መቶ አለቃ ማስረሻን አየር ኃይል ግቢ ውስጥ ቀርቶ እስር ቤት ውስጥም አያምኑትም፣ ይፈሩታል፣ ይጠሉታል። በዚህም ምክንያት ከአብዛኛው እስረኛ ነጥለው ጨለማ ቤት አከረሙት። በቂሊንጦ ቃጠሎ ወቅት ጨለማ ቤት ውስጥ ነበር። ጨለማ ቤት ውስጥም ሆሞ ግን ግንቦት 7፣ ኦነግ፣ አልሻባብን ታደራጅ ነበር አሉት። መቶ አለቃ ኢህአዴግ ዶላር ለመሰብሰብ የሚያደራጀውን አልሸባብን ሲያደራጅ አስቡት!
በቃጠሎው ሰበብ ሸዋሮቢት ወስደው አሰቃዩት። ጣራ ላይ አንጠለጠሉት። ገመዱን በድንገት ቆርጠው መሬት ላይ ጣሉት። ከዚህ ሁሉ ተረፈ። አንደኛ ተከሳሽ አደረጉት።
መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ ፍርድ ቤት ላይ በልበ ሙሉነት ይናገራል። እንኳን እንደዛ ተናግሮ እንዲያውም ይፈሩታል። ጨለማ ቤት አስረውት በአካል የማያገኛቸውን እስረኞች ለበርካታ ድርጅቶች አደራጅቷል ይሉታል። እንኳን ተናግሮ እንዲያውም ይጠሉታል። እሱም ከመናገር ወደኋላ አይልም። በአንድ ችሎት:_
“እኔ የፈፀምኩት ወንጀል የለም። ወንጀል ያደረጉት አማራነቴን ነው፣ የታሰርኩት አማራ በመሆኔ ነው!” ብሏል።
የቃጠሎው ክስ ተነስቷል ተብሎም አንደኛ ተከሳሹ መቶ አለቃ ማስረሻ በእስር ላይ ነው። በቀደመው ክሱ የተፈረደባቸው ጓደኞቹ ተፈትተዋል። እሱን ሰበብ ፈልገው በቀደመው ክስ እንዳቆዩት እየተነገረ ነው።
ልክ እንደ መቶ አለቃ ማስረሻ በማንነታቸው የታሰሩ፣ በማንነታቸው የሚጠሏቸው፣ ገመናቸውን የሚገልጡባቸውን በርካቶች አሁንም በማሰቃያ ቤት አጉረዋቸዋል!