>

''የሚያርፈው አጽማቸው ሳይሆን ህሊናችን ነው'' (ዮሐንስ  መኮንን)

በአንድ ወቅት መቀሌ የሚገኘውን ”ሐውልቲ” በመባል የሚታወቀውን እና የህወኃትን የ17 ዓመታት ”ገድል” የሚያስቃኘውን ቤተ መዘክር ለመጎብኘት ዕድሉ ገጥሞኛል፡፡ ጉብኝታችንን ስናጠቃልል ምድር ቤት በሚገኝ አንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ 11 የእሬሳ ሳጥኖች የሕወኃትን ”ሰንደቅ” ለብሰው ተደርድረዋል፡፡ አስጎብኚያችን ምንነታቸውን ስጠይቀው ”በትጥቅ ትግሉ ወቅት የተሰው ታጋዮችን ለማሰብ የተሰበሰበ አጽም ነው” ብሎን ነበር፡፡ በእርግጥ ለምን ቁጥራቸው 11 እንደተደረገ አልነገረንም፡፡ ምናልባት ፓርቲው የተመሠረተበትን የካቲት 11 ለማሰብ ይሆናል፡፡
ዓላማው ለምንም ይሁን ለምን የወደቁ ጓደኞቻቸውን አጽም በክብር ሰብስበው ያሳረፉት የቀድሞ ታጋዮች እህል ውሃ ሲያንከራትታቸው በአረመኔዎች እጅ ወድቀው እንደበግ የታረዱ ወገኖቻቸውን አስከሬን አንስተው በሀገራቸው ለመቅበር ዳተኞች መሆናቸው አሳዝኖን ነበር፡፡ እንኳንስ አስከሬናቸውን በክብር አንስቶ ለመቅበር በወቅቱ ለለቅሶ የወጡ ወጣቶችን ለመበተን ፖሊሶች ቆመጥ ይዘው መሠማራታቸውንም አንዘነጋም፡፡ ግብጻውያን ግን ከእኛዎቹ ነጂዎች (በዐብይ አገላለጽ) ቀድመው አስከሬናችንን በክብር አሳርፈውልናልና በዚህ ተግባራቸው አመስግነናቸዋል፡፡
አሁን ደግሞ እድሜ ሰጥቶን፣ ዘመን ገጥሞልን ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ሰሞኑን ”ግብጽ ወርጄ በግፍ የታረዱ ኢትዮጵያውያንን አጽም አፍልሼ በሀገራቸው በክብር አሳርፈዋለሁ” ማለታቸውን ሰምተናል፡፡ በዘመነ ኢህአዴግ ቋሚዎች በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር ሆነው በሚንከራተቱባት የመከራ ምድር በባእዳን ምድር የወደቁ አጽመ ቅዱሳንን የሚሠበሰብ መሪ ሲነሳ እድል ገጥሞን፣ ከዘመኑ ደርሰን ማየታችንን እንደመታደል እንቆጥረዋለን፡፡ በዚህ ለመደሰት ሃይማኖተኛ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ ይበቃል፡፡
ምክንያት ፈልጎ ከማመስገን ይልቅ ሰበብ ፈልጎ ለመውቀስ የሚመርጡ አንዳንዶች ”እየዞረ አጽም ከመልቀም እዚህ በአሁኑ ሰአት እየተበደሉ ያሉትን ነጻ ያውጣ” ማለታቸውን አንብበናል፡፡ ቢያድለን ኖሮ እኮ ይህ ሥራ ”ማተባችን ከሚበጠስ አንገታችን ይበጠስ” ብለው መራራውን ሞት የታገሱላትን ቤተክርስቲያን ”የሚመሩ” የሃይማኖት አባቶች እና የወገኖቻቸው ኢትዮጵያውያን መሆን ነበረበት፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ይኽንን በጎ ሥራ በማሰባቸው ብቻ ቤተክርስቲያኒቱ በአደባባይ ልታመሠግናቸው እና አስፈላጊውን ሃይማኖታዊ ሥርዓተ ፍልሰት በብሔራዊ ደረጃ ለማከናወን ልትዘጋጅ ይገባል፡፡ ጉዳዩን በሊቃውንት አስመርምራ የሚገባቸውን ማእረግ ለመስጠትም ጊዜው አሁን ነው፡፡ በወገኖቻችን መከራ በጥልቅ ሀዘን በወደቅንበት ወቅት ሊቁ ጌትነት እንየው በግጥሙ እንደወቀሰን በሊቢያ በረሃ ስለ እግዚአብሔር ደማቸውን ያፈሰሱ ክርስቲያኖችን የገፋናቸው ”እኛው” ነበርን፡፡ አዲሲቷን ኢትዮጵያ በደማቸው ያስተሳሠሩት ሰማእታት ”ሲኖሩ ተንከራታች ሲያልፉ ግብጻውያን” ለምን ይሆናሉ? ሀገራቸው ለኑሮ ባትመቻቸውም ለአጽማቸው ማረፊያ ልትነፍጋቸው አይገባም፡፡ ኢትዮጵያዊ ሆነው የሀገራቸውን በረከቷን ለማየት ባይታደሉ ቢያንስ ከአፈሯ ተቀላቅለው ”ኢትዮጵያ” ይሁኑ፡፡ ይህንን በማድረጋችን የሚያርፈው የሰማእታቱ  አጽማቸው ሳይሆን ህሊናችንም ጭምር ነው፡፡
Filed in: Amharic