>

አማራዎች ይፈናቀላሉ፣ ልሂቃኑ ይጠላለፋሉ፣ የህወሓትን ግብ ያሳካሉ! (ስዩም ተሾመ)

ባለፉት ሦስት ሳምንታት ከተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች ስለተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆች ጉዳይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት እየተነገረ ይገኛል። ብዙ ተስፋ የተጣለበት አዲሱ የዶ/ር አብይ አመራር፣ በተለይ ደግሞ ወደ ባህር ዳር በመሄድ በኢትዮጲያዊነት መንፈስ የኦሮሞና አማራ ሕዝቦች አንድነትና አብሮነት መልሶ እንዲያሰራራ ያደረጉት ኦቦ ለማ መገርሳ በፕረዜዳንትነት በሚመሩት ክልል ውስጥ የአማራ ብሔር ተወላጆች መፈናቀላቸው ለብዙ የአማራ ልሂቃን አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆን አደናጋሪ ሆኗል።

ባለፈው ከምዕራብ ሸዋ ዞን የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች ወደ ቄያቸው በተመለሱ ማግስት ከኢሊባቡር ዞን የተፈናቀሉ 200 ሰዎች በአማራ ምግብ ዋስትና መስሪያ ቤት እንደሚገኙ መገለፁ ይታወሳል። ሰሞኑን ደግሞ ብዛት ያላቸው የአማራ ተወላጆች ከወለጋ አከባቢ ተፈናቅለው ወልዲያ አከባቢ እንደሚገኙ ተገለፀ።

ከወዳጄ መንግስቱ ዘገየ ጋር በመሆን እነዚህ ሰዎች ለምንና መቼ እንደተፈናቀሉ ለማጣራት ጥረት አደረኩኝ። በዚህ መሰረት፣ ተፈናቃዮቹ ከወለጋ ብቻ ሳይሆን ከኢሊባቦር ዞን፣ እንዲሁም ከጋምቤላ ክልል ጭምር የተፈናቀሉ መሆኑን ለመረዳት ችያለሁ። የተፈናቀሉበት ግዜ ግን ከሦስት ወር በፊት፥ በየካቲት ወር መጀመሪያ ላይ ነው። ከሁለት ሳምንት በፊት ከኢሊባቡር ዞን ተፈናቅለው በአማራ ምግብ ዋስትና መስሪያ ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚገኙትን በስልክ አነጋግሬያቸው ነበር። ስለዚህ በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የተፈናቀሉበት ምክንያትና ግዜ አንድና ተመሳሳይ ነው።

ባለፈው ሳምንት በባህር ዳር የሚገኙትን ተፈናቃዮች አስመልክቶ የአማራ ክልላዊ መስተዳደር የአጣሪና መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አቋቁሟል። ይህ ኮሚቴ ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመሄድ በአከባቢው በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ላይ ስለተፈፀመው በደልና ግፍ በአካል ተገኝቶ አጣርቷል። ይህንንም የኮሚቴው አባላት ጋር ስልክ በመደወል አረጋግጬያለሁ። በተመሳሳይ የኦሮሚያ ክልል አመራሮች ከክልሉ የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን ወደ ቄያቸው ለማስመለስና ችግሩን ከስሩ ለመቅረፍ ፍቃደኛ መሆናቸውንና ከአማራ ክልል ኃላፊዎች ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደሆነ ለማወቅ ችያለሁ።

በወልዲያ አከባቢ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ችግር ለመቅረፍ የተቋቋመው ኮሚቴ ከኦሮሚያ ክልል ኃላፊዎች ጋር ለመነጋገር ትላንት ወደ አዲስ አበባ መምጣቱን ወዳጄ መንግስቱ ዘገየ አረጋግጦልኛል። የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ኃላፊዎችም የኮሚቴውን አባላት በቀናነት ተቀብለው እንደሚያስተናግዷቸው እና ችግሩን በዘላቂነት እንደሚቀርፉት እምነቴ የፀና ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ በኦሮሞና አማራ ልሂቃን በኩል ሊሰመርባቸው የሚገቡ ነጥቦች አሉ።

የአማራ ተወላጆች ከተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች የተፈናቀሉት በየካቲት ወር አጋማሽ ላይ ነው። የየካቲት ወር የህወሓት ትግል የተጠነሰሰበት ብቻ ሳይሆን የተጨናገፈበት ጭምር ነው። ህወሓት የካቲት 1967 ዓ.ም ሲመሰረት የአማራ ሕዝብን በጠላትነት ፈርጆ፣ ቂምና በቀልን ዓላማ አድርጎ ነው። ይህንን ደግሞ በተለያየ መንገድ እስከ የካቲት 2010 ዓ.ም ድረስ ተግባራዊ አድርጎታል። በዚህ ዓመት የካቲት ወር ላይ ህወሓት በኦሮማራ ጥምረት አከርካሪው ከመመታቱ በፊት የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በማወጅ ራሱን ለመታደግ ጥረት አድርጓል። ለዚህ ደግሞ በኦሮሞና አማራ ተወላጆች መካከል ግጭትና ሁከት ማስነሳት አለበት።

ስለዚህ ከየካቲት 5/2010 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች በሚኖሩ የአማራ ተወላጆች ሕይወትና ንብረት ላይ ጥቃት እንዲፈፀም አድርጓል። በዚህ ምክንያት ከላይ በተጠቀሱት አከባቢዎች የሚኖሩ አማራዎች ከቄያቸው ተፈናቅለዋል። ያለ ማንም ድጋፍና እርዳታ በተበታተነ መልኩ፣ ገንዘብ ያለው በራሱ ወጪ፣ የተቀሩት ደግሞ መንገደኛ እየለመኑ ተጉዘው ወደ ባህር ዳር፣ ወልዲያና ሌሎች አከባቢዎች ለመሰደድ ተገድደዋል። ከዚህ በተጨማሪ በቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ ንፁሃን የኦሮሞ ተወላጆች በግፍ ተጨፍጭፈዋል። በአርሲ ዞን ኢተያ አከባቢ ደግሞ የሃይማኖት ግጭት ተቀስቅሷል።

በአጠቃላይ የዚህ አመቱ የካቲት ወር ባለፉት 27 አመታት ከነበሩት ሁሉ የተለየ ነው። ህወሓት በተለመደ ሸርና አሻጥር በስልጣን ለመቆየት ምስኪን የአማራ ተወላጆችን አፈናቅሏል። የአማራና ኦሮሞ ሕዝቦችን ጨምሮ መላ የሀገሪቱ ሕዝብ በወቅቱ በነበረው ፖለቲካዊ ሁኔታ ፍፁም ግራ ተጋብቷል። የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችም ከሀወሓት ጋር የለየለት ትንቅንቅ ውስጥ ገብተው ስለነበር በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች የተከሰተውን መፈናቀል ተከታትሎ ለማስተካከልና የእርምት እርምጃ ለመውሰድ የሚችሉበት ሁኔታ አልነበረም። ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አማካኝነት አንዳንዶቻችን እስር ቤት ገባን። የአዋጁ ዓላማ ግን ዋና ዋና የኦህዴድና ብአዴን አመራሮችን ለማሰር ነበር።

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ ከሶስት ወር በፊት የኦህዴድና ብአዴን ከፍተኛ አመራሮች እንኳን የሚመሩትን ሕዝብ የራሳቸውን ሕልውና ማረጋገጥ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ነበሩ። በዚህ ወቅት በብዙ አከባቢዎች ሰዎች ተፈናቅለዋል፣ ተገድለዋል። እነዚህ ሰዎች ፍትህ ማግኘት፣ ወደ መኖሪያ ቄያቸው መመለስ አለባቸው። ከላይ በፅሁፌ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የሁለቱም ክልል መስተዳደሮች ችግሩን ለመቅረፍ በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ፣ ከሶስት ወር በፊት፣ በዚያ ቀውጢ ሰዓት የተፈናቀሉ የአማራ ተወላጆችን ልክ ትላንት በእነ ለማ መገርሳ እና ገዱ አንዳርጋቸው ቸልተኝነት እንደተፈፀመ አድርጎ ማቅረብ ፍፁም ስህተት ነው።

በአማራና ኦሮሞ ልሂቃን እንዲህ ያለ መከፋፈል የህወሓትን ዓላማና ግብን ከማስፈፀም የዘለለ ፋይዳ የለውም። እርግጥ ነው ችግሩ ተከስቷል። ነገር ግን፣ “ለምንና መቼ ተከሰተ?” ብለን መጠየቅ አለብን። የችግሩን መሰረታዊ መንስዔ መለየት ከቻልን ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ይቻላል። እርስ-በእርስ መጠላለፍና መዘላለፍ ከጀመርን ግን አሁን ያለውን የለውጥ ጭላጭል ያዳፍነዋል።

Filed in: Amharic