>

ዐቃቤ ሕግ በሁለቱ ሚዲያዎችና በሁለት ታዋቂ ግለሰቦች ላይ አቅርቦት የነበረውን ክስ ማንሳቱ ታውቋል (ጌታቸው ሺፈራው)

~በአርበኞች ግንቦት 7 የተከሰሱ በርካታ ተከሳሾች ክስ አልተቋረጠም

~በማዕከላዊ ከፍተኛ በደል የደረሰባቸው አስቻለው ደሴ፣ ዮናስ ጋሻው፣ ጌታ አስራደ እና ሌሎች የአማራ ተወላጆች ክስ አልተቋረጠም

(በጌታቸው ሺፈራው)
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በእነ ዶክተር መረራ ጉዲና ክስ መዝገብ በሁለት  በሚዲያዎች እና ሁለት ታዋቂ ግለሰቦች  ላይ አቅርቦት የነበረውን ክስ ማንሳቱን ምንጮች ገልፀዋል። በእነ ዶክተር መረራ ክስ መዝገብ  የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው የነበሩት የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት)፣ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትወርክ (ኦ ኤም ኤን)፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ጃዋር ሞሃመድ ክስ መቋረጡ ታውቋል። ዶ/ር መረራ ጉዲና ክስ ቀደም ብሎ መቋረጡ ይታወሳል።
ዐቃቤ ሕግ  137 ተከሳሾችን ክስ እንዳነሳ የገለፀው  የሁለቱን ሚዲያዎች እና ግለሰቦች ክስ ጨምሮ መሆኑ ታውቋል።
ይሁንና በግንቦት 7 ተከሰው በማዕከላዊ ስቃይ የደረሰባቸው፣ ብልታቸው የተኮላሸው አስቻለው ደሴ እና ዮናስ ጋሻው ክስ እንዳልተቋረጠ ለማወቅ ተችሏል። በተጨማሪም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ መምህሩ ጌታ አስራደን ጨምሮ የበርካታ አማራ ተወላጆች ክስ አለመቋረጡን ምንጮች ገልፀዋል።
በተቃራኒው  በአሁኑ  ወቅት በእስር ላይ ያሉትን ክስ ከማቋረጥ ይልቅ ቀደም ብሎ ክሳቸው የተቋረጠላቸውን ስም በማካተት የብዙ ተከሳሾች ክስ እንደተቋረጠ ለማስመሰል ተጥሯል ተብሏል።
ከአሁን ቀደም ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር የተፈቱ አስቻለው አብርሃምና ሌሎች ተከሳሾችን ስም ዐቃቤ ሕግ በአሁኑ ወቅት ክሳቸው ተቋርጧል በሚል የቁጥር ማሟያ አድርጓቸዋል ተብሏል።
Filed in: Amharic