>

ተቃዋሚዎች እና ዘጠኙ ቂሎች (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

ዶ/ር አቢይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስልጣን ከተቆናጠጡ ዛሬ (ግንቦት 24) ስድሳ ቀን ሞላቸው፡፡ እኛም የዶ/ር አቢይን እርምጃ አንዳንዴ በጥርጣሬ፣ አንዳንዴ በመገረም፣ አንዳንዳንዴም በመደነቅ እየተመለከትንና እያስተዋልን 60 ቀናት ያህል በዝምታ ቆየን፡፡ አሁን የተቃዋሚዎች ቅዋሜ ደርዝ የለሽ እየሆነ መሄዱን በታዘብን ጊዜ ዝምታችንን ሰብረን ብቅ አልን፡፡
.
እዚህ ላይ ዶ/ር አቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ የከወኑትን ደግመን አንዘረዝርም፡፡ የሚታወቅ ነውና፡፡ “ተዓምር” ሰርተዋል ብለንም ከበሮ አንደልቅም፡፡ እንዲያም ሆኖ የኢትዮጵያን መልከ ጥፉ ፖለቲካ ለማሳመር እየወሰዱ ያሉት እርምጃ የሚናቅ አይመስለኝም፡፡ “እጅ በነክ” የሚባል እንጂ፡፡
.
በነገራችን ላይ የዶ/ር አቢይን እርምጃ “እጅ በነክ” አለማለት ይቻላል፡፡ መንቀፍም፣ ማብጠልጠልም ይቻላል፡፡ ነቀፋው ቅጥ ሲያጣ ግን ያስተሳዝባል፡፡ “ሱሪ በአንገት አውልቁልኝ” ማለትም አላዋቂነት ይመስለኛል፡፡ የቀድሞው አለቃዬ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና እንዲህ ዓይነቱ ፅንፍ የለሽ ነቀፋ አስገርሞት ይመስለኛል “ …ምናልባት ዶ/ር አቢይ ሥልጣናቸውንም ቤተመንግሥቱንም ለተቃዋሚዎች ለቀው ቢሄዱ እንኳ ምን አስበው ነው ብሎ የሚቃወም ሰው ይኖራል” ሲል በኢሳት ቴሌቪዥን የተደመጠው፡፡
 .
በዚህ የሲሳይ አባባል ውስጥ “የተገኘው ፖለቲካዊ ድል ይዞ ለተጨማሪ ድል መምግዘግ ሲገባ ሁሉን ነገር ሁሉን ነገር እጃችን ላይ ዘርግፉልን ማለት ትርፉ መከራ ነው” የሚል መልዕክት ያዘለ ይመስለኛል፡፡ የሚገርመው ነገር የዶ/ር አቢይን እርምጃ ከመንቀፍ አልፈው የሚያብጠለጥሉትና ለማንኳሰስ የሚጣደፉት “ተራ ተርታው” (ተራ ተርታ የሚባል ካለ) ሰው ብቻ አይደለም፡፡ አንዳንድ የተቃዋሚ  ፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጭምር መሆናቸው ነው የሚገርመው፡፡  (“አንዳንድ” የሚለውን ቃል ያዙልኝ)…. ለምሳሌ ያህል ከእነዚህ አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች መሃል አንዱ ትናንት በፌስቡክ ገፃቸው ከሰነዘሩትን አስተያየት በጥቂቱ ልጥቀስ፡-
.
“እንደ አዲሱ ግልብጥ በዶር አቢይ በኩል የኢህአዴግ ደጋፊ መንጋ አተያይ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ቀላል ቢሆን ኑሮ እኔም የኢሕአዴግ ደጋፊ እሆን ነበር” ሲሉ ነው የሚጀምሩት እኚህ የፖለቲካ ድርጅት መሪ፡፡ የግንቦት ሰባቱ መሪ በአንዳርጋቸው ፅጌ መፈታት፣ እንዲሁም ከዶ/ር አቢይ ጋር በመገናኘታቸው የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ያደነቁ ሰዎችን ነው “መንጋ” የሚሉት፡፡ በአጭሩ እኚህ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሪ ፅሁፍ ማዕከላዊ ጭብጥ ዶ/ር አቢይ “የሚመጥን የፖለቲካ እርምጃ ሲወሰድ አላየሁም” የሚል ሃሳብ ነው የያዘው፡፡
.
 የሚገርመው ነገር እኚህ ሰው “መንጋ” የሚሉትን ሕዝብ መምራት እችላለሁ ብለው ነው ፓርቲ የመሰረቱት፡፡  ሃሳባቸውን እንኳ በትክክል መግለፅ ሳይችሉ ነው ሕዝብን “መንጋ” የሚሉት፡፡ እስቲ ከላይ የጠቀስኩላቸውን ዓረፍተ ነገር ልብ ብላችሁ አንብቡት? “እንደ አዲሱ ግልብጥ” ማለት ምን ማለት ነው?  ከቀጣዩ ሃሳብ ጋር እንዴት እና በምን ይያያዛል? ሃሳብን እንኳ በትክክል መግለፅ ሳይችሉ ለነቀፋ መንደርደርስ ምን የሚሉት አዋቂነት ነው?፡
.
እንደዚህ ዓይነት ነቃፊዎችን ባስተዋልኩ ቁጥር ትዝ የሚሉኝ “ዘጠኙ ቂል ወንድማማቾች” ናቸው፡፡ ታሪኩ ዘጠኙ ቂል ወንድማማቾች ለዘመቻ ታዘው በሄዱ ጊዜ የሆነ ነው አሉ፡፡
.
እናታቸው “በጦርነቱ ላይ ተለያይታችሁ ከቁጥር እንዳትጎሉ፤ አደራ” ብላ አስጠነቅቃ ለዘጠኙም ዘጠኝ ጭብጦ ሰጥታ ሸኘቻቸው፡፡ እናም መንገድ ጀመሩ፡፡
በመሃሉ …..
“እናታችን ከቁጥር እንዳትጎሉ ብላናለችና  አሁኑን እንቆጣጠር” ተባባሉ፡፡  መሃል ላይ እኮ ነው ያሉት፡- መንገድ ላይ፡፡ ዘመቻው ቦታ ሳይደርሱ ነው “እንቆጣጠር” የተባባሉት፡፡
ተስማሙ፡፡
አንዱ ወንድሞቹን ደርድሮ ቆጠረ፡፡
ስምንት ናቸው፡፡
ደነገጠ፡፡
ሌላው ተተካና ወንድሞቹን ደርድሮ እንደዛው ቆጠረ፡፡
ስምንት ናቸው፡፡
.
ጉድ ፈላ! የእናት አደራ መና ሊቀር ነው፡፡ ደነገጡ፡፡
.
በዚህ መሃል አንድ ሰው ቂሎቹ ወንድማማቾች ወዳሉበት መጣ፡፡ ችግራቸውን ነገሩት፡፡ ከቁጥር መጉደላቸው እንደጨነቃቸው አስረዱት፡፡ አንድ ወንድም ጎደለብን አሉት፡፡  ሰውየው በመገረም አያቸው፡፡ ቆጣሪዎቹ ራሳቸውን ባለመቁጠራቸው የተነሳ “ከቁጥር እንደጎደሉ” ገባውና ናሳቅ አለ፡፡
“እኔ ወንድማችሁን ባገኝላችሁ ምን ትሰጡኛላችሁ?” ሲል ጠየቃቸው ሰውየው፡፡
“የያዝነውን ጭብጦ እንሰጥሃለን” አሉት፡፡
.
ተደርደሩ አላቸው፡፡ እናም ቆጠራቸው፡፡ ዘጠኝ ናቸው፡፡ ከቁጥር አልጎደሉም፡፡ ደ….ስ አላቸው፡፡ ጭብጦአቸውን ለመንገደኛው ቆጣሪ አስረክበው ሄዱ፡፡
.
ይኸው ነው፡፡
አሁን በተቃውሞው ጎራ  ነቀፋ እንደ ቂሎቹ ትርክት ዓይነት ነው የሚመስለው፡፡ “ከተቃዋሚነት ቁጥር እንዳትጎሉ አደራ” የተባሉ ነው የሚመስለው፡፡ ዘመቻው ቦታ ላይ ሳይደርሱ መሃል ቆመው “ከተቃዋሚነት እንዳትጠፋፉ አደራ” የተባሉ ይመስል፣ “ይኸው አቢይን/ኢህአዴግን” አብጠልጠልኩት የሚል የባዶ ጀግንነት ጀብድ መተርከክ የሚፈልጉ ነው የሚመስሉት፡፡ ወደ ዋናው የፖለቲካ ሜዳ ዘልቀው ከመፋለም (መስራት የሚገባቸውን ከመስራት፣ ደጋፊያቸውን ከማንቃትና ከማደራጀትና የፖለቲካ ሂደቱ ላይ ከመንቃት ይልቅ) ራሳቸውን ሳይቆጣጠሩ/ሳይቆጥሩ፤ እርስ በርስ “በመቆጣጠር” ላይ ያሉ ነው የሚመስሉት፡፡
.
ይኸው ነው! በቃ ይኼንን ነው የሚመስሉት!
Filed in: Amharic