— ‹‹ያ ነው እኮ የእናንተ ችግር!! እንዴ!? አቅላችሁን ስታችኋል ልበል!?? እንዴት ሆኖ ነው — በጠብመንጃ ተሟሙቶ ያገኘውን ሥልጣን — በእስኪሪፕቶ ልቀማህ ስትለው እሺ የሚለው??!! ጤነኛ ናችሁ ግን??!! ወይስ ህፃን??!! . . . ››
ሰሞኑን — ገዢው ኢህአዴግ — የ27ኛ ዓመት ሥልጣነ-ንግሡን ሊያከብር — ሽር-ጉድ እያለ ነው፡፡ እኔን ይሄ በዓል — ዕረፍትን ከሚለግሰኝ በረከቱ ውጭ — እምብዛም አይመስጠኝም፡፡ ኢህአዴግ መንበረ-ሥልጣኑ ላይ ኖረም አልኖረም ብዙምም ደንታዬ ሆኖም አያውቅም፡፡ እስከማውቀው ድረስ ኢህአዴግ — ከጠብመንጃ ቋንቋ በቀር ሌላ ቋንቋ የማይገባው አምባገነን ነው ያለውን — የደርግ ሥርዓትና የቆመለትን ሠራዊት — በጠብመንጃ አፈሙዝ ገርሥሶ — ሥልጣኑን የተቆናጠጠ ባለጠብመንጃ ኃይል ነው፡፡ ለባለፉት 27 ዓመታት የሥልጣን ቆይታውም — ኢህአዴግ — ለትግል ያነገበውን ጠብመንጃ አውርዷል የሚል እምነት የለኝም፡፡
ኢህአዲግ የቀድሞውን ጦር በጉልበት አሸንፎ ስልጣን ከያዘበት ግንቦት1983 ጀምሮ እሚዋጋው ጠላት አላጣም። መንፈስ ይሁኑ aliens ከማይታወቁ የጠባብ፣የትምክህት፣የደርግ ርዝራዦች፣ኒዬሊበራሊስቶች…ወዘተ እየተዋጋ ነው።
ምናልባት ከዝቅተኝነት እሳቤ (inferior complexity) በመነጨ ይሁን አይሁን እርግጠኛ ባልሆነም እንደ ኢህአዲግ ግን ለራሱ ጠላት እየፈጠረ እድሜውን ሁሉ ጦረኛ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት አላየሁም።
በእኔ አመለካከት — ምናልባት ኢህአዴግ — በትረ-ሥልጣኑን ከመጨበጡ በፊት እና ከጨበጠ በኋላ — የሚለይበት ብቸኛው ነገር — ሥልጣኑን ከመቆጣጠሩ በፊት የደርግን ሠራዊት የሚዋጋ ሠራዊት ነበር — ሥልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ ግን እንደቀድሞው የደርግን ሠራዊት የሚዋጋ ሠራዊት ሣይሆን — የደርግን (‹‹ቀዳም››) ሠራዊት ጨምሮ – መላውን የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚዋጋ ግንባር ነው፡፡ የመንግሥትን ሥልጣን በያዘ እና ባልያዘ ኃይል መካከል ልዩነቱ ያ ነው፡፡ የመንግሥትን ሥልጣን የያዘው ኃይል — የአንድ ቡድን ወይም ወገን ሣይሆን — የመላ ሀገሪቱ ገዢ ይሆናል፡፡ መንግሥት ይሆናል — እንደማለት፡፡
ግን ግን — የሆነው ሆኖ — የኢህአዴግ ሠራዊት — የቀድሞውን ሠራዊት ደምሥሶ — ሥልጣኑን የተቆጣጠረበትን በዓል — ግንቦት 20‘ን — የጠብመንጃ ብቻ ቋንቋ የሚገባውን ኃይል — በዚያው በሚያውቀው የጠብመንጃ ቋንቋ አናግሮ ሥልጣኑን በእጁ ያስገባበት ቀን ነውና — ይህ ቀን — በጠብመንጃ ኃይል የሚተማመኑ የተሸነፉበት — የጠብመንጃን መንገድ የመረጡም ደግሞ ድል የተቀዳጁበት — አሸናፊውም፣ ተሸናፊውም ጠብመንጃ እና ጠብመንጃ የሆነበት — አስገራሚ ቀን ነው፡፡
ኢህአዴግ ይህን በጠብመንጃ ኃይል ሥልጣን ላይ የወጣበትን ዕለት ከሚያከብረው በበለጠ — ወይም ይልቅ — በነፃ ምርጫ ተወዳድሮ — ያለጠብመንጃ ኃይል — በፍፁም የሕዝብ ፍቃድ — በሕዝብ ተመርጦ — የመንግሥትን ሥልጣን የሚረከብበትን ዕለት — ‹‹የኢህአዴግ በዓለ ሲመት›› ብሎ ሰይሞ — ቢያከብረው — እና እኛንም አክብሩት ቢለን — ኖሮ — በዓሉ — በሥራ ለተጠመዱ ኢትዮጵያውያን ብሔራዊ ዕረፍትን ከማጎናፀፍ በተጨማሪ — እውነተኛ የዲሞክራሲ በዓለ-ልደት — እውነተኛ የብዕር-ኃይል በዓለ-ትንሣዔ — የእውነተኛ ጥይት-አልባ ሕይወት ማብሠሪያ ዕለት፣ የአዲስ ሠላማዊ መንግሥት መታሰቢያ — ሆኖ ሊዘከርለት ይችል ነበር — የሚል የፀና እምነት አለኝ፡፡
በበኩሌ — ቅድም እንዳልኩት — ኢህአዴግ ለ1 ቀን በገዢነቱ ቀጠለ — ወይም ለ1 ዓመት — አሊያም ለ100 ወይም ለ1 ሺህ ዓመት — ያ ለእኔ — በበኩሌ — ጉዳዬ አይደለም፡፡ ሆኖም አያውቅም፡፡ ዋናው የእኔ ጉዳይ — ሥልጣኑን የጨበጠው ማን ሆነ ወይም አልሆነ አይደለም፡፡ ዋናው እና ብቸኛው ጉዳዬ — ያን ሥልጣን የጨበጠው አካል — ሥልጣኑን የጨበጠው በምን ዓይነት መንገድ፣ እና በምን ዓይነት የምርጫ አስፈጻሚ ተቋማት አማካይነት ነው?? የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ነው ብቸኛው መሥፈርቴ፡፡ ይህን መሥፈርት በትክክል አሟልቶ እስከመጣ ድረስ — ለእኔ — ኢህአዴግም ሥልጣኑን ይጨብጥ፣ ወይም ኦነግ፣ ወይም ኦብነግ፣ ወይም ትሃት፣ ወይም ህወሃት፣ ወይም ብአዴን፣ ወይም መአህድ — በእኔ ሚዛን — ማናቸውም — ማን መሆናቸው ወይም ያለመሆናቸው — ለውጥ የለውም — የሥልጣን አያያዛቸው — ነፃ፣ ገለልተኛና ፍፁም ፍትሐዊ ዳኝነትን በሚሰጡ — የምርጫ አወዳዳሪዎችና ቆጣሪዎች ፊት — በነፃ ተወዳድሮ — በነፃ የሕዝብ ፈቃድና ምርጫ — ሥልጣን ላይ እስከወጡ ድረስ!!!!!! The means justifies the means! And that’s all!
በሌላ አነጋገር —ዋናው የሥልጣን ቅቡልነት መሥፈርቱ — ሥልጣንን የተቆናጠጠው ኃይል — ሥልጣን ላይ የወጣው — አሊያም ሥልጣን ላይ የቆየው — ፍፁም ነፃና ገለልተኛ፣ እና ከማናቸውም አድልዎና ተፅዕኖ ነፃ መሆኑ በተረጋገጠለት — በአስተማማኝና ታማኝ የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም አማካይነት ነው??? — ወይስ — ‹‹ነፃ›› የሚለውን ቅብ እንዲቀባ — በሎሌነቱ ፅናት መሥፈርትነት ተመልምለው በተውጣጡ — በሎሌነት ለባለ ጠብመንጃው ባደሩ፣ አድሎአዊ በሆኑ፣ ኢ-ነፃ፣ ኢ-ገለልተኛና ኢ-ፍትሃዊ — የምርጫ አስፈፃሚ ተቋማት አማካይነት — በተሰጠ ግምድል ፍርድ አማካይነት ነው??? — የሚለው ነው — ከምንም በላይ ሥልጣን መንበር ላይ የተቀመጠውን ፓርቲ፣ ወይም ማናቸውም ኃይል — ይገባዋል ብዬ የማጨበጭብለት — አሊያም አይመለከተኝም፣ አያገባኝም፣ ለምን ገደል አይገባም? ብዬ የምጎማዘዝበት — ብቸኛው መለኪያዬ — ብቸኛው መሥፈርቴ!!!
ይመስለኛል — ባለፈው ሰሞን — ከ2ኛው ዙር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቀደም ብሎ — በኢ ኤን ኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ በቀጥታ ተላልፎ በነበረው የተለያዩ ምሁራንና ፖለቲከኞች ጉባዔ ላይ — ዶ/ር መረራ ጉዲና — በመድረክ ላይ ወደነበሩት ወደ እነ አቶ በረከት ስምዖን እያየ የሰጠው አስተያየት — ባልሣሣት — ይህ ምሁርና ፖለቲከኛ — ይህንኑ ያነሣሁትን የሥልጣን ቅቡልነት መሥፈርት — ለባለፉት 27 ዓመታት በሥልጣኑ ላይ የሠነበተው ኢህአዴግ — ስለማሟላቱና ያለማሟላቱ በተመለከተ — በወቅቱ የደረሰበትን ድምዳሜ ያሳያል፡፡ እንዲህ ነበር ያለው፡- ‹‹እስቲ ልብ ካለው — ኢህአዴግ — ምርጫ ቦርድን እና ጠብመንጃውን ያውርድና — በባዶ እጁ ተወዳድሮ — የኢትዮጵያ ሕዝብ ከመረጠው — እኔ በግሌ — ለመቶ ዓመት ኢትዮጵያን እንዲገዛ እፈርምለታለሁ! — ይኸው በሰው ፊት ነው ቃል የምገባው — ኢህአዴግ ያለምርጫ ቦርድና ያለጠብመንጃ በምርጫ ተወዳድሮ ካሸነፈ — ይኸው ለመቶ ዓመት እንዲገዛኝ በአስር ጣቴ እፈርማለሁ!›› ነበር ያለው ይህ በግልጽና በፊት ለፊት ያሰበውን የሚናገር አንጋፋ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሁር፣ ተፎካካሪ ፖለቲከኛና ታሣሪ-ተፈቺ ያገር-ሰው፡፡
እንግዲህ ከላይ በመነሻዬ ላይ — በእኔ አስተያየት — ይህ የግንቦት 20 ቀን — መታሰቢያነቱ — ያሁኑ ገዢ ግንባር ኢህአዴግ — የዛሬ 27 ዓመት — የጠብመንጃ ቋንቋ ብቻ የሚገባውን ወታደራዊ ኃይል — በዚያው በሚያውቀው የጠብመንጃና የጠብመንጃ ቋንቋ አናግሮ — ሥልጣኑን በመቀማት — የመንግሥትነት መንበረ ሥልጣኑን በጠብመንጃ ኃይል በእጁ ያስገባበት ቀን ነው፡፡ ግን ከዚያ በኋላ በተከተሉት 27 ዓመታት እና አሁንስ??? እውን እዚህች ሃገር — ኢትዮጵያ ውስጥ — ሥልጣን የያዘውን ባለጠብመንጃ ግንባር — ያለ ጠብመንጃ፣ ያለ ደምና አጥንት — በእስኪሪብቶና ወረቀት፣ በሃሳብና በሙግት፣ በነፃ ውድድርና ምርጫ — ከወጣበት ሥልጣኑ ማውረድ — የሚቻል ነው ወይ? እውን ይህ የብዕርና የቃል-የሃሳብ ነፃ የፖለቲካ ሥልጣን አያያዝ መንገድ — በእኛ ሃገር ላይ — እውን ክፍት ነው ወይ?? — ወይስ በከፍተኛ ተጋድሎና መሥዋዕትነት — በጠብመንጃ ቋንቋ እና በደም እና በአጥንት ሥልጣን የተቆናጠጠውን ኢህአዴግን — ከሥልጣን ማውረድ የሚቻለው — በዚያው ባወረደበት እና በወጣበት በዚያው ዓይነት አሠቃቂ መንገድ ብቻ ነው ወይ?? ይህ ይመስለኛል — በአሁን ወቅት — በመላው ኢትዮጵያውያን — በግንቦት 20 ዕለት — በአስተማማኝ ሁኔታ — ምላሽ ሊያገኝ የሚገባው — ዋነኛ ጥያቄ፡፡
ለዚህ ዋነኛ የጊዜያችን ጥያቄ የምንሰጠው መልስ — አዎ! ይቻላል! ላለፉት 27 ዓመታት ሥልጣኑን የሙጥኝ ያለውን ኢህአዴግን — በብዕር እና በክርክር እና በፉክክር ብቻ — ከሥልጣን ማውረድም — በሥልጣኑ ማቆየትም — ይቻላል፡፡ በሃገራችን — ብቸኛው የሥልጣን አያያዝም ሆነ አወራረድ መንገድም — ይሄና ይሄ ብቻ ነው — ሆኗል — ወደፊትም ይሆናል — የሚል ምላሽ የሚሰጡ — ተስፋን ያነገቡ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት — እንግዲህ — አማራጫቸው — በዚሁ ቀና አስተሳሰብ ተጉዞ — የመጨረሻውን ቀና ውጤት መጠበቅ ይመስላል ያላቸው አማራጭ፡፡ ምናልባት — ያ እስኪሆን ድረስ — ምን ያህል ግንቦት 20ዎችን እናሣልፍ ይሆን?? — በበኩሌ አላውቅም፡፡ መገመትም አልችልም፡፡ አንድ ነገር ግን መናገር እፈልጋለሁ፡፡
ኢህአዴግም ሆነ ማንኛውም የፖለቲካ ኃይል ሥልጣን ላይ እንዲወጣ የአወዳዳሪነትና የዳኝነት ቁልፍ ሚናን የሚጫወተው — የኢትዮጵያ የምርጫ ተቋም — ፍፁም ገለልተኛ ነው ብዬም ግን አላምንም፡፡ ያለማመን መብቴ ነው፡፡ የሃሳብ ነጻነት የሚባለው — ማመን ወይም ያለማመን ነው አይደል?? እና እኔም በእኔ ልክ እስኪያሳምነኝ ድረስ የማላምነውን አላምንም፡፡ ስለሆነም — ያ ታላቅ የዲሞክራሲ አካል — የምርጫ አስፈጻሚ ተቋም — ፍፁም ገለልተኛ እና ፍጹም ታማኝ — እንዲሆንም ነው ትልቁና ዋናው ጥረቴ፣ ግቤና ምኞቴ፡፡ ታማኝ ስል — ተግባሩን በታማኝነት የሚወጣ እና በሁሉም ዘንድም የሚታመን ሊሆን ሲችል ማለቴ ነው፡፡
በእኔ አስተያየት — ዋናው የኢትዮጵያ ዲሞክራሲ ጥያቄና መልሱ ያለው — ሥልጣን ላይ ማን ወጣ ወይም አልወጣ የሚለው ነጥብ ላይ አይደለም፡፡ ጥያቄውና ትግሉ ከኢህአዴግም ጋር አይደለም፡፡ ከሌላ ከማንምም ጋር አይደለም፡፡ ዋናው ትግል፣ እና ዋናው ጥያቄ፣ እና ዋናው ዓላማ — በሥልጣን ላይ ለመውጣት የሕዝብን ድምፅ ያገኘውንና ያላገኘውን ተወዳዳሪ ማንነት የሚወስነውን የምርጫ ተቋም — ፍፁም ጤናማ፣ ፍፁም ገለልተኛ፣ ፍፁም ፍትሃዊ፣ ፍፁም ሚዛናዊ፣ ፍፁም ታማኝ፣ እና ፍፁም የተከበረ ማድረጉ ነው — ዋናው ግብ፣ ዋናው ዓላማ፣ ዋናውና ትልቁ ዘመንን የሚሻገረው ትልቁ የኢትዮጵያውያን የቤት ሥራ፡፡
ያ ከሆነ — ያ ጥያቄ በአስተማማኝነት ከተመለሰ — በኢትዮጵያችን — ወላ ኢህአዴግም ይሁን ጎግድሂቤግ — ወይም ጉምፃብዴግ — ወይም የፈለገው ዓይነት ፓርቲ ይምጣ — ከዚያ በኋላ — እገሌ ለምን ሥልጣን ላይ ወጣ? ለምን ሰነበተ? ለምን በደነ? ለምን ወረደ? — የሚሉ ጥያቄዎች በፍፁም አይነሱም፡፡ ሊነሱም አይችሉም፡፡ ምክንያቱም የምርጫው አስፈጻሚ አካል — ፍፁም ነፃና ገለልተኛ ስለሚሆን — በእርሱ በኩል ካለፈ — ትራምፕም መጣ ኦባማ ወይም አብይ — በእሺታ ትቀበለዋለህና፡፡
እና ያ እውነተኛ የዲሞክራሲ ተቋም ባልዋለበት — ግንቦት 20 በዓል ማክበር — የጠብመንጃን ኃይል በጠብመንጃ ኃይል መደምሰሱን ከመዘከር ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም ባይ ነኝ — በበኩሌ፡፡ ወይም — ይህ የግንቦት 20 በዓል — ሙሉ ይሆን የነበረው — ስላልሆነ — በሃገራችን የሥልጣን አያያዝና የምርጫ ዳኝነት — ሁሉም በሚያምንበት ፍፁም ገለልተኛ ተቋም እጅ ቢገባ ነበር — የሚል ፅኑ አቋምና እምነት አለኝ፡፡
ይህን ሁሉ ካልኩ በኋላ — አንዲትን ገጠመኜን ሰንዝሬ ሃሳቤን ልቋጭ፡፡ በቀደም‘ለታ — ከአንድ የማከብረው ጓደኛዬ ጋር — በዚሁ በፈረደበት የግንቦት 20 ቀን መነሻነት በተጀመረች ቀላል እንቶ-ፈንቶ ተነስተን — ሞቅ ወዳለ ክርክር ተሸጋገርን፡፡ እና በአንዳንዶቻችን ‹‹ፕሮ-ኢህአዴግ›› ወይም ‹‹ቱ-ኦፕቲሚስቲክ›› ሃሳብ እርር ያለው ያ ጓደኛዬ በንዴት ጦፎ — በስንብቱ ላይ እንዲህ ብሎ ተለየን፡-
‹‹እናንተ እኮ ችግራችሁ ምን መሠላችሁ?? — በጠብመንጃ ኃይል ተጋድሎ፣ የስንት ሺህ ሰው ሕይወት ገብሮ፣
በስንት ሞትና ሽረት፣ ተሟሙቶ የያዘውን ሥልጣን —ኢህአዴግ — እንዲያው ተፎካካሪ ሃሳብን ብቻ ፈርቶ —
አፍና ቃልን ብቻ አክብሮ — በእስኪሪብቶ ኃይል ብቻ — ጨምድዶ ከያዘው ሥልጣን ሊወርድ ይችላል በሚል
— ከንቱ ቅዠት ውስጥ መገኘታችሁ እኮ ነው!! ያ ነው እኮ የእናንተ ችግር!! እንዴ!? አቅላችሁን ስታችኋል ልበል!??
እንዴት ሆኖ ነው — በጠብመንጃ ተሟሙቶ ያገኘውን ሥልጣን — በእስኪሪፕቶ ልቀማህ ስትለው እሺ የሚለው??!!
ጤነኛ ናችሁ ግን??!! ወይስ ህፃን??!! ኢህአዴግ እኮ የካሴት ክር አይደለም በእስኪሪፕቶ አሽከርክረህ የምትገለብጠው!
እንደካሴት በእስኪሪፕቶ ልትገለብጠው ስትሄድ፣ ኢህአዴግ የሚጠብቅህ ‹‹ሲዲ›› ሆኖ እንደሆነ ሃቁን እመኑ፡፡ እንዲያውም
በቃ ኢህአዴግ ‹‹ሲዲ›› ነው!!›› ብሎን — የጀመረውን ድራፍት ባንድ ትንፋሽ ጨልጦት ተነሣ፡፡
ቀጠለና ደሞ፡— ‹‹እንዲያውም ሒሳቤንም አልከፍልም! ራሳችሁ ክፈሉ! ወይም ሲዲ‘ው ኢህአዴግ ይክፈልላችሁ! መልካም ግንቦት 20!!!›› ብሎን እንደጦፈ ጥሎን በረረ!! በሠላም ቤቱ እንዲገባ መርቄው ባለሁበት ቀረሁ፡፡ ነገር እያውጠነጠንኩ፡፡ . . . . ‹‹ግን ግን … ይሄ ኢህአዴግ የሚሉት ግን… እውን ካሴት ይሆን.. ወይስ ሲዲ..??›› እያልኩ፡፡ በዝምታ ተውጬ፡፡ ራሴን እየጠየቅኩ፡፡
በበኩሌ — ፀቤ ከኢህአዴግ ጋር አይደለም፡፡ ማንም ይሁን ብያለሁ፡፡ ብቸኛው ትኩረቴ ነፃ የምርጫ ተቋም መኖሩ እና ያለመኖሩ ላይ ነው፡፡ ያ ደግሞ ይፍጠንም ይዘግይ — መሆኑ አይቀርም፡፡ ዳግመኛ መረን-ጠብመንጃዎች ክቡሩን የወገን ህይወት መቅጠፍ ሣያስፈልጋቸው — ያ እንደሚሆን — በፍፁም ልቤ አምናለሁ፡፡ እመኛለሁ፡፡ በተስፋም ይሆን በቀቢፀ-ተስፋ — ብቻ ግን — ያ እንደሚሆን — አምናለሁ፡፡ በበኩሌ — የማትሪክ ፈተናን፣ የሚኒስትሪን ፈተና አልፈው — እና ውጤቱንም በፀጋ ተቀብለው — ካለፉ የኢትዮጵያ ትውልዶች አንዱ ነኝ፡፡ ሚኒስትሪና ማትሪክን በዚያ መልኩ ለተከታታይ ትውልዶች በያመቱ ስታርምና ሃቀኛ ውጤት ስትሰጥ የኖረች ሃገር — በአራትና አምስት ዓመት አንዴ የሚመጣን — ብሔራዊ የምርጫ ካርድ በሃቅ ቆጥራ — ሃቀኛ ውጤት መስጠት ይሣናታል የሚል ሽራፊም ጥርጣሬ የለኝም፡፡ በቅርቡ ያ ካልሆነ — ወይም ያ እንዳይሆን የሚፈልግ የኢትዮጵያ ህዝብ ካለ — ወደፊት ምን እንደምንሆን ካሁኑ መገመት ወይ መተንበይ አልችልም፡፡
ሃቅ እንዳይሰፍን፣ አንድ ተቋም ሃቀኝነቱ የሚረጋገጥበት መንገድ እንዳይበዛ፣ ሃቀኝነቱ በሽፍንፍኑ እንዲቀር የሚፈልግ ዜጋ፣ ወይም ፓርቲ፣ ወይም ባለሥልጣን፣ ወይም ሰው — በዚህች ሃገር፣ በዚህ ዘመን፣ በመካከላችን ቢገኝ፣ እና ዓይኑን አፍጥጦ ያን ላስቀጥል ወይም ልተግብረው ቢል — ምን እንደሚከተል — ወይም ምን እንደምንል — በበኩሌ ማወቅም፣ መገመትም ይቸግረኛል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አረማዊ — ከዚህች ምድር ይንቀልልን ብዬ ከመመኘት በቀርም የምለው የለኝም፡፡ እንዲህ ዓይነት ፍላጎት ያላቸው ሰዎች በዚህች ሃገር እንደማይበዙ፣ እንደሚመናመኑ፣ እና እንደሚተንኑም ድብን አድርጌ አምናለሁ፡፡ እና ሥልጣን በእስኪሪፕቶ ኃይል መጨበጥ እንደሚቻል በዓይኔ በብረቱ እስካይ ድረስ አምላኬን በሀገሬ እንዲያቆየኝ እለምነዋለሁ፡፡ እኔም ባልሆን ልጄ፣ የልጅ ልጄ እንደሚያየው አልጠራጠርም፡፡
የምጠራጠራት ግን አንዲት ቀጭን ጥርጣሬ ብቻ አለችኝ፡፡ ያቺም ነገር . . . ይሄ ኢህአዴግ የሚሉት ግን — ያ በንዴት የጨሰ ጓደኛዬ እንዳለው — እውነት ግን . . . የምር — ኢህአዴግ ሆዬ . . . እውነት ‹‹ሲዲ›› ይሆን እንዴ?? — የምትል — ከክር የቀጠነች ብቸኛ ጥርጣሬ!!!
መልካም ዓውደ-ምህረትን ተመኘሁ! አምላክ ኢትዮጵያንና መፃዔ ትውልዶቿን እንዲባርክ ጭምር! እምዬ ኢትዮጵያችን — በእውነት — በተስፋ — በፍቅር — በፅናት — ለዘለዓለም ትኑር፡፡