>

የፌደሬሽኑ ውሳኔ ተገቢ ነው!!! (መሳይ መኮንን)

የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የስፖርት ፌደሬሽን ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢ ነው። ምክንያቴ ግን ዶ/ር አብይ እንዳይገኙ ከመፈለግ አይደለም። ለእሳቸው ካለኝ አቋም ጋር በተያያዘም አየደለም። የአንዳርጋቸው ፍቺና በመቀሌው የህወሀቶች ጉባዔ ላይ የሰማሁት ነገር ሁኔታዎችን በጥሞና መከታተል እንዳለብኝ ተሰምቶኛል። ቀድሞውኑ እሳቸው ለውጥ የማምጣት ፍላጎት አላቸው በሚለው አወንታዊ አመለካከቴ ላይ የሰሞኑ የአንዳርጋቸው አፈታት ላይ ያደረብኝ ተስፋ ሲጨመርበት በቀጣይ ስትራቴጂካዊ በሆነ መልኩ ዶ/ር አብይን ማበረታት እንደሚገባ አምኜለሁ። ለውጥ ለማምጣት የሚችል ሰው ቤተመንግስት ገብቷል የሚል እምነት አለኝ።
 የእስከአሁኑ ጉዞአቸው ለውጥ ለማምጣት ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት ያሳያል። ለውጡ ግን ገና ነው። ምልክቶቹ ተስፋ ቢሰጡም በፖሊሲ ደረጃ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት የሚረዱ እርምጃዎች ገና እየተጠበቁ ነው። ከልክ ካለፈ ተቃውሞና መጠኑን ከሳተው ፍቅር የወጣ ስትራቴጂካዊ በሆነ ድጋፍ ዶ/ር አብይ ከህወሀቶች ጋር የገቡበትን ትግል በድል እንዲወጡት ማድረግ ለሀገራቸን መጪ የዲሞክራሲ ጉዞ ወሳኝ ነው።
የፌዴሬሽኑ ውሳኔን የደገፍኩት ዲያስፖራው ሌላ ትርምስ ውስጥ እንዳይገባ በሚል ነው። አሁን ባለው ስሜት፡ በተከፋፈለው ዲያስፖራው መሀል ዶ/ር አብይ ቢመጡ ሀገር ቤት እንደፈጠሩት ዓይነት አንድነት ያመጣሉ ብዬ አላምንም። ከዚያ ይልቅ አንድነቱን የሚሸረሽር፡ ለመቀራረብ እየታየ ያለው ተስፋ የሚያጨልም ነው። ዲያስፖራ ውስጥ አሁንም በዶ/ር አብይ አካሄድ ላይ ጥያቄ የሚያንሱ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሉ። የእነዚህን ኢትዮጵያውያን እምነት የማግኘት ስራ ከዶ/ር አብይ ይጠበቃል።
 ከመቃወም ሱስ ጋር ሳይያያዝ መሰረታዊ ጥያቄዎችን በማንሳት የእሳቸውን አስተዳደር የሚሞግቱ ኢትዮጵያውያን እምነት ማሳደር ይፈልጋሉ። እምነት ማግኘት ከባድ ስራ ነው። ከኢህአዴግ ማህበር የመጣ ይቅርና በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መሪም እምነት ለማግኘት ብዙ በዓይን የሚታዩ ስራዎችን ይጠይቃል። እናም ዶ/ር አብይ በመልካም ስሜት በጀመሩት ጉዟቸው ላይ መሰረታዊ ለውጦችን የሚያመጣ እርምጃ እየወሰዱ ሲሄዱ በጥርጣሬ የሚያዩ ሰዎችንም በማሸነፍ ጠንካራ እምነት ያሳድራሉ። ያን ጊዜ ዘንባባ አንጥፎ የሚቀበላቸው እንጂ የሚቃወማቸው አይኖርም። ያ ሳይሰራ በሆይ ሆይታና ሞቅታ ውስጥ ሆኖ በችኮላ መምጣት ጥርጣሬውን ሊያሰፋ፡ አንድነቱንም ሊያናጋ ይችላል። የእሳቸው ስም በዚህ መልኩ በመጥፎ እንዲነሳ መደረግ የለበትም። የእሳቸው ፍላጎት እንደህወሀቶች አንድነትን ማጥፋት፡ መከፋፈልን መፍጠር አይደለም።
ከዚህ አንጻር ፌዴሬሽኑ በበሳል አካሄድ የደረሰበት ውሳኔ ዶ/ር አብይንም ታድጓል የሚል እምነት አለኝ። ውሳኔውን የገለጸበት መንገድም ለዶ/ር አብይ ያለውን አክብሮት ያሳየበት በመሆኑ ሊደነቅ ይገባል። እስከሚቀጥለው ዓመት የተወሰነ ፍንጭ መታየቱ አይቀርም። ዶ/ር አብይ በጀመሩት ተስፋ ሰጪ መንገድ ላይ መሰረታዊ እርምጃዎችን በቆራጥነት የሚወስዱ ከሆነ ዲያስፖራው አንድ ሆኖ በፍቅር የሚቀበላቸው ልዩ የስፖርት በዓል ሊሆን እንደሚችል ከውዲሁ መገመት አይከብድም።
Filed in: Amharic