>

ኦሮሞ ነኝ!! ኢትዮጵያዊ ነኝ!! አሸባሪ ግን አይደለሁም!! (ገመቹ መራራ ፋና)

ይኼንን የምፅፈው በብዙ ነገሮች ስለተረበሽኩ ነው፤ ጎኔን ከፍራሼ በጊዜ ባዋድድም እንቅልፍ ሊወስደኝ ስላልቻለ ከተጋደምኩበት ተነስቼ ነው። በየቀኑ የምሰማው እና የማየው ነገር እነ1984ን እና Hunger Gamesን አይነት ፊልሞች የምመለከት እንጂ የምር እየኖርኩት ያለሁት ነገር እየመሰለኝ አይደለም። መጪው ጊዜ ብሩህ አይደለም!!! ጭለማ እና አስፈሪ ሆኖብኛል።
* * *
ይሄ ሌሎች ሰዎች ላይ የደረሰ ሳይሆን በኔው በራሴው ላይ የደረሰና የኖርኩት ገጠመኝ ነው፦
አምቦ፣ ሕዳር 1998 ዓ/ም። 
ከትምህርት ቤት ሲወጡ እዚያው ትምህርት ቤት በር ላይ ስለተገደሉት የ10ኛ ክፍል ተማሪዎች አላወራላችሁም። በሰላማዊ መንገድ ያለምንም ሁከት ተቃውሟቸውን ያሰሙ ልጆች ላይ ፊት ለፊት ጥይት ስለሚተኩሱ «ሰላም አስከባሪዎች»ም አልተርክም። አዎ የተገደሉት ከተገደሉ በኋላ በአንድ ዝም ባለ ቀን የተደረገ ነገር ነው።
በዚህ ዕለት አሁን በሕይወት የሌሉ አያቴን እያስታመምኩ ለማደር ከሰፈር ወጥቼ አያቴ ወደተኙበት ወደ አምቦ ሆስፒታል እያመራሁ ነበር። ወደዋናው የአስፓልት መንገድ ልደርስ አንድ ቅያስ ሲቀረኝ በስፍራው የነበሩት ሁለት ፌዴራል ፖሊሶች ጠሩኝ። ምርጫ አልነበረኝም፤ እየቀፈፈኝ ወደቆሙበት ጥግ ሄድኩ።
«መታወቂያ!» ሲል ጮኸብኝ አንደኛው ፌዴራል ፖሊስ ዱላውን እያሽከረከረ። አረንጓዴዋን የቀበሌ መታወቂያዬን ከኋላ ኪሴ አውጥቼ ሰጠሁት። ያሽከረክረው የነበረውን ዱላውን ትከሻዬ ላይ አሳረፈው። «ማን ይሄን ጠየቀህ?! የኦነግ መታወቂያህን አውጣ!» ሲል ጮኸብኝ።
«ኧረ የለኝም…» ንግግሬን አልጨረስኩም። የሁለተኛው ፖሊስ ዱላ አረፈብኝ። የተለያዩ መልስ የማይፈልጉ ጥያቄዎች እየጠየቁ በእግራቸው ተቀባበሉኝ። ሲበቃቸው «ሂድ ከዚህ ጥፋ፣ እናንተ ናችሁ ያስቸገራችሁት..» አሉኝ። ተነስቶ ለመሄድ የሚያስችል አቅም ግን አልነበረኝም፤ ይሄም ለሌላ ዱላ ዳረገኝ። እንደምንም ታክሲ ይዤ ሆስፒታል ደረስኩና አደርኩ። ያንን ድብደባ የማልረሳበት ሌላም ምክንያት አለኝ።
* * *
ይሄ መንገድ እየሄድኩ ሳለሁ የገጠመኝ ነገር ነው። ለተቃውሞ ድምፁን ያሰማ ሰው ደግሞ ምን ሊደርስበት ነው? መገመት ነው። ኦሮሞ ስለሆንኩ፣ ጥያቄ ስለጠየቅኩ፣ አንገቴን ቀና አድርጌ ስለሄድኩ «ኦነግ» የሚል ታፔላ በማንም እንዲሰጠኝ አልፈልግም!!! ሰው ነኝ!!! ኢትዮጵያዊ ነኝ!!! ኦሮሞ ነኝ!!! አሸባሪ ግን አይደለሁም!!! አባቶቼ ለዚህች አገር እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ደምተዋል። ቅድም አያቴ ትግራይ ድረስ ሄደው ዘምተው የሃገራቸውን ዳር ድንበር ሲያስከብሩ ተሰውተዋል። ከማንም ያልበለጥኩ፣ ከማንም ያላነስኩ የዚህች አገር ዜጋ ነኝ።
* * *
ይሄንን እና ሌሎችም ነገሮችን በጭንቅላቴ እንደሰነግኩ ነው እንግዲህ ወደ መቐለ ዩኒቨርሲቲ ለትምህርት የሄድኩት። እዚያ እንደደረስኩም ብዙ ሳንቆይ ነበር የብሔር ግጭት የተነሳው። በኋላ ላይ ሲጣራ አንዲት ልጅ አፍቅሮ ራሱን ባጠፋ አንድ የአዳማ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ምክንያት ነበር «እኛም አንድ ኦሮሞ መግደል አለብን» ተብሎ በጠራራ ፀሃይ የተዘመተብን። እኚህ ጥቂት የተማሩ ደደቦች የፈፀሙት ድብደባና ሌሎች አስፀያፊ ድርጊቶች የትግራይን ወይም የመቐለን ሕዝብ ይገልፁት ነበር? በፍጹም!!!
ለአራት አመታት የኖርኩበት ይህ የትግራይ ሕዝብ ከተማሪው ሸሽቶ ከዩኒቨርሲቲው ጊቢ በመውጣት በደመነፍስ ወደ ሃይማኖት ተቋማት እና ሌሎች ስፍራዎች የሸሸውን የሌላ ክልል ተማሪ ምግብና መጠለያ ሰጥቶ ክፉ ቀኑን ያሳለፈለት ደግ ሕዝብ ነው!! ታምሜ ለሳምንት በተኛሁበት አጋጣሚ በአካል እንኳን ሳታውቀኝ መታመሜን ስትሰማ «ወይኔ ልጄን» ብላ በልጇ ምግብና ማር የላከችልኝን እናት ያገኘሁበት ሕዝብ ነው!! ምንም የማያውቀኝን እኔን ተቀብሎ ቤቴ ያለው እንዲመስለኝ አድርጎ የተንከባከበኝ፣ ከአባቴ ያላነሰ ገንዘብና ሞራል እየሰጠ ለአራት አመታት ከአጠገቤ ያልተለየ አባት ያገኘሁበት ሕዝብ ነው!! የዚህን ሕዝብ ደግነት በጥቂቶች ድድብና በዜሮ ላባዛው? የተወሰኑ ፖለቲከኞች አሊያም «አክቲቪስቶች» ድርጊትና ንግግር ይሄንን እውነት ይሰውርብኝ? ፈጽሞ!!!!
አዎ እንዲህ አይነት የደግነት ታሪኮች በሌሎች አካባቢዎችም ብትሄዱ በብዙ ትሰማላችሁ። በተቸገረ ሰው ጨክኖ «ብሔሩ ምንድነው?» የሚል ሕዝብ የትም ቦታ የለም። ስለኖርኩብትና ስላሳደገኝ ስለደጉ የኦሮሞ ሕዝብ ሌላ ጨምሬ የምናገረው ነገር የለኝም። በተለያዩ ጊዜያትና አጋጣሚዎች በበቂ ሁኔታ ተነግሯል። በቅርቡ፣ በጣም በቅርቡ ግን በረባውም ባልረባውም በዘር መከፋፈል ነው የማየው። የሃይማኖት ጉዳይ ሆኖበት «የክርስቲያን/የሙስሊም ስጋ አልበላም» ይል የነበረው ማህበረሰባችን «የኦሮሞ/አማራ/ትግሬ ስጋ አልበላም» የሚልበት ጊዜ የመጣ እስኪመስል ድረስ ልዩነት በባትሪ ይፈለጋል። እርስ በርስ የሚያባላን የከፋ ችግር የለብንም። እንደሌላው ዓለም የዘር (race) ችግር የለብንም፤ ሁላችንም ጥቁር ነን። ተመሳሳይ ኑሮ የምንኖር፣ የመግባቢያ ችግር የሌለብን፣ ለዘመናት ስንጋባና ስንዋለድ የኖርን ሕዝቦች ነን። አንዱ «ብሔር» ከአንዱ «ብሔር» በከፋ ሁኔታ፣ አንዱ ሃይማኖት ከሌላኛዎቹ ሃይማኖቶች በተለየ ሁኔታ በተለያዩ ሥርዓቶች የተገፋበትን ሁኔታ አይተናል። አዎ ሥርዓቶች፣ መንግስታት/ገዢዎች ያልፋሉ፣ በሌላም ይተካሉ፤ ይህ ያለና የነበረ የተፈጥሮ ሥርዓት ነው። ሕዝቦች ግን አያልፉም።
ብሔር አጣርተው አይደለም ወላጆቻችን ለጎረቤታቸው ችግር ሲደርሱ እና ሲደረስላቸው የኖሩት። ብሔር ተጠያይቀን አይደለም እዚህ የደረስነው። ብሔር ቆጥረን አይደለም ምርጥ ጓደኞቻችንን ያፈራነው። ሰውነታችንን አስቀድመን ነው!!! ዛሬ በማወቅም ባለማወቅ የሚደረጉ የብሔር የርስ በርስ ግጭት ውስጥ መግባት የለብንም። ያ እንደ ብሔርም ሆነ እንደ ሃገር የማንወጣው አዘቅት ውስጥ ነው የሚከተን። አሁን ያለንበትንም ይሁን ያለፍንበትን ልዩነት በእጅጉ የሚያስመኝ ክፉ አዘቅት ውስጥ ተዋጠልንም አልተዋጠልን ተዋልደናል። ተዋደናል። ተዛምደናል። ተጋምደናል። የተሻለችዋን ነገኣችንን ልንፈልግና ልናገኝ የምንችለው አንዲት የሁሉንም ሰው መብት እና ሰብዓዊ ክብር በምትጠብቅ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ነው። ከታሪክ ልንማር ይገባል ምናምን አልልም። አይናችንን አንስተን ደቡብ ሱዳንን ማየት በቂአችን ነው። ከሱዳን እስክትገነጠል ድረስ ፅኑና የሚገርም ትግል ለዓመታት አድርጋለች። ከተገነጠለች በኋላ ግን የሆነችውን ሆናለች። የኛም የተናጠል ጉዞ መድረሻው ያው ነው። አማራ ቢገነጠል ጎጃም፣ ጎንደር፣ ወሎ፣ ሸዋ እያለ ይናከሳል። ኦሮሚያ ብትገነጠል ሸዋ፣ ሐረርጌ፣ ወለጋ፣ አርሲ እያለ ይባላል። ትግራይ ቢገነጠል ተምቤን፣ እንደርታ፣ ዓድዋ፣ ሽሬ እያለ ይጫረሳል። «ታግሎ» ሲያበቃ «ነፃ» ባወጣት «ሃገር» የሚፈጠረው ቀውስ የዳር ተመልካች መሳቂያ ያደርገዋል።
***
አይን የሌለው ኢፍትሃዊነትን በሚተገብር እና ግፍ በሚፈፅመው አካል ሳይሆን ዳር ሆኖ ያንን ድርጊት በሚደግፈው ሰው ልቤ ትደማለች። ከክቡሩ የሰው ልጅ ሕይወት ይልቅ በተራ የንብረት መውደም የሚብሰከሰከውን ብኩን ሳይ ነፍሴ ክፉኛ ታዝናለች። ልጁን በሞት ካጣ ወላጅ ሃዘን ይልቅ ወደፊት ምናልባት ኪሴ ሊገባ ይችላል ብሎ ለሚያስበው ሽራፊ ሳንቲም በሚቆረቆር «ሰው» ንቀቴ ይበረታል። ትናንት እርሱ ላይ ሲጫን የነበረውን የበደል ቀንበር ዛሬ ባለቀን ሆኖ ሌላው ላይ አክብዶ በሚጭነው ላይ ጥላቻዬ ይከራል። አንድ ሕሊና ያለው ሰው እንዴት በባዶ እጅ በወጣ ሰልፈኛ ላይ ቀጥታ የተተኮሰን ጥይት ደግፎ ሊናገር ይችላል? አንድ ችግር የኛን ቤት እስኪያንኳኳ ድረስ የባለቤቱን ያህል ላይሰማን ይችላል፣ ነገር ግን እንዴት በተቃራኒ ያስቆማል? አላውቅም። የዚህ አይነት አስተሳሰብ አይገባኝም።
* * *
Rabindranath Tagore «Gitanjali» በተሰኘው መድብሉ ውስጥ በጣም የምወድለት እንዲህ የምትል የልመና/የፀሎት ግጥም አለችው፦
Where the mind is without fear and
the head is held high;
Where knowledge is free;
Where the world has not been broken
up into fragments by narrow domestic walls;
Where words come out from the depth of truth;
Where tireless striving stretches its arms towards perfection;
Where the clear stream of reason has not
lost its way into the dreary desert of
dead habit;
Where the mind is led forward by Thee
into ever-widening thought and action—
Into that heaven of freedom, my Father,
let my country awake.
አሜን!!
* * *
ኦሮሞ ነኝ!! አሸባሪ አይደለሁም!! 
#OromoProtests
#StopKillingCivillians
#StopKillingUnarmedProtesters
Filed in: Amharic