>

ሁለት ሄክታር (ቃዳ) መሬት ለአንድ የአማራ ገበሬ አዲሱ የወያኔ አማራን የማፈናቀያ ስልት! (አምሳሉ ገ/ኪዳን)

የእነ ለማ መገርሳ አሥተዳደር “ሁለት ሄክታር (ቃዳ) መሬት ለአንድ የአማራ ገበሬ!” የሚል ድንጋጌ ይዞ የአማራ ገበሬዎች ግብር እየከፈሉበት ለዐሥርት ዓመታት እያረሱት የኖሩትን መሬት እየነጠቀ ለኦሮሞ ወጣቶች እየከፋፈለ በመስጠት ሒደት ላይ ይገኛል፡፡
አቶ ሽፈራው ሽጉጤም ተመሳሳይ እርምጃ በአማራ ገበሬዎች ላይ ለመውሰድ ትዕዛዝ እንዳስተላለፈ የሰጠውን ትዕዛዝ ባለፈው ሳምንት በማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ መውጣቱ ይታወሳል፡፡ ወያኔ ሽፈራውን በዐቢይ ሸንጎ ውስጥ ያካተተውስ ለዚህ አይደል? ከልምዱ የተነሣ ትዕዛዙን በሚገባ እንደሚፈጽም ስለታመነበት፡፡
ሽፈራው ሽጉጤ በመለስ ዜናዊ ትዕዛዝ ወደ ሰማንያ ሽህ የሚጠጉ አባዎራዎችን ከጉራፈርዳ “ደን መንጥራቹሀል!” በሚል ሐሰተኛ ምክንያት በግፍ ሲያፈናቅል በወቅቱ በቀጥታ የሬዲዮ (የነጋሪተ ወግ) ስርጭት በሚደረግ የስልክ (የመናግር) ውይይት ላይ “”እነኝህ ወገኖቻችን በየትኛው ፍርድ ቤት ክሳቸው ታይቶ ወንጀሉን መፈጸማቸውም ተረጋግጦና “ቤት ንብረታቸውን ተነጥቀው ይፈናቀሉ ይባረሩ!” ተብሎ ተፈርዶባቸው ነው እርምጃው የተወሰደባቸው??? የጸጥታ ኃይሉም ሆነ ሌሎች የመንግሥት አካላት ያለ ፍርድቤት ትዕዛዝና ውሳኔ በማንአለብኝነት ግፍ የተሞላበት እርምጃ እየወሰደ ነው ወይ የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት አለ የሚባለው???”” ብየ በመናገሬ አገዛዙ ስሕተቱ ታውቆትና ተጠያቂነቱ አሥግቶት ከዚያ በኋላ ያፈናቀሏቸውን ወገኖች ቀበሌውን ፍርድ ቤት፣ የቀበሌ ሠራተኞችን ዳኛ እያደረጉ እራሳቸው ከሳሽ፣ እራሳቸው ምስክር፣ እራሳቸው ዳኛ ሆነው በአንድ ቀን “ችሎት” ገበሬዎችን “ተፈርዶባቹሀል!” እያሉ ሕገወጥ እርምጃቸውን ሕጋዊ በማስመሰል ነበር የማፈናቀል ግፉን የቀጠሉበት፡፡ አሁን ደግሞ ወያኔ የዐቢይ አሥተዳደር በሚባለው የውሸት የለውጥ አሥተዳደር በኩል መልኩን ለወጥ አድርጎ አቶ ለማ እና አቶ ሽፈራው አማራን የማፈናቀል የማሳደዱን ተግባር በአዲስ መልክ እንዲቀጥሉ እያደረገ ይገኛል፡፡
የዚህ አዲሱ የአማራ ገበሬዎችን የማሳደድ የማፈናቀል ተግባር ኢፍትሐዊነትና ሕገወጥነት ምንድን ነው? ብለን የጠየቅን እንደሆነ ኢፍትሐዊነቱ የአማራ ገበሬዎችን ብቻ የሚመለከት በመሆኑ፣ አማራን “ሕገ ወጥ!” ባሉበት መንገድ መሬት የያዙትን ኦሮሞዎች ሌሎች እንዲሁም ከሁለት ሄክታር (ቃዳ) መሬት በላይ ያላቸውን ኦሮሞዎችና ሌሎችን ሁሉም በተመሳሳይ መልኩ ይህ እርምጃ እንዲመለከታቸው ባለመደረጉ ነው፡፡
እስከዛሬ ድረስ ወያኔና የለማ አሥተዳደር እንዲሁም የሽፈራው ሽጉጤ ሌሎችም፤ የአማራ ገበሬ አንድም ከሌላው በተለየ መንገድ መሬት የያዘበት ሁኔታ ሳይኖር “ሕገ ወጥ ሰፋሪ! ወይም ሕገወጥ ይዞታ!” የሚሉት ቃል እንዴት ሆኖ የአማራ ገበሬዎችን ብቻ የሚመለከት ሊሆን እንደቻለ ማብራሪያ ሲሰጡ ታይተው ተሰምተው አያውቁም፡፡
ምክንያቱም የአማራ ገበሬ የኦሮሞ ወይም የሌላ ገበሬ መሬት ከሚይዝበት መንገድ በተለየ መንገድ መሬት የያዘበት ሁኔታ ኖሮ አያውቅምና ነው “በዚህ በዚህ ምክንያት!” ብለው ማብራሪያ ሊሰጡ ያልቻሉት፡፡
ነገር ግን ዓላማቸው የአማራ ገበሬዎችን መድረሻ ማሳጣት ነውና ይሄንን እርምጃ በሚወስዱበት ጊዜ “ለምን?” ተብሎ ቢጠየቅ ምክንያታቸውን ተገቢነት ያለው ለማስመሰል “ሕገ ወጥ ሰፋሪ ወይም ሕገ ወጥ የመሬት ይዞታ!” የሚል ምክንያት አዘጋጅተው የአማራን ገበሬ ከመላ ሀገሪቱ በማሳደድ ላይ ይገኛሉ፡፡
የአማራ ገበሬዎች “ሕገ ወጥ ይዞታ ነው!” የተባሉትን መሬት የያዙበት መንገድ “ሕገ ወጥ ነው!” ከተባለ ሕገወጥ የሚሆኑት የአማራ ገበሬዎች ብቻ ሳይሆኑ የኦሮሞው፣ የትግሬው፣ የደቡቡ የሁሉም ጎሳና ብሔረሰቦች ገበሬዎችም ሕገወጥ ናቸው፡፡
ስለሕጋዊነት ካነሣን እንዲያውም የአማራን ገበሬ የሚያክል ሕጋዊ ገበሬ በዚህች ሀገር የለም፡፡ ብሔራዊ ፓርኮችን (መካነ እንስሳትንና ጥብቅ ደኖችን (ጥብቅ ሲነበብ ብ ትጠብቃለች) ሳይቀር እየወረረና እየመነጠረ መሬት የያዘው የአማራ ገበሬ አይደለም፡፡ ቁጥቋጦና ደን አንድ አይደሉም ይለያያሉ፡፡
አንድም የአማራ ገበሬ ባለበት ሥፍራ ያለበት ቀበሌ አሥተዳደር ሳያውቀው፣ ፈቃድ ሳይሰጠው፣ ይዞታው መሆኑን ሳያውቅለትና ሳይገብርበት የሚያርሰው መሬት የለም፡፡ ለዚህም ማስረጃው ገበሬዎቹ የያዟቸው ሰነዶች ናቸው፡፡
እነ ለማ እነ ሽፈራው ሆይ! እውነቱ ይሄ በሆነበት ሁኔታ የአማራ ገበሬ ዕድሜ ዘመኑን ገንዘቡን፣ ጊዜውን፣ ጉልበቱን ገፍግፎ በመከራ አልምቶ የሚያርሰውን መሬት በምንም መንገድ ይዛዘው በምን ከኦሮሞውና ከሌላው ገበሬ ተለይቶ ሕገ ወጥ የሚሆንበት ምክንያት ምንድን ነው???
ቁልፉ ጥያቄ ይሄ ነው፡፡ እነ ለማ መገርሳ፣ እነ ሽፈራው ሽጉጤና ሌሎቹ የወያኔ ቅጥረኞች ሕገመንግሥታቹህ እንደሚለው “ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ የትኛውም ክፍል የመዘዋወር፣ ኑሮን የመመሥረትና ሀብት የማፍራት መብት አለው!” የሚለውን ድንጋጌ የምታምኑበት፣ የምትቀበሉትም ከሆነና “ሁሉም ዜጋ ዕኩል ነው!” ብላቹህ የምታምኑ ከሆነ የአማራ ገበሬ ከሌላው ብሔረሰብ ገበሬ የተለየ የፈጸመው አንድም ነገር ሳይኖር እንዴት ተነጥሎ ተለይቶ “ሕገ ወጥ!” እየተባለ ሊፈናቀልና መሬቱን ሊነጠቅ እንደሚችል ልታስረዱ ትችላላቹህ???
በተለየ መንገድ መሬት ሳይይዙ የአማራ ገበሬዎችን ሕገወጥ ካላቹህ “ሁሉም የኢትዮጵያ ገበሬዎችም ሕገወጥ ናቸው!” እያላቹህ ነውና መሬት ነጠቃው ሁሉንም የሚመለከት መሆን ይገባዋል፡፡
ካልሆነ ግን የአማራ ገበሬ ብቻ ተጠያቂ የሚሆንበት አንድም አግባብ ሊኖር አይችልምና እባካቹህ ስለጉልበታቹህ አምላክ ብላቹህ የማይመስል ተልካሻ ምክንያት እየጠቀሳቹህ የአማራን ገበሬ ከመመንጠር ከማጽዳት ከማሳደድ ኢሰብአዊና ሕገወጥ ተግባራቹህ ታቀቡ!!!
አማራ ፈጽሞ መድረሻ እንዲያጣ እየተደረገ ነው ያለው፡፡ ከየቦታው ተፈናቅሎ “ክልልህ ነው!” በተባለበት ሥፍራ ሲሔድ እንኳ ሳይቀር ማረፊያ ተሰጥቶት እንዲያርፍና ኑሮውን እንዲመሠርት አልተፈቀደለትም፡፡
የአማራ ጠላት የሆነው ብአዴን እነኝህ በየጊዜው “ወደ ክልላቹህ!” እየተባሉ በግፍ የሚፈናቀሉ የሚሳደዱ የአማራ ገበሬዎችን “ወደ ክልላቹህ ተብላቹህ ከተፈናቀላቹህ፣ ከተሳደዳቹህ እዚህ ክልላቹህ ላይ ላስፍራቹህ!” ሳይልና ጭራሽ እንዲያውም “አላውቅላቹህም!” ብሎ ስንቱን አራሽ አንደፋራሽ ክንደ ብርቱ የአማራ ገበሬን የትም ጎዳና ላይ እየበተነ ለጎዳና ተዳዳሪነትና ለልመና ዳርጎ ዛሬ ግን ጎጃም ቡሬ ላይና ወሎ ከሚሴ ላይ የሶማሌ ክልል ከሚሉት የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን አስፍሮ አሳርፏል፡፡ አማራ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል ማረፊያ እንዲያገኝና ኑሮውን በተረጋጋ ሁኔና እንዲመራ ፈጽሞ አልተፈቀደለትም፡፡
አማራ ሆይ! ያለውን የመረረ እውነታና ተጨባጭ ሁኔታ ጠንቅቀህ ታውቀዋለህ፡፡ ያለው እውነታ ቆርጠህ ጨቅነህ ካልተነሣህና መብትህን እራስህ በጉልበትህ በኃይልህ ካላስከበርክ በስተቀር “መብት አለህ ዜጋ ነህ!” ብሎ መብትህን ሊያከብርልህ የሚችል አንድም እንደሌለ ጥርት አድርጎ ካረጋገጠልህ ዘመናት አልፈዋልና አሁንም እጅግ ብትዘገይም ሻይመሽብህና የተጋረጠብህን አደጋ ፈጽሞ መቀልበስ ወደማትችልበት ሁኔታ ገብተህ ዘርህ ከምድረገጽ ሳይጠፋ ፈጥነህ ተነሥ!!!
ድል ለግፍ ተጋቹ አማራ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
Filed in: Amharic