>

የተስፋለም የእልህ ስሜት ለምን? [ጋዜጠኛ ኤሊያስ ገብሩ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ እንደጻፈው]

ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ፣ የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ከፍተኛ አዘጋጅ አስማማው ኃይለጊዮርጊስና ኤዶም ካሳዬ እንዲሁም ጦማሪያኑ አጥናፍ ብርሃኔ፣ ዘላለም ክብረትና ናትናኤል ፈለቀ በቀጠሯቸው መሰረት በትናትናው ዕለት (ሰኔ 07 ቀን 2007 ዓ.ም) በአራዳ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ይታወሳል፡፡ስለነበረው የፍርድ ቤት ውሎ እኔም ሆንኩ ሌሎች በስፍራው የነበሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያኖች በዚህ ፌስ ቡክ ገጾቻችን ላይ ጽፈን ነበር፡፡በወቅቱ በጣም ስሜቴን ከረበሹት ሁነቶች አንዱን እንዲህ ልንገራችሁ፡፡
የጋዜጠኝነት መርህን በማክበር፣ ለሚዛናዊ ጋዜጠኝነት እጅግ ተጠንቅቀው እና ተጨንቀው ለዓመታት ይጽፉ የነበሩት የልጅነት ወንድሜ እና ጓደኛዬ ጋዜጠኛ ተስፋለም ወልደየስ አጠር ያሉ እጆች ትናንትም ብረት ካቴና ተከርችመዋል፡፡
ተስፋለም፣ መሳሪያ በታጠቁ ፖሊሶች እንደታጀቡ ከጋዜጠኛ አስማማው [ባለፈው ሳምንት አዲስ ጉዳይ መጽሔት ‹‹የአስማማው እንባ›› በሚል ርዕስ ስለአስማማው ግላዊ እና ሙያዊ ሕይወት የተጻፈው ጽሑፍ እጅግ ልብ ይነካል፣ ያላነበባችሁ ሰዎች ብታነቡት ደስ ይለኛል፡፡] እና በብዙዎች ዘንድ በጣም ከሚወደደው ጦማሪው ዘላለም ክብረት ፊት ሆኖ ፈጠን ፈጠን እያለ ወደችሎቱ ለመግባት ሲራመድ አየሁት፡፡ ሶስቱንም ወደፍርድ ቤቱ ቅጥር ግቢ ሲገቡ ከነበርኩበት ቦታ አኳያ ለማየት አልቻልኩም ነበር፡፡
ሆኖም ተጠርጥረው የተያዙበት ጉዳይ ወደሚታይበት ችሎት አቅራቢያ ሲደርሱ ግን ሁሉንም በቅርብ ርቀት ላያቸው ችያለሁ፡፡ በተለይ ተስፋለም ከፊት ስለነበረ ፊት ለፊት የመተያየት ዕድሉ ገጠመኝ፡፡ እጄን አንስቼ ‹‹አይዞህ!›› አልኩት፡፡ ከጎኔ እስከዳር አለሙ [የጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ ታናሽ እህት] ነበረች፡፡ ተስፍሽ፣ ሁለታችንን አትኩሮ እያየ እልህ በተቀላቀለበት ስሜት ውስጥ ገብቶ፣ ሁለት እጆቹን በደንብ ጨምጦ፣ የታሰረበትን ካቴና በእልህ እያነቃነቀ ከፍ አድርጎ ሊያሳየን ሞከረ – ከአንደበቱ ግን ምንም ቃል አልወጣም፡፡ ፣ ‹‹ፍርድ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ ምንም ትንፍሽ እንዳትሉ!›› የሚል ትዕዛዝ ተሰጥቷቸው ከሆነስ ማን ያውቃል?!

ለጥቂት ቀናት ማዕከላዊ ታሰሬ በነበረበት ወቅት ከእነዚህ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ጋር ‹‹ጨለማ ክፍል›› በሚባለው የማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ አብረው ታስረው የነበሩ ኢትዮጵያዊ ወገኖቼን አግኝቼ አነጋግሬያቸው ነበር፡፡ በተለይ ተጠርጣሪዎቹ ለሁለተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበው ወደማዕከላዊ ሲመለሱ ፖሊሶች ‹‹እስኪ እነዚያ ፈረንጆች ያስፈቷችሁ እንደሆነ እናያለን? ፈረንጆቹ መጥተው ያስፈቷችሁ!›› በማለት በተቆጣ ስሜት እንደተናገሯቸው አውግተውኛል፡፡ [በሁለተኛው የፍርድ ቤቱ ቀጥር ግቢ ተገኝተው የነበሩ በርካታ የውጭ ሀገር ጋዜጠኞች እና ዲፕሎማቶች ተገኝተው ነበር]
እና ትናንት በተስፋለም ላይ ያየሁት የተንቀለቀለ የእልህ ስሜት በተውስታ ወደልጅነት ሕይወቱ ወስዶኛል፡፡ ተስፋለም፣ በልጅነቱ ወላጅ አባቱ እና እናቱ እንኳን ሳይቀር ትክክለኛ ባለሆነ መንገድ ሲረዱት፣ ሲናገሩትና ሲቆጡት በመሰል የእልህ ስሜት ውስጥ ሆኖ እውነቱን ለማስረዳት ጥረት ሲያደርግ እና በሀሳብ ሲሟገት አውቀዋለሁ፡፡ አሁንም ተጠርጥሮ የተያዘበት ጉዳይ ትክክል አይደለም በሚል ሀሳብ የንዴት ስሜት ውስጥ ገብቷል ብዬ አስባለሁ፡፡ ለሁለት እና ለሶስት ቀናት ተስፍሽን በአራዳ ፍርድ ቤት ሳየው ያ ለዓመታት የማውቀው የደስተኝነት ስሜቱን ፊቱ ላይ ፈጽሞ ማየት አልቻልኩም፡፡

ትናንትም አጠገቤ ሆና፣ የተስፋለምን እልህ የተቀላቀለበት የንዴት ስሜት በቅርብ ርቀት የተመለከተችው እስከዳር አለሙ በወቅቱ እንባዎቿን መቆጣጠር አልቻለችም ነበር፡፡ እኔም ብሆን ትናንት አመሻሽ ላይ በብራዚሉ የዓለም ዋንጫ ኮሎምቢያ እና ካሜሮን ያደረጉትን የእግር ኳስ ጨዋታ ከጓደኞቼ ጋር እየተመለከትኩ በፍርድ ቤት የታዘብኩትን የተስፋለም የእልህ ስሜት ለምን? ስል ሀሳብ እነጉድ ነበር፡፡ ኮሎምቢያ ሁለተኛ ጎል ሲያስቆጥር አይኖቼ ቴሌቭዥኑን እያዩ ቢሆንም ቀልቤ በቦታው የለም፡፡ አጠገቤ የነበረውን ጋዜጠኛ ዳዊት ሰለሞን ‹‹ጎል ገባ እንዴ?›› ብዬ ጠየኩት፡፡ ‹‹አዎን›› አለኝ፡፡ አላውቅም ወቅቱ ዳዊት ሳይታዘበኝ አልቀረም፡፡ ግን ምን ላድርግ? የተስፋለም ሁኔታ ረበሸኝ፣ አልክድም፣ በወቅቱ አይኖቼ እንባ አርግው ነበር – ዋጥኩት እንጂ፡፡ በቅርበት በሥራ እና ጎረቤት በመሆን ተስፋለምን የምታውቀው ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ በተደጋጋሚ ስለእሱ የምትጽፈው እውነት ነው፡፡ እህቴ ጽዮን፣ ተስፋለም እንደታናሽ ወንድም አንቺንም እንደናፈቀሽ ሁሉ እኔንም በጣም ናፍቆኛል፡፡ለማንኛውም እስኪ የሁሉም ተጠርጣሪ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የፖሊስ ምርመራ አልቆ የሚባሉትን አብረን ለማየት እና ለመስማት ያብቃን!

Journalsit Tesfalem

Filed in: Amharic