>
5:30 pm - Thursday November 1, 3506

‹ጨዋታ ሥጋዊ ወ መንፈሣዊ› . . . ! ! (አሰፋ ሀይሉ)

አንድ በዓለም የታወቀ መንፈሣዊ ሰባኪ ስለ ራሱ እና ስለ መንፈሣዊ አገልግሎቱ ያለውን ከፍ ያለ መተማመን እንዲህ እያለ ሲናገር ነበር፡፡ ይህ ሰባኪ በአንድ ወቅት ወደ አፍሪካይቱ ሃገር ጋቦን ሄጄ – የንጉሡን የኦማር ቦንጎን የመጀመሪያ ወንድ ልጅ (እና አልጋ ወራሽ) በቤተመንግሥቱ ሄጄ – የክርስትና ዕምነትን እንዲቀበል ልሰብከው በዝግጅት ላይ እገኛለሁ፤ ይህንንም የማደርገው በራዕይ ይህን  እንዳደርግ እግዚአብሔር ተገልጾልኝ ስላዘዘኝ ነው – በማለት ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጠ፡፡
እንግዲህ እኚያ ኦማር ቦንጎ ማለት (የዛሬ 9 ዓመት ሞተዋል!) ኦማር ቦንጎ በአፍሪካችን – ለ44 ዓመታት በመንበረ ሥልጣናቸው ላይ ከቆዩት ከራሳችን ግርማዊ ጃንሆይ (ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) በመቀጠል – ለረዥም ዘመን በሥልጣን ላይ በመቆየት በ2ኛ ደረጃ የሚገኙና ለ42 ዓመታት ጋቦንን በመሪነት ያስተዳደሩ የታወቁ አምባገነን ነበሩ፡፡ ኦማር ቦንጎ ቀድሞ የክርስትና ሐይማኖትን ይከተሉ የነበረ ቢሆንም – በሊቢያው የቀድሞ መሪ በሞአመር አል ጋዳፊ ተሰብከው – (እና አንዳንዶች እንደሚያሟቸው ደሞ – መዓት ፔትሮ ዶላር ከብራዘር ጋዳፊ ተዘርግፎላቸው!) – ሐይማኖታቸውን ወደ እስልምና የቀየሩ፣ ስማቸውን ደግሞ ‹‹አልበርት በርናርድ ቦንጎ›› ከሚለው ወደ ‹‹ኤል-ሃጅ ኦማር ቦንጎ›› በመቀየር የሚታወቁ – ደፋርና አነጋጋሪ ፈላጭ ቆራጭ አፍሪካዊ ንጉሥ ነበሩ፡፡ በዚያው የሥልጣን አልጋቸው ላይም እያሉ ነው ሞት የቀደማቸው፡፡
እና እንግዲህ ያ ሰባኪ ወደ አፍሪካ ሄጄ – ወደ ክርስትና ሐይማኖቱ እንዲመለስ ልሰብከው አስቤያለሁ ያለው – እርሱን የአባቱን እግር ተከትሎ ሐይማኖቱን ወደ እስልምና የለወጠውን – የንጉሡን የኦማር ቦንጎን ልጅ – ወይም አልጋወራሽ ልዑል ነው፡፡ ታዲያ በጊዜው በህይወት የነበሩት ኦማር ቦንጎ – የዚያን ሰባኪ መግለጫ ከዓለም የመገናኛ ብዙሃን ሲሰሙ – ምንም መልስ ከመስጠት ተቆጥበው ነበር፡፡ ምንም መግለጫምም አልሰጡም፡፡ ዝም ነው ያሉት፡፡
ያን ሰባኪ ግን ብዙዎች አስፈራሩት፡፡ ተው አትዳፈር፡፡ ወደ ጋቦን እሄዳለሁ ብለህም እግርህን አታንሣ፡፡ እኚያ ንጉሣን ቤተሰቦች እኮ በዓለም ከልካይ የሌላቸው – ያሻቸውን ሊያደርጉ የሚቻላቸው – የታላቅ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው፡፡ ደግሞም እኮ የአንድ ሀገር ንጉሥ፣ የአንድ ሉዓላዊት ሃገር አልጋ ወራሽ ናቸው እኮ – ያን እንደ ቀላል አትውሰደው፡፡ ሊያጠፉህ፣ ወይም ወህኒ ሊወረውሩህ፣ ወይም ደብዛህን ሊያጠፉትም ይችላሉና – ተው በእሣት መጫወት ይቅርብህ –  እንዲህ ዓይነቱ አጉል ቅብጠት አይበጅህም – ተወው!  ብለው ብዙዎች መከሩት፡፡ ዘከሩት፡፡ እርሱ ግን በጄ አላለም፡፡ በመጨረሻ ሄደ፡፡
እነ ኦማር ቦንጎስ ምን አደረጉ? ወይም አደረጉት?? – እነርሱማ – ምንም አላደረጉትም፡፡ ጭራሽ ድፍን ዓለምን ይግረማችሁ ሲሉ – እንዲያውም ሰባኪውን – በቤተመንግሥታቸው ማረፊያ ሰጥተው – በክብር አስተናግደው – የሚገባውን እንክብካቤ ሳያጓድሉ – ከቤተሰባቸው ጋር አቆይተው – የመጣበትን ስብከቱንም አዳምጠው – ነገር ግን እነርሱ በእስልምና ሐይማኖታቸው ፀንተው ለመቆየት የወሰኑ መሆናቸውን በትህትና አስረድተው – ወደመጣበት ሀገሩ – ወደ ጀርመን – በሠላም ሸኙት፡፡
ያ ሰባኪ ወደመጣበት ሀገሩ ሲመለስ – ታላቅ አቀባበል ነበር የጠበቀው፡፡ ሞትን ያህል ነገር ንቆ – የእግዚአብሔርን ቃል ሊመሰክር – ወደ አፍሪካ የሄደውን ተዓምረኛ ሰባኪ ለማየትና – ቃሉን ለመቀበል፣ ስለእርሱ ትኩስ ዜና ለመዘገብ ያሰፈሰፉ – እና የእርሱን ወደሃገሩ መመለስ ነቅተው የሚጠባበቁ – የአፍሪካውን ደርሶ መልስ ጉድ ሊሰሙ – ጆሮአቸውን አስፍተው የሚጠባበቁ ጋዜጠኞች ነበሩ -በኤርፖርቱ ካሜራና መቅረፀ-ድምፅ ወድረው – ሰባኪውን የጠበቁት፡፡ እና ግን የሁሉም ጥያቄ አንድና አንድ ነበር፡፡ ‹‹ለመሆኑ ግን አንተ – እንዴት ብለህ ንጉሥን ያህል ነገር፣ እንዴትስ ብለህ የንጉሥን ልጅ ያህል ነገር፣ እንዴትስ ብለህ እንደዚያ ያለ ትልቅ ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች፣ እንዴት ልትደፍር ቻልክ?? ምን ያህልስ ብትተማን ነው ግን… ህይወትህን አደጋ ላይ ጥለህ… በቤተመንግሥታቸው ሄደህ ለመስበክ ድፍረቱን ያገኘኸው??›› የሚል፡፡ እርሱም የሰጠው መልስ ቁርጥ ያለ ነበር፡፡ እንዲህ ነበር ያላቸው፡-
‹‹አዎ ልክ ናችሁ፡፡ ኦማር ቦንጎ የአንድ ሃገር ንጉሥ ናቸው፤ ልጃቸውም የአንድ ሀገር ልዑል አልጋ-ወራሽ ነው፡፡ በሀገራቸው ግዛት ውስጥ በተገኘ ሰው ላይ ሁሉ ሥልጣናቸውም ከልካይ የለውም፤ ልክ ናችሁ፡፡ ነገር ግን የረሣችሁት ደግሞ አንድ ነገር አለ፡፡ እኔም ደግሞ – የዓለም ሁሉ ንጉሥ፣ የህዋው፣ የምድሩ፣ የሠማዩ ሁሉ ንጉሥ የሆነውን የእግዚአብሔር አምላክን መልዕክት ይዤ የተጓዝኩ – የንጉሥ ቆንሲል – የንጉሥ አምባሳደር – የኃያላን ሁሉ ኃያል የሆነው አምላክ በፍቅሩ ልጁ ያደረገኝ – የዓለም ሁሉ ገዢ የሆነ የታላቁ ንጉሥ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ እኔም፤ እኔም ከሥልጣናት ሁሉ በላይ የሆነ – የዓለም ሁሉ ሥልጣናት በፊቱ ሲቀርቡ ችለው ሊቆሙ የማይቻላቸው – የዓለምን ሁሉ ኃያል በሥልጣኑ የሚያብረከርክ – በሰማይ በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን ያለው  – የሠማዩ አምላኬ ልጅ ነኝ እኔም – እኔም የሁሉን ቻዩን ንጉሥ የፈጣሪ አምላኬን መልዕክት ይዤ የሄድኩ – የታላቅ ንጉሥ አምባሳደር ነኝ! እና እኔስ ከንጉሥ ኤል ሃጅ ኦማር ቦንጎ ልጅ – በምን አንሳለሁ?? . . . ያን እውነት ነው እናንተም የዘነጋችሁትና የተገረማችሁት!!! . . . ያን ሳስብ ነው እኔም በንጉሣን ቤት ተገኝቼ ለንጉሡ ልጅ ስለ ኃያሉ አምላኬ ለመስበክ ድፍረቱን ያገኘሁት!! ንጉሣኑም አላሳፈሩኝም፤ ያመንኩት ኃያል ንጉሥ እግዚአብሔርም በመንገዴ ሁሉ ከእኔ ጋር ነበረ፤ አላሣፈረኝምና ክብር ምስጋና ለእርሱ ለፈጣሪ አምላክ ይሁን!!!››
/አ ሜ ን ! !  አ ሜ ን ! ! ዋዋዋው….. ዋውውው!! ኦ….ው!!!! እንዴት ውስጤን አበራው ይሄ ሰባኪ??!!!! እንዴት ያለስ ታላቅ መንፈሳዊ መሰጠት ነው አቦ??/
እውነት ነው፡፡ አይታበልም፡፡ ይሄ ዓይነቱ ታላቅ መንፈሣዊ ልዕልና በውስጥህ ሲያድርብህ – ምድራውያን ንጉሣን ለመንፈሳዊው ጌታ ይሰግዱለት ዘንድ ትመራቸዋለህ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ልዕልና ሲርቅህስ?? – የዚያ ዓይነቱ ሰባኪ መንፈሳዊ ወኔ፣ መንፈሳዊ መሰጠት፣ መንፈሳዊ ማንነት ሲርቅህማ – አንተ የአምላክ መንፈሳዊ አባት ሆነህ ሳለ – አንተ የምታበራው መንፈሳዊ መልዕክትና ታላቅ ኃይል – ምድራውያን ጌቶች አጎንብሰው ሊቀበሉት የሚገባቸው ሆኖ ሳለ – አንተ ግን – የራስህን የኃያላን ሁሉ ኃያል ንጉሥ ረስተህ – ለምድራውያን ንጉሣን ትሰግድ ዘንድ ትጻፋለህ፡፡ በእርግጥ – ያቺም – መንፈሳዊ ትህትና ልትሰኝ ትችል ይሆናል፡፡
እኔ ግን የምረዳው – አምላኬ ይቅር ይበለኝና – ስጋውያን ለመንፈሱ መስገድ ሲገባቸው – መንፈሱ ለሥጋውያን የሚሰግደው – አንተ – የንጉሣን ሁሉ ንጉሥ መሆንህን የመዘንጋት አሳዛኝ ግፋፌ-ፀጋ ሲደርስብህ – እና የራስህን የነገሥታት ንጉሥ ረስተህ – ለምድራውያን ንጉሠ-ነገሥት እንድትሰግድ የጣፈህ ዕለትህ ነው – ማለት ነው – ብዬ ነው የምረዳው!!! የአምላክ በረከትና መንፈሳዊ ልዕልና – በእግዚአብሔር አገልጋዮች ላይ ይገለጥባቸው ዘንድ – በምስኪን ኮልታፋ አንደበቴ የወጣችውን ኢምንት ፀሎት ወደ አምላኬ አደረስኩ!!!
የኃያላን ሁሉ ኃያል ለሆነው – የነገሥታት ሁሉ ንጉሥ – የምድር-የሠማይ ፈጣሪ ለሆነው – አልፋና ኦሜጋው ፈጣሪ አምላካችን – ክብር ሁሉ ከዘለዓለም እስከዘለዓለም ይሁንለት፡፡ የምህረት አምላክ – የኢትዮጵያን እና የኢትዮጵያውያንን አንገት – በምህረቱ፣ በክብር፣ በልዕልና፣ በአይበገሬነት ቀና ያደርግልን ዘንድ -መንፈሣውያን አባቶቻችንንም – እንደ ሰማዕቱ አባት – እንደነ አቡነ ጴጥሮስ – በማይናወጥ ዕምነትና ልዕልና – በፅናት ጠባቂያችን አድርጎ ያቆምልን ዘንድ – ከልብ ተመኘሁ፡፡ አምላክ ሃገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ አበቃሁ፡፡
Filed in: Amharic