>

ለታላቋ ትግራይ አላማ ሲሉ ራስ መንገሻ ስዩም  በአርማጭሆ በወልቃይት በጠገዴ አርበኞች ላይ የፈጸሙት ክህደትና ወንጀል!?! (ጥሩነህ ይርጋ)

ስጋውን ላይበሉት ደሙን ላይጠጡት፥
ቢትወደድ አዳነን ለምን ገደሉት?
የወልቃይት ጥያቄ የተነሳው ገና የኢትዮጵያ ግዛት ተደላድሎ፥ ደጃዝማች አዳነ መኮነን በአውራጃ ገዥነት ዋና ከተማቸውን ዳባት ላይ አድርገው፥
ወልቃይት ጠገዴን ከሰሜን ወገራ እስከ ሰቲት ሁመራ ኤርትራ ምላሽ በሚያስተዳድሩበት ዘመን በ60 ዎቹ መጀመሪያ ላይ ነበር።
ጥያቄው ለንጉሱ የቀረበው በዘዴ ነበር፥ በደጃዝማች አዳነ ቂም ያዘሉ ጥቂት የወልቃይት የባንዳ ልጆችን አስተባብረው በትግሬው ልዑል ራስ መንገሻ እንደነበር የቅርብ አዋቂዎች ይናገራሉ።
የወልቃይት ቂመኞች ምክንያትም ሌላ ሳይሆን በጠላት ወረራ ዘመን ከጥሊያን ጋር ወግነው በተሰለፉ የጠላት አሽከሮችና በጀግናው አርበኛ ቢትወደድ አዳነ መኮነን ጦር በተደረገ መራራ ውጊያ ላይ አባቶቻቸው የተገደሉ፣ የባንዳ ልጆች ቂም ይዘውባቸው ስለነበር፥ ቢትወደድ አዳነ ሊገዙን አይገባም በሚል የመጠቃት ሀፍረት መሆኑ ይነገራል።
ራስ መንገሻ ስዩም ግን እሄን የቂመኞች አጋጣሚ ለንጉሱ ያላቸውን ቅርበት በመጠቀም ትግራይ በለም መሬት እጦት ስለተቸገረ ወልቃይት ጠገዴ ለትግራይ በግዛትነት ይሰጠን በሚል ጮሌነት ነበር ጥያቄውን ያቀረቡት፥
ሆኖም ንጉሰ ነገስቱ ኮስተር ብለው፥ ከልጃችን ከአዳነ ግዛት ስንዝር መሬት ልንሰጥህ አንችልምና ሁለተኛ እንዳታነሳብኝ የሚል ቅልብጭ ያለ ምላሽ ነበር የተሰጣቸው።
ስለዚህ ዋናው ምክንያት ምንድነው፥ እንዴት ጀምረው የት ሊጨርሱት ነው ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፥
የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም አማራ ሕዝብ ሊያውቀው የሚገባ ትልቅ ጉዳይ አለ፥
ይሄውም በአማራ መቃብር ላይ ታላቋን ትግራይ የመገንባት የትግሬ የመስፋፋት ዓላማ ነው።
ወያኔ የተባለው የትግራይ ወራሪ ኃይል የጎንደርንና የጎጃምን መሬት ቆርሶ ቤኔሻንጉል ጉሙዝ የሚባል ግዛት ፈጥሮ፥ የአማራን መሬት ከሁመራ እስከ ኦሜድላ ጠቅልሎ፥  ትግራይን እስከ ጋምቤላ ጫፍ ለጥጦ፥ ታላቋን ትግራይ የመፍጠር ቅዠት ነው። የህዳሴው ግድብም የዚሁ ወረራ አንዱ አካል ነው።
ይህ ለብዙዎች ቀልድ ይመስላል፥ ነገሩ ግን እውነት ነው፥ ዛሬ ዘርፈ ሰፊው አማራን የማጥፋት ዘመቻ በሁሉም ጠርዝ የሚታይ ሆኗል፥ ላለፉት ዓመታት ይህ ጉዳይ አይመለከተንም ብለው በጎሪጥ ሲያዩት የነበሩ ሁሉ፥ ዳሩ ሲፈርስ ማህሉ ዳር ይሆናልና ቀስ ብሎ ችግሩ መሃል እየገባ በመሄዱ መጻፍና መናገር ጀምረዋል።
በተለይ ለእኛ በጉዳዩ የቅርብ ተጠቂ ለሆነው፥ መጀመሪያ አባቶቻችን፥ በመቀጠል ታላላቅ ወንድሞቻችን፣ እየቆየ ታናናሽ ወንድሞቻችንና፥ የእህት የወንድም ልጅ ያለ ማቋረጥ በመገበር ላይ ያለነው፥
የአርማጭሆ የወልቃይት የጠገዴ ልጆች፥ በአጠቃላይ የሰሜን ጎንደር ተወላጅ አማራዎች ላለፉት 28 ዓመታት የሚስጥር ጦርነት ታውጆብን እየታገልን ያለንበት፥ እየሞትንና እየተሰደድን በእየቀኑ የምናለቅስበት ይህ የዘር ማጥፋት ዘመቻ የውስጥ ህመማችን ነው።
አጀማመሩ እንደዚህ ነው።
አብዮቱን ተከትሎ በደርግ መንግስት ላይ ያመጸ፥ በልዑል ራስ መንገሻ ስዩም እና በጀኔራል ነጋ ተገኘ የሚመራ ኢድዩ የሚባል ድርጅት ነበር። መንገሻ ስዩም ከትግሬ፣ ነጋ ተገኘ ከጎንደር፥ ሁለቱም የጃንሆይ አማቾች ናቸው።
በአብዛኛው የኢዲዩ ጦር ከጎንደር ሲሆን ጥቂት የትግራይና ኦሮሞዎችም ነበሩበት፥ በውጭ ያለው አመራርም እንደዚሁ የብሄር ስብጥር ያለው ነበር።
ኢዲዩ ከሰቲት ሁመራ፣ ከአብደረፊ፣ ከመተማ ጀምሮ ብዙ የአርማጭሆ የወልቃይት ጠገዴ ጀግኖች የታገሉበትና መስዋዕትነት የከፈሉበትና በመጀመሪያ የትግል ዘመኑ ጥሩ ተንቀሳቅሶ ወዲያው በተቀነባበረ አሻጥር የከሰመ ድርጅት ነው።
ክቡር ቢትወደድ አዳነ መኮነን ከወልቃይት ጠገዴ እስከ አጅሬ ጃኖራ ወገራን ይዞ፥ ሻለቃ አጣነው ዋሴ ከመተማ ቋራ እስከ አለፋ ጣቁሳ ጭልጋን ይዞ፥ ሻለቃ ዋክሽም ነወጠ ታች አርማጭሆን ይዞ መሃሉን፥ ሻለቃ ዘውዱ አልጣህና ሻለቃ አስራደ በየነ ላይ አርማጭሆ በጦር አዝማችነት በጀግንነት የመሩት፥ እነ ሻለቃ በሪሁን ገብረየስ፣ አዳነ ተገን፣ ጠሃይ ጥሩነህ፣ አድማሱ በላይ የሚባሉ የአርማጭሆና የጋይንት ሃያል የጦር መሪዎች ከሰሜን እስከ ደቡብ ጎንደር፥ ከፍተኛ ተጋድሎ ያደረጉበት ድርጅት ነው።
ከዚያ ሁሉ በኋላ ግን ኢዲዩ ቀስ በቀስ ብዙዎችን አግልሎ፥ በትግራዩ ልዑል መንገሻ ስዩምና በልጃቸው በስዩም መንገሻ እጅ ብቻ የሚዘወር ከዚህ ግባ የማይባል የትግራይ ተዋጊዎች ማገገሚያ፥ ኢዲዩ የሚለውን ስም ብቻ ይዞ የቀረና የታላቋን ትግራይ ጉዳይ ለማስፈጸም የቆመ ነበር፥
በራስ መንገሻ ስዩም ሚመራው ኢዲዩ በእነ በረከት ስምዖን ከሚመራው ኢህአፓ ቀጥሎ ወያኔ በሚስጥር የሰራበት የትግሬ ድርጅት መሆኑን በ1981 ዓ.ም ከአርማጭሆ በርሃ ተልከው ወደ ሱዳን የመጡ 2 ዘመዶቼን ይዤ ካርቱም ዴም ክፍለ ከተማ የነበረውን የኢድዩ ጽህፈት ቤት በጎበኘሁበት ጊዜ በዓይኔ ዓይቼ መታዘቤን በዚህ አጋጣሚ መግለጽ እፈልጋለሁ።
ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ከነልጃቸው ከህወሃት ጋር በምስጢር በመገናኘት ብዙ የኢድዩን ጀግኖች አስጠፍተዋል።
ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም ወልቃይት ጠገዴ ወደ ትግራይ እንዲካለል የአንበሳውን ድርሻ ወስደዋል፥ ወደፊትም ታች አርማጭሆን እስከ መተማ እና ቋራ በዘዴ ጠቅልለው ታላቋን ትግራይ ለመፍጠር የሚያስችለውን ስራ እረቂቅ በሆነ መንገድ እንዳከናወኑ የሚያስረዳ ብዙ ዱካዎች አሏቸው።
ህወሃት ወልቃይት ጠገዴን ወደ ትግራይ ለማካለል ያስቸግሩኛል ያላቸውን ኢህአፓ እና ኢዲዩ ጦርነት እንዲገጥሙና የለቱም ጦር እንዲበተን በስውር አሲረው ካስገደሏቸው ክቡር ቢትወደድ አዳነ መኮነን እና ወንድሞቻቸው ጀምሮ፥ ኢድዩ ውስጥ የነበሩ የወልቃይት ጠገዴና የአርማጭሆ ጀግኖችን እስከ 1982 ዓ. ም ድረስ በትግሬው ልዑል ራስ መንገሻ ስዩም አማካኝነት በረቀቀ ዘዴ አጥፍታለች።
ከዚህ እውነት ተነስተን ነው፥ የወያኔ ትግራይ ነፃ-አውጭ ግንባር በአማራ ህዝብ ላይ የጥፋት ዘመቻ ያወጀው ዛሬ አይደለም፥ ጊዜ እየጠበቀ እንጂ ከላይ ጀምሮ ነው ቆይቷል የምንለው።
የሚታዩት ፎቶዎች ሻለቃ ጌታቸው ፤  ሻለቃ መከታው አዛናው እና ልጅ አበጀ ፈለቀ ይባሉ፥
ልዑል መንገሻ ስዩም ከወያኔ ጋር ተመሳጥረው ካጠፏቸው የጎንደር አማራዎች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው፥
በትግራይ ነጻ-አውጭ ግንባር ወያኔ በ1982 ዓ.ም ከሱዳን ታፍነው፥ የት እንደገቡ ሳይታወቅ ደብዛቸው የጠፋ፥ የሰሜን ጎንደር አማራ ተወላጆች የአርማጭሆ፣ የወልቃይት ጠገዴ አርበኞች ናቸው።
ከዚህ ላይ ያልተጠቀሱትን ስም ዝርዝራቸውን የሚያውቁ እንደሚጨምሩልኝ አምናለሁ።
ሻለቃ ጌታቸው ይርጋ
ሻለቃ መከታው አዛናው
ሻለቃ አስራደ በየነ
ልጅ አበጀ ፈለቀ
አቶ ሃጐስ ጌታሁን
አቶ እምሩ ገብረህይወት
አቶ ፈንታ ገብያው
አቶ በሬ ከበደ
ዶክተር አሰፌ ዋሴ
እያለ እሰከ ጀግናው ሻለቃ አጣናው ዋሴ ድረስ፥ ወደ 19 የሚሆኑ አርበኞች በዓንድ ሰሞን ታፍነው እንደ ጠፉ ይታወቃል። ሻለቃ ጌታቸው ይርጋ,,, ከሴቲት ሁመራ ሀብታም ገበሬዎች አንዱ ነበር።  ሻለቃው በፈረስ ስሙ ”አባ ጣለው“ የታወቀ ጀግና ነበር።
ሁለተኛው ሻለቃ መከታው አዛናው,,,,, የአርማጭሆ ወልቃይት ጠገዴ አርበኛ የአርበኛ ልጅ የኢዲዩ መስራች ነው፥ በፈረስ ስሙ “አባ ድፈን” መከታው አዛናው የአርማጭሆ ጀግና፥ በአብደራፊ ፣ መተማ፣ በቋራ በርሃና፥ በሰሜን ተራራዎች የተፈተነ ሃይለኛ የጦር ሰው ነበር።
ሶስተኛው በግፍ የተገደለ ሻለቃ አስራደ በየነ ይባላል አጎቴ ነው። መጀመሪያ ሱዳን ጠረፍ አብደራፊ በትራክተር የሚያርስ ሃብታምና ጀግና ገበሬ ሲሆን፥ የኢድዩ መስራችና የጦር መሪ የታወቀ ጀግና አርበኛ ነበር።
ልጅ አበጀ ፈለቀ፥ በንጉሰ ነገስቱ እና በደርግ መንግስት በጎንደር የገቢዎች ባለስልጣን እና የመተማ ወረዳ አስተዳደሪነት ጨምሮ በልዩ ልዩ የአስተዳደር ዘርፍ አገሩን ያገለገለ የመንግስት ሰራተኛና የኢዲዩ መስራችና ጀግና አርበኛ ነበር፥
እዚህ ላይ በትንሹ ለማንሳት ያክል እንጂ የእያንዳንዳቸው የጀግንነት ታሪክ ቢወራ አያልቅም።
ወልቃይት ጠገዴ አርማጭሆ የጀግና አገር ነው። ጠላቶቻችንም ያውቁታል፤ እኛም አስረግጠን እንነግራቸዋለን።
እንሂድ ካላችሁ እንሂድ ተነሱ፥
ሁመራ ቅርብ ነው ዳንሻ ከደረሱ፦ ይላል ያገሬ ገበሬ፥
ልዑል ራስ ስዩም መንገሻ ያመናቸውን የወልቃይት ጠገዴ ህዝብና ጀግና የትግል አጋሮቹን ክዷል። የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲካሄድበት ከወያኔ ጋር ተባብሯል። ህዝቡን ለ27 ዓመታት የህወሃት የግፍ ሰለባ አድርጎታል።
መልሽው መከታው፥ የመከታው አዛናው ልጅ ናት።
የጀግናው አርበኛ ልጅ ፍትህ ያስፈልገኛል ትላለች።
አባቷ መከታው አዛናው እና ጌታቸው ይርጋ በ1982 ዓ/ም ሱዳን አምራኩባ ከተባለው የስደተኞች ሰፈር አካባቢ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ እንዳሉ በሱዳን ፖሊሶች  “ለጥያቄ ትፈለጋላችሁ” ተብለው በቀን ዶካ ወደሚባለው እስር ቤት ከተወሰዱ በኋላ ደብዛቸው ጠፍቷል። ልዑል ራስ መንገሻ ያስጠፏቸው ሰዎች በቁጥር ብዙ ናቸው፣ ለ27 ዓመታት አሉ፣ ወይም ሞቱ የሚታወቅ ነገር የለም። ለቤተሰቦቻቸው እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል፣ ልባቸው አላረፈም።
እኛም እንደ ህዝብ፣ እንደ አማራ ወገን፥ እነዚህ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የአርማጭሆ አማራዎች ምን ሆነው ይሆን ብለን ልንጠይቅና የፍትህ ያለህ ብለን ልንጮህ ይገባል።
በሚቻልበት መንገንድ ሁሉ ዘመቻ ልናደርግና ጫና መፍጥር ለሚችሉ የተለያዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ልናሳውቅ ግድ ይለናል።
በህይወት ካሉ ያሉበትን ያሳውቁን፥ በህይወት ከሌሉ ደግሞ እንዴትና መቼ እንደሞቱ አውቀን ወንጀለኛውን ለፍርድ ማቅረብ እንዲቻል ማን እንደገደላቸው ሊያሳውቁን ይገባል።
መልሽው መከታው የተወለደችው አባቷን ህወሃቶች ካጠፉት በኋላ ነው።
እናቷ መልሺው ያለቻትም አባቷን እንድትመልሰው ነው።
መልሺው በምትኖርበት አገር ለሚገኝ ለአንድ የመብት ተሟጋች ድርጅት የአባቷንና የሌሎቹን ጉዳይ እንዲያጣሩላት በደብዳቤ አሳውቃ ነበር። ድርጅቱም በግዜው ኢትዮጵያ ባሉት የመብት ተሟጋቾች በኩል የተወሰነ መንገድ ተጉዞ “በዚህ ጉዳይ ከዚህ በላይ መሄድ አልቻልንም ” በማለት ብዙ ሊገፉበት አልቻሉም። የኢትዮጵያ መንግስት ጫና ስላደረገባቸው መሆኑ ነው።
ህወሃት የነዚህ ጀግኖች ጉዳይ እንዲነሳበት አይፈልግም፣ የት ገቡ ብለው የጠየቁ ሰዎች ተገድለዋል፣ ጠፍተዋል፣ ታስረዋል፣ በጉድጓድ ውስጥ እንደታሰሩ ሞተው በዛው ተቀብረው ቀርተዋል።
ዛሬም የአርማጭሆ የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ በወያኔ መገደል፣ መፈናቀልና መሰደድ አላቆመም፥ በሰላም ሰርቶ የሚኖረውን ገበሬ ከቤቱ እያስወጡ ጫካ አስገብተው እንደ ዱር አውሬ ማደኛ ያወጡባቸዋል፥ አባቶች ይገደላሉ ልጆች ይሰደዳሉ። ሚስቶች ያለባል ይቀራሉ፣ እናት የሙት ልጇን ለማሳደግ ስትጣጣር ሳትወድ በግድ የሰፋሪ ትግሬ መውለጃ ትሆናለች፥ በአማራ ላይ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ማለት እሄው ነው።
Filed in: Amharic