***
“እኔ እንኳን ፍርድ ሞት አልፈራም ሞት ከማይፈራው አርማጭሆ ነው የመጣሁት!”
አበበ ካሴ
በፌደራል ማ/ቤቶች ከማዕከላዊ ጀምሮ በአስተባቡና በማንነቱ የተነሳ በአካሉ፣በሞራሉና በስነ ልቦና ከባድ ጥቃት የተፈፀመበት አርማጭሆ ያፈለቀችው ጀግና የአምባገነኖች ዱላ ያልበገረው፣እየገረፉት፣እያሰቃዩት፣እያንኮላሹት እንኳ ማንንም ሳይፈራ አላማውንና የወገኖቹን ክብር ብቻ በማክበር”እኔ አበበ ካሴ ለመቆየት ካበቃህ መቶ ዓመት መፍረድ ትችላለህ”በማለት በችሎት ላይ የተናገረው ቆፍጣናው ታጋይ አበበ ካሴ የመንደርተኞች ጠንካራ በትር ዋጋ አስከፍሎታል።
ብልቱን አንኮላሽተውታል፣በአካሉ አንካሳ እንዲሆን አድርገውታል፣እንደ እባብ በምርመራ ስም ቀጥቅጠውታል።ምን አልባት ቅጥቀጣው ከእባብ የተለየው አበበ ካሴ ጭንቅላቱን ብቻ ሳይሆን ሙሉ አካሉን ነው።
እኔ ቂሊንጦ ውስጥ አብሬው ታስሬ እያለሁ ይፈፀምበት የነበረው ለከት ያጣ ግፍን በዚህ ደካማ ቃል ለመግለፅ እቸገራለሁ።ይህን ሰው ማንም ኢትዮጵያዊ በተለይም አማራ ማጣት እንደሌለበት እነግራቹሀለሁ።ብዙ የስርዓቱን ገመና ተሸክሞ የተቀመጠ ሰው ነው፣ከፅናት ተምሳሌቱ አንዳርጋቸው ፅጌ ቀጥሎ ማንም የሰው ልጅ ስለ ፣ስለ ፍትህ፣ስለ ነፃነት ፣ስለ ክብር፣ስለ እኩልነት፣ስለ ማንነት እጨነቃለሁ እታገላለሁ የሚል ሁሉ ሊጨሁለት የሚገባው ሰው ነው።
አበበ ካሴ በፀረ ሽብር አዋጁ አንቀፅ 7(1) ተከሶ 7 ዓመት የተፈረደበት፣በችሎት መድፈር 9 ወር በጥቅሉ 7ዓመት ከ9 ወር እንደተፈረደበት እንዲሁም በቃሊቲ እስር ቤት እንደሚገኝ ይታወቃል።ያለ ማንም ጠያቂ ለእኔም፣ለአንተም፣ላንቺም፣ለእናንተና ለእኛ ለሁላችን ዋጋ እየከፈለ ያለ ጀግናችን ኢሰብአዊ ድርጊቶች የተፈፀሙበት መሆኑ አለም የሚያውቀው ሀቅ ነው፣ይህም የተፈፀመው መንደርተኛ አስተሳሰብ በተበከሉ፣ቂም ባረገዙ፣በሀሳብ የበላይነት ሳይሆን በግለሰብ የበላይነት የሚያምኑ፣የግፍ ፅዋቸው የማይሞላ፣የስርዓት እድሜ የሚያራዝሙ እየመሰላቸው በእኔ ትውልድ ላይ የዘመቱ የሀሳብ ደሀዎች የሚችሉትን ፈፅመውበታል።አበበ ግን የዋዛ አይደለም እስኪገድሉት ድረስ ያመነበትን ነገር ከመስራት ወደ ኃላ የማይል ብርቱ ሰው መሆኑን ተገንዝቤያለሁ።የተፈቱት ጠንካራ አባሪዎቹ ታጠቅና ብርሀኑ የበለጠ እነሱ የሚመሰክሩት ሀቅ ነው።
አበበ ዳኞችንም ጨምሮ ገለልተኛ አለመሆናቸውን ፊት ለፊት በመንገር፣ወይም ሲያሻው ችሎቱ የከተማ ሽፍታ ተባባሪ ነው በማለት ፊቱን ዙሮ በመቀመጥ፣ዳኛ ሲገባ ባለመነሳት፣አማራ ላይ የተቃጣውን ጥቃት በተለይ በወልቃይት፣በጎንደር፣በባህር ዳር እና በሌሎችም አካባቢዎች እስር ቤት ማቃጠልን ጨምሮ ስርዓቱ ሲያደርስ የነበረውን ጭፍጨፋ በግልፅ ቋንቋ ችሎት ላይ አውጉዟል፣ተቃውሟል።
ወደ ቃሊቲ ከተወሰደ በኃላም አማራ ክልል የድሮ በይቅርታ የወጣህበት የሀያ ዓመት ፍርድ አለብህ ተብሎ የመጣበት መሆኑ ታውቋል።”እኔ አበበ ካሴ እንኳን ፍርድ ሞት አልፈራም ሞት ከማይፈራው አርማጭሆ ነው የመጣሁት!”እያለ ሁሉንም ፍርድ እንዳመጣጡ ተቀብሎ አስተናግዷል።ቃሊቲ እስር ቤት ያመጣውን የመለያ ዩኒፎርምንም እኔ አበበ ካሴ ራቁቴን ብሄድ እንኳ የአንተን ሞርደፋ አለብስም” በማለት ለበርካታ ወራት በፅናት የታገላቸው መሆኑን አአውቃለሁ።
ለወገን ተቆርቋሪው ታጋይ አበበ ካሴ ይፈታ!ይፈታ!ይፈታ!
በአባይ ዘውዱ የቀረበ