5:13 pm - Monday April 18, 0698

አዲስ የኦሮሞ ብሄርተኛ አመራሮች ዜጎችን በዘፈቀደ ህገ-ወጥ እያሉ የሚያሰናብቱበት የህግ አግባብ የለም!??!

                                                           የህግ ባለሙያ – መልካሙ ተሾመ
የቀድሞው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ቃል አቀባይ አቶ አዲሱ አረጋ ኪትሳ አማራዎች ከሃያ ዓመት በላይ ይዘውት የኖሩትን መሬት መነጠቃቸውን እና መፈናቀላቸውን ሳይክዱ ይልቁንም አምነው ህገ-ወጦች ስለሆኑ ነው እንጅ አማራ በመሆናቸው አይደለም የሚል መልስ ሰጥተዋል፡፡ በእግረ-መንገዳቸውም የመፈናቀላቸውን ዜና ወደ አደባባይ ያወጡትን ወገኖች ሸንቁጠዋል፡፡ እኛም እንደሚከተለው እንጠይቃለን፡፡
1)ከ 20 ዓመት በላይ በእጆታቸው ስር አድርገው በእውነት እያዘዙበት ይዘውት የሚኖሩት መሬት በየትኛው ህግና ማስረጃ ነው ህገ-ወጥ ይዞታ የሚሆነው? ስልጣን ያለው የመንግስት አካል ህጋዊ ይዞታቸው መሆኑንና እነሱም ራሳቸው ህጋዊ ነዋሪዎች መሆናቸውን አረጋግጦ ህጋዊ የገጠር መሬት ይዞታ ማረጋገጫ ደብተር ሰጥቷቸው እያለ አሁን በዚህ ፍጥነት ህገ-ወጥ መሆናቸው የተረጋገጠው በእንዴት ያለ ምርምራ ነው?
2)የእነዚህ አማራዎች ይዞታ የየራሳቸው ህጋዊ ይዞታ ነው ወይስ በህገ-ወጥ መንገድ የያዙት ነው? የሚለውን ጭብጥ የመወሰን ስልጣ የማን ነው? የኦህዴድ የወረዳ እና ወይም የዞን/ክልል ካድሬዎች ነው ወይስ የመደበኛው ፍ/ቤት ነው?እነዚህ አማራዎች መሬታቸውን የተነጠቁት በፍ/ቤት ውሳኔ መሰረት ነው ወይስ በኦህዴድ ፖለቲካዊ ውሳኔ ነው?
3)አቶ አዲሱ አረጋ በመንግስት ስልጣናቸው የተፈናቀሉት አማራዎች ህገ-ወጦች ናቸው የሚሉን ምን ማስረጃ ኖሯቸው ነው?
4)ግዴለም ህገ-ወጦች ናቸው እንበል፡፡ በህገ-ወጥ መንገድ የያዛችሁት ስለሆነ መሬቱ የግል ይዞታ ነው ቢባል ለባለይዞታየ ነኝ ባዩ፤ የመንግስት ይዞታም ቢሆን ለክልሉ መንግስት እንዲለቅቁና እንዲያስረክቡ በመደበኛው ፍ/ቤት ክስ ቀርቦባቸው ተከራክረው እንዳስፈላጊነቱ እስከ ፌዴሬሽን ም/ቤት ድረስ አቤቱታቸውን/ክርክራቸውን አቅርበው ሲወሰንባቸው ከሚለቅቁ በቀር አዲስ የኦሮሞ ብሄርተኛ አመራሮች በዘፈቀደ ህገ-ወጥ መሆናቸውን እያወጁ የሚያሰናብቱበት ምንም ዓይነት የህግ አግባብ የለም፡፡
ይህን የምለው ህጋዊውን መንገድ ቢከተሉም ውጤቱ ተመሳሳይ መሆኑን በመዘንጋት አይደለም፡፡ ውጤቱ ተመሳሳይ የሚሆነውም እነዚህ አማራዎች ህገ-ወጦች በመሆናቸው አይደለም፡፡ ይህን የምለው የአዲሱ አረጋ መልስ ምንም የሚጨበጥ ቁምነገር የሌለው በአረም ሰበብ ስንዴ የመንቀል የባጀ ፖለቲካ መሆኑን ለመግለጥ ብቻ ነው፡፡ የአማራዎች መፈናቀል ከህግና ከህጋዊነት ጋር የሚያገናኘው ምክንያት የለም፡፡ ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው፡፡ መፍትሄውም፡፡
በነገራችን ላይ ፖለቲካ ሁልጊዜ መልስ አለው፡፡ የመልስ ፖለቲካ ወደየትም አይወስድም፤ባለንበት ነው ሚያስረግጠን፡፡ የሚበጀን መፍትሄ መስጠት ነው፡፡ የእኛ ጥያቄ የመልስ ፖለቲካው ይቅርና የመፍትሄ ፖለቲካ ይተግበር የሚል ነው፡፡ ፖለቲካ ለኦቦ በቀለ ገርባ ፣ ለእስክንድር ነጋ መታሰርም፣ለታየ ደንድአ ወህኒ መውረድም መልስ ነበራት፡፡ እውነቱ፣ ሃቁና ፍትህ ግን እንዲህ ካለው የመልስ ፖለቲካ ቦታ የላቸውም፡፡
* *
የግርጌ ማስታዎሻ፡- አዲሱ ኦህዴድ በጠቅላላ እና የለማ መገርሳ ካቢኔ በተለይ አደገኛ ፖለቲካዊ ውሳኔዎችን ማከታተሉ አይቀርም፡፡ መመሪያው የኦሮሙማ ፖለቲካ ነውና፡፡ አማራው ከማለቃቀስ እና ከልመና ፖለቲካ ወጥቶ መብቱን፣ጥቅሙንና ፍላጎቱን የሚያስከብርለትን ድርጅት ማቆም አለበት፡፡
https://ethiothinkthank.com/2018/05/21/addisu-response-on-amharas-displacement-from-western-showa-zone/
Filed in: Amharic