>

‹‹ቂሊንጦ ውስጥ የተነሳውን እሳት እኛ ነን የቀሰቀስነው፤ እገሌ አቃጥሉ ብሎን ነው›› ካላልን መሞታችን ነው!!!

ከ ጭቆናው ይብቃ የተገኘ
በሐሰት ተወንጅለን፣ በግፍ ታስረን፣ እየተንገላታን ከዛሬ ነገ ‹‹ከታሰርንበት እንፈታለን›› ብለን ስንጠብቅ ይኸው በአንድ ጀምበር ሁኔታዎች ተቀያይረው እንኳን ስለመፈታት በሕይወት መትረፋችንንም የማናውቅበት ሁኔታ ውስጥ ወድቀናል፡፡ በነበርንበት ቂሊንጦ ከተነሳው የእሳት አደጋ በአላህ ፍቃድ ብንተርፍም መትረፋችን ያስቆጫቸው አፋኞቻችን ግን ሌላ እሳት ውስጥ ጨምረውናል፡፡ ነፍስ አላህ ሙቺ ካላት ቀን በፊት የማትሞት ሆና እንጂ ለደካማይቷ ሕይወታችን ያለንበት ስቃይ በቂዋ ነበር!
.
ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች! መቼም ይህ መልእክቴ ደርሷችሁ ከሆነ የዚህች ጽሑፌ ዓላማ እየተፈጸመብን ያለውን፣ እንዲሁም ሊፈጸምብን የተጠነሰሰውን ሴራ ለህዝብ ይፋ ለማድረግ መሆኑ አይጠፋችሁም፡፡ መቼስ እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዛሬ የቲሞች ነን፡፡ የሚወክለን አካል የለምና የመንግስት አቅጣጫ ማስቀየሪያ፣ የአጀንዳ ማስከፈቻ፣ የወንጀል ማከማቻ ሆነናል። ይኸው አሁን ደግሞ በርካታ ሕይወት የቀጠፈው የቂሊንጦ እሳት አደጋ እኛው እስረኞች ላይ ሊደፈደፍ ታቅዶ ሽርጉዱ ተይዟል፡፡ የማዕከላዊ መርማሪዎች ወደተወሰድንበት ሸዋ ሮቢት መጥተው ‹‹የሚሽኑ ጠንሳሽ እናንተ ስለሆናችሁ ነው ከእናንተ ውስጥ አንዳችሁም ያልሞታችሁት›› አሉን …. በአደጋው ባለመሞታችን ቁጭት ቢያንገበግባቸው!
.
ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች…! እሳት አደጋው የተነሳው በመንግስት ጠንሳሽነት ነው፡፡ አደጋው ከመነሳቱ በፊት በነበሩት ወራቶች የተለያዩ የወህኒው ጥበቃ አካላቶች ስራቸውን ጥለው መሸሻቸውን ሁላችንም እናውቃለን። በዚያው ወር ውስጥ ግምገማ እንደነበረባቸውም ሰምተናል። በጎንደርና በኦሮሚያ ከተነሣው ተቃውሞ ጋር ተያይዞ እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ ውጥረት እንደነበር አልዘነጋነውም። መንግስት ከአደጋው ምን ሊያተርፍ እንዳቀደ ለጊዜው ይቆይና ምን እንደተፈጠረ በአጭሩ ልንገራችሁ…
***
ምግብ ማስገባት በተከለከለ ማግስት ገና በጠዋቱ ጆሯችን እንግዳ ነገር አደመጠ፡፡ የተኩስ ድምጽ ነበር። ሁላችንም ተደናግጠን ከየት እንደተተኮሰ ግራ ገብቶን ስናማትር ተኩሱ ይደጋገም ያዘ፡፡ እሪታ እና ዋይታ… የድረሱልን ጥሪ ግቢውን ሞላው፡፡ ወደ ሰማይ የሚንበለበል እሳትና ጭስ ተመለከትን፡፡ ይሄኔ የእሳት አደጋ እንደተነሳ ሲገባን ከእኛ ቀጥሎ ወዳለው ዞን ለመሸሽ በህብረት በሩን መግፋት ጀመርን፡፡ አልከፈት አለን፡፡ ሌላ ምርጫ አልነበረንምና ሁላችንም በአንድ ድምፅ መጮሁን ተያያዝነው፡፡ ጥበቃዎች ግን በሩን ከፍተው እኛን ከተነሳው የእሳት አደጋ በማሸሽ ፋንታ እኛው ላይ አስለቃሽ ጭስ ይተኩሱብን ጀመር፡፡ ተኩሱ እና ጩኸቱ አላባራ አለ፡፡ በእርግጥም አደገኛ ሁኔታ ነበር!
ከሁሉም የሚያሳዝኑት ሆን ተብሎ የሚተኮስባቸውን ጥይት ለማምለጥ ሲሸሹ እሳት የበላቸው እስረኞች ነበሩ፡፡ ከእሳት አደጋው ለማምለጥ ብለው በተተኮሰባቸው ጥይት ህይወታቸው ያለፉም በርካቶች ነበሩ፡፡ በዚያ ስቃይ መሐል አንድ ላይ የነበርን ሙስሊም ታሳሪዎች አንደኛው የአንደኛውን በህይወት መኖር ለማረጋገጥ ስም እየተጠራራን ተቃቅፈን ከመላቀስ በስተቀር ምንም ልንፈጥር አልቻልንም።
የዚያች ሌሊት ስቃይ ታሪኩ ሰፊ ነው፡፡ ለሁላችንም ደህንነት በማሰብ ፍቃዳቸውን ሳልጠይቅ ስለ ቃጠሎ ማንሳት ባይኖርብኝም በጥቂቱ ግን ይህን ካልኳችሁ ይብቃ፡፡ አላህ ብሎ አሁን ካለንበት ስቃይ ከተረፍን አንድ ቀን በአደባባይ እንናገረው ይሆናል! ማን ያውቃል!?
መንግስት ‹‹እሳት አደጋውን ያስነሱት እስረኞች ናቸው›› ሲል ለማሳበብ ቀድሞ አቅዶ ነበር፡፡ ለዚህም ከአደጋው አንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ታሳሪውን የሚያስቆጣ ሰበብ መፈለጉን ተያይዞት ነበር፡፡ እኛን ሆን ብለው ለማስቆጣት የተለያዩ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የቆዩት ለዚሁ ነው፡፡ ለረጅም ቀናት ውሃ አጥፍተውብን መቆየታቸው አንዱ ትንኮሳ ነበር፡፡ ያም ሆኖ ግን በቂ ሆኖ ስላላገኙት ከእሳት አደጋው አንድ ቀን በፊት ምግብ ከቤተሰብ እንዳይገባልን ከለከሉ። የእሳት አደጋው ‹‹ክልከላውን ተከትሎ የተነሳ አመፅ ነው›› ሲሉ ለማሳበብ መሆኑ ጥርጥር የለውም።
ስላለፈው ይህን ካልኩ ይብቃ፡፡ በቀጣይ ጊዜያት የኢትዮጵያ ሙስሊም እስረኞች ላይ ስለተደገሰው የተንኮል ድግስ የማውቀውን ልንገራችሁ….
አሁን ያለንበት ሁኔታ እጅግ አሳዛኝ ነው። ሸዋ ሮቢት ከአጋዚ ጥበቃዎቿ ጋር ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ!›› ብላ ተቀብላናለች። ከመጣንበት እለት ጀምሮ አንዱ ቀን የአንድ ወር ያክል ረዝሞብናል። እጃችን በካቴና ተቆልፏል፡፡ ጨለማ ክፍል ተዘግቶብን ዓይናችን ከብርሃን ተራርቋል፡፡ ከጸሐይም ከቤተሰብም ጋር የምንገናኘው በህይወት መኖራችንን ለማየት ቤተሰብ ሲመጣ በምትፈቀድልን ሶስት ደቂቃ ብቻ ነው።
ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች…!
ሰው ማሰቃየት እንጀራቸው የሆኑት የማዕከላዊ መርማሪዎች ካለንበት እስር ቤት ሰፍረዋል፡፡ አንድ በአንድ እየጠሩ ያሰቃዩናል። ሙሉ በሙሉ የእሳት አደጋውን በእኛ ላይ ለመደፍደፍ እንዳሰፈሰፉ ግልጽ ሆኗል፡፡ ከሙስሊም ታሳሪዎች አብዛኛውን መልሰው ወደ ማዕከላዊ ሊያስገቡን እና ሶስት ውንጀላዎች ሊያቀርቡብን እንደሆነ መርዶውን አርድተውናል።
‹‹ወንጀላችሁ ሶስት ነው›› አሉን ገራፊዎቻችን….
‹‹መንግስት ያለበሳችሁን ዩኒፎርም ማቃጠል… !!!››
‹‹ማረሚያ ቤት ውስጥ አመጽ መፍጠር…. !!!!››
‹‹እሳት ለኩሶ የታሳሪዎችን ነፍስ ማጥፋት… !!!!››
*****
ያልሰራነውን ወንጀል ደፈደፉብን! ለዚህ የሃሰት ክሳቸውም 25 አካባቢ ምስክሮችን አዘጋጅተዋል። ከምስክሮቹ ብዙዎቹ ከዚህ በፊት የመንግስት ሰራተኛ የነበሩና በሙስና ተወንጅለው የነበሩ ናቸው፡፡ ቂሊንጦ ልዩ ዞን አራት በሚባል ቦታ አስቀምጠዋቸዋል።
እስካሁን ወደ ሶስት ጊዜ ያክል እየጠሩ ፎቶ አንስተውናል። ወደ ማዕከላዊ ሲወስዱንም የተለመደውን የሃሰት ዶኩመንታሪ እንደሚሰሩብን እንገምታለን። መቼም እኛ ወንድሞቻችሁ ነገ ስቃይ እና ግርፋት አብዝተውብን በመንግስት ቲቪ አቅርበው ‹‹ቂሊንጦ ውስጥ የተነሳውን እሳት እኛ ነን የቀሰቀስነው፡፡ እገሌ አቃጥሉ ብሎን ነው›› ካላልን ግድያም ሊከተል እንደሚችል በተለያየ መንገድ እያሳወቁን ነው። በስቃይ ብዛት እኛ ነን ቢያስብሉን እንኳ እንደማትጭበረበሩ እናውቃለንና ብቸኛ መጽናኛችን እሱ ነው!
አሁን ላይ ሁሉን ነገር አክፍተውብናል፡፡ እጃችን በካቴና ተጠፍሮ የምንሰግደውንም ሰላት ይከለክሉን ጀምረዋል። ውሃ ከቤተሰብ እንዳይገባልን ተደርጎ በዚያ በረሃ በውሃ ጥም ተቃጠልን። ልብስ እና ጫማችንን የቂሊንጦ እሳት በላው። እዚህ ደግሞ እንዳይገባልን ከለከሉን። ማታ ማታ የሚያሰሩን ከባድ ስፖርት አታከተን። ከአቅማችን በላይ የሚያሰሩን የቀን ስራ አጎበጠን፡፡ ይህ ሁሉ በሀሰት እኛን ለመክሰስ የሚደረግ ጥረት ነው።
ውድ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች…! ይህ መልእክት የደረሳችሁ ወንድምና እህቶች…!
እኛ መሞትም ባልገደደን ነበር… ሙስሊሙ ላይ እየተደፈደፈ ያለው የሃሰት ውንጀላ ግን አልፈንም ይቆጨናል፡፡ ሞተንም ይቆረቁረናል፡፡ ተገፍተን… ታስረን …. በሐሰት ተፈርዶብንም ዝም ባልንበት ለምን ይህ ሁሉ ግፍ ይሰራብናል? ጥፋታችንስ ምንድን ነው? ለምንስ ዳግም የሃሰት ውንጀላ ይጠብቀን?
ይህ መልእክት የደረሳችሁ ሙስሊም ወንድምና እህቶች…. ከእናንተ የምንፈልገው ከሁሉም በፊት ዱዓችሁን ነው! ብትችሉ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ በሀሰት እንዳንከሰስ የተቻላችሁ ሁሉ ጣሩልን! ድምጻችንን አሰሙልን! ወሰላሙዓለይኩም ወራህሙቱላህ!
….
የጨነቀኝ ወንድማችሁ…. ከግፍ ማሰቃያው ሸዋ ሮቢት #EthioMuslims
Filed in: Amharic