>
5:18 pm - Wednesday June 16, 9232

ሥርዓት ያልያዘው የጠበል ጥምቀት (ከይኄይስ እውነቱ)

የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በጠበል ጥምቀት ከሚገኘው ፈውስ ጋር ተያየዞ በየጠበል መጠመቂያ ቦታዎች የሚታየውን አንዳንድ ከሥርዓት የወጣ አፈጻጸም ሥርዓት እንዲይዝ ያደርጉ ዘንድ በየደረጃው ላሉ የኢኦተቤ/ክ. አስተዳደር አካላት (የቤተክርስቲያኒቱ አካል የሆነውን ማኅበረ ቅዱሳንን ጨምሮ) ሥርዓት እንዲይዝ ያደርጉ ዘንድ መልእክት ለማስተላለፍ ነው፡፡

የወያኔ ትግሬ አገዛዝ በአገራችን ከፈጠራቸው ማኅበራዊ ቀውሶች ዋንኛው በሃይማኖት ጉዳይ በቀጥታ ጣልቃ በመግባት በተለይም በኢኦተቤ/ክ. ባሠማራቸው ካድሬዎቹ አማካይነት ቤተክርስቲያኒቱን የፖለቲካ መሣሪያና የዝርፊያ ምንጭ ማድረጉ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ለእግዚአብሔርም፣ የህልውናዋ መሠረት ለሆኑትም ምእመናን ተጠያቂ አስተዳደር ባይኖራትም ልዑል አምላክ አገርንም ሆነ ቤተክርስቲያንን አለ ምስክር አይተዋቸውምና፤ እግዚአብሔርን የሚፈሩ፣ ስለመንጋው የሚጨነቁ አገልጋዮች ጥቂትም ቢሆኑ አይታጡምና መልእክቴ በዋናነት ለቤ/ክ. ተቈርቋሪ ካህናት አባቶችና ወንድሞች እንዲሁም ምእመናን ይሆናል፡፡

መግቢያ

ታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ› በሚለው መጽሐፋቸው ጠበልን የጥምቀት ውሃ÷ የተባረከ÷ የተጸለየበት ወይም በታምራት የፈለቀ÷ ከደዌ የሚያድን የሚፈውስ በማለት ይተረጕሙታል፡፡

የኢኦተቤ/ክ ካሏት መንፈሳዊ ሀብቶች አንዱ በጠበል አማካይነት የሚገኘው ፈውስ ነው፡፡ በዚህም የቤተክርስቲያኑ አማንያን ብቻ ሳይሆኑ ሙስሊም ወገኖቻችን፣ እንዲሁም ባዕዳን ጭምር ባሕር አቋርጠው ከደዌ ሥጋ ደዌ ነፍስ ተፈውሰው ድኅነተ ሥጋ ድኅነተ ነፍስ ያገኙባት፤ አሁንም ይኸው መንፈሳዊ አገልግሎት የሚሰጥባት የቤተሳይዳ አምሳል የሕሙማን መጠጊያ ነች፡፡ ይህ ለዘመናት የዘለቀው አገልግሎት የኢኦተቤ/ክርስቲያንን ዘመናዊ ሕክምና ባልነበረበት፣ ባልተስፋፋበት እና አሁንም ለአብዛኛው ሕዝብ ባልተዳረሰበትና ባቅምም ምክንያት ተደራሽ ባልሆነበት አገራችን የ‹ጤና ጥበቃ› ሚናን ስትወጣ ቆይታለች፤ አሁንም እየተወጣች ነው፡፡ በጠበል የሚገኘው ፈውስ ሊቃውንተ ቤ/ክርስቲያን በጥበብ መንፈሳዊ ሰፍረው÷ ቈጥረው÷መዝግበው ካቆዩልን ለልዩ ልዩ ደዌያት ፈውስነት የሚያገለግሉ ዕፅዋትና ቅዱሳን በኪደተ እግራቸው የባረኩት ጸበል (ብናኝ÷ትቢያ÷ዐቧራ÷ደቃቅ ዐፈር) እንዲሁም በጸሎተ ቅዳሴ አማካይነት የሚከብረው ‹ዕመት› መድኃኒትነት እንደተጠበቀ ሆኖ ነው፡፡

ኑሮአቸውን ከእግዚአብሔር ጋር አንድ ያደረጉ ቅዱሳን ፃድቃን ሰማዕታት እንደ ገድላቸውና ትሩፋታቸው መጠን የልዩ ልዩ ቃል ኪዳናት ባለቤቶች ናቸው፡፡ ቤ/ክ ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት አድርጋ ለእነዚህ ቅዱሳን ለስማቸው መታሰቢያነትና በተገባላቸውም ቃል ኪዳን ምእመናን ይጠቀሙ ዘንድ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች፣ በአድባራትና ገዳማት በጠበል የሚፈጸሙ የፈውስ ቦታዎች በስማቸው ተሰይመው እናገኛለን፡፡ ምእመናንም ልባቸው በወደደው/ፈቀደው ቅዱሳን መታሰቢያነት በተሰየሙ ቅዱሳን መካናት በመሄድ አገልግሎቱን ያገኛሉ፡፡ የጠበል መፈወስ ምሥጢር የእግዚአብሔር ኃይል ወይም መንፈስ የተዋሐደው መሆኑ ነው፡፡

 

  • የጠበል ዓይነት፤

 

በጽሑፉ መግቢያ በተቀመጠው የጠበል ትርጓሜ መሠረት ለፈውስ የምንገለገልበት ጠበል ሁለት ዓይነት ገጽታ አለው፡፡

1.1 በተፈጥሮ በተአምራት የፈለቀ ጠበል፣ እና

1.2 የድጋም ጠበል (ቅዱሳትና አዋልድ መጻሕፍትን በጸሎት በማድረስ የሚዘጋጅ ጠበል)

 

  • የጠበል አገልግሎት የሚሰጥባቸው ቦታዎች

 

በኢኦተቤ/ክ. ሥርዓት መሠረት በጠበል አማካይነት የሚሰጥ የማጥመቅ አገልግሎት የሚፈጸምባቸው ቦታዎች በከተማና በገጠር በሚገኙ አድባራትና (አብያተ ክርስቲያናት) እና ገዳማት እንዲሁም በነዚሁ ሥር በሚተዳደሩ ቤ/ክ. እውቅና በሰጠቻቸው መካናት ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በቤ/ክ. ስም በየመንደሩ ቆብ አጥልቀው፣ ሻሽ ጠምጥመው፣ ካባ ደርበው፣ አንዳንዶችም መስቀል ይዘው እናጠምቃለን/እንፈውሳለን የሚሉ ሐሳውያን አጥማቅያንን ቤ/ክ አታውቃቸውም፡፡ ከሥርዓት የወጣ ነው፡፡ በተለይም በገንዘብ የማይተመነውን መንፈሳዊ ሀብት እንደ ዓለማዊ ሸቀጥ ገንዘብ በማስከፈል እናጠምቃለን የሚሉ ግለሰቦች ዝርፊያ ላይ የተሠማሩ ቀማኞች በመሆናቸው በየተዋረዱ ያሉ የኢኦተቤ/ክ. አስተዳደር አካላት በስሟ የሚነግዱ ሕገወጦችን ሥርዓት በማስያዝ ምእመናንን በነፍስ በሥጋ ከሚደርስባቸው ጉዳት መታደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በጠበል ማጥመቅ ሥርዓት ዙሪያ ትምህርት መስጠት ብዙም የተለመደ ስለማይመስል፣ መምህራነ ቤ/ክ. እና ሰባክያነ ወንጌል ለተጠማቂ ምእመናን፣ ለአጥማቅያን እንዲሁም በመካነ ጥምቀቶች ተጓዳኝ የድጋፍ አገልግሎት ለሚሰጡ ኹሉ ሠፋ ያለ ትምህርት በመስጠት አገልግሎቱን በእውቀት ማገዝና ሥርዓት ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

  • የጠበል አገልግሎት ተጠቃሚ ምእመናን (ተጠባዮች)

 

ቅዱሳት መጻሕፍትን መሠረት ባደረገው የኢኦተቤ/ክ. አስተምሕሮ ደዌያት በሙሉ (ግዙፉ/አካላዊው፤ ረቂቁ/የመንፈስ ኹከት) አጋንንት ናቸው፡፡ አጋንንት የሚወጡት ደግሞ በጾም፣ በጸሎት፤ የእግዚአብሔር ኃይል በሚገለጽባቸው በመስቀል፣ በጠበል/በጸበል ነው፡፡

በጠበል ለመጠመቅ ወደ ተለያዩ አድባራት፣ ገዳማትና ቅዱሳት መካናት የሚሄዱ የኢኦተቤ/ክ ክርስቲያኖች ሲሆኑ፣ ብዛታቸውን በውል መግለጽ ባይቻልም ከተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ውጭ ያሉ ሕሙማን ፈውስ ፍለጋ መምጣታቸው እንግዳ ነገር አይደለም፡፡

  1. ከተጠባይ ክርስቲያኖች የሚጠበቁ ዝግጅቶች

4.1/ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት

በጠበል የሚገኝ ፈውስ መንፈሳዊ እስከሆነ ድረስ ለድኅነት ዋና መሠረቱ እምነት ነው፡፡ ትርጓሜ ወንጌል እንደሚነግረንና ሊቃውንተ ቤ/ክርስቲያን እንደሚያስተምሩን የሰናፍጭ ፍሬ/ቅንጣት እጅግ ትንሽ ብትሆንም ነቅዕ (ስንጥቅ/ክፍተት) የለባትም፡፡ በዚህም ምክንያት ጥርጣሬ ለሌለበት ምሉዕ እምነት ምሳሌ ሆናለች፡፡

በጠበል ፈውስ የሚሻ ታማሚ ምእመን ጥርጥር ከሌለው እምነት ጋር ይሆንልኛል ይደረግልኛል ብሎ በፍጹም እምነት መቅረብ የሚሻውን ፈውስ ያስገኝለታል፡፡

4.2/ አፍኣዊ ንጽሕና፤ ሰውነትን ታጥቦ ንጹሕ ሆኖ ከመቅረብ ጋር ፀዐዳ ኀፍረትን መሸፈኛ የውስጥ ልብስ ማድረግ፡፡ ደዌው/ሕማሙ ከሴቶች ግዳጅ ጋር ወይም ከወንዱ ርስሐት (ማደፍ) ጋር የተያያዘ ካልሆነ በቀር፣ ሴቶች ከወርኀዊው ልማድ ነፃ የሆኑበትን ጊዜ ጠብቆ መቅረብ፡፡ ወንዶች ራስን ከሕልመ ሌሊት/ዝንየት ጠብቆ መቅረብ፡፡

4.3/ ውሳጣዊ ንጽሕና፤ በማወቅም ሆነ አለ እውቀት ስለተሠራ ኀጢአት ከልብ በመጸጸት ንስሓ መግባት፡፡ ለዚህም ካህን (የነፍስ አባት) ጋር ቀርቦ ተናዝዞ እና በካህኑ የሚሰጠውን ቀኖና ፈጽሞ መቅረብ፡፡

  1. የጠበል አጠማመቅ በተግባር

5.1/ ካህናት አባቶች የሚመሩት የማጥመቅ/ፈውስ ሥርዓት

   ጠበል በራሱ የመፈወስ ኃይሉ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ሥልጣነ ክህነት ያለው ሕጋዊ ቄስ ወይም መነኮስ ጸሎት በማድረስና በመስቀል በመዳሰስ የሚከናወን የጠበል ማጥመቅ ሥርዓት አንዱ ሲሆን፣ ይህም የድጋም ጠበል ባለበትና ባብዛኛው የፈለቁ ጠበሎች ባሉበት ቦታም ይከናወናል፡፡

5.2/ አጥማቂ ካህን በሌለበት የሚፈጸም ጥምቀት

    ሕሙማን ምእመናን በአስታማሚዎቻቸው ወይም የመራዳቱን አገልግሎት በክፍያ ወይም በፈቃደኝነት በሚሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች ወይም ከደዌያቸው ተፈውሰውና ብጽአት ገብተው በቦታው ለማገልግል ፈቃደኞች አማካይነት ወደ ጠበሉ ቀርበው የሚጠመቁበት ሁኔታ ነው፡፡ በዚህ በሁለተኛው ጥምቀት አፈጻጸም ረገድ ወረድ ብዬ የምገልጻቸው ፈተናዎች ስላሉ፣ አቅም እስከፈቀደና እስከተቻለ ድረስ በኹሉም የጠበል መጠመቂያ ቦታዎች ቤ/ክርስቲያን ክህነት የሰጠቻቸውና የምታውቃቸው ካህናት አባቶች በቋሚነት መድቦ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

  1. በጠበል መጠመቂያ ሥፍራዎች የሚስተዋሉ ከሥርዓት የወጡ ድርጊቶች

6.1/ ጠበልተኞችን ‹በሚራዱ› ግለሰቦች የሚታይ የኃይል ተግባር

        ጠበል ለመጠመቅ በየማጥመቂያ መካናቱ የሚሄዱ ምእመናን አብዛኛዎቹ በደዌ ሥጋ በደዌ ነፍስ የተያዙ፣ በአካልም በነፍስም የተጎዱ በመሆናቸው ክብካቤ ያስፈልጋቸዋል፡፡ በእምነት እንደምንቀበለው ምክንያተ ፈውሱ በጸሎቱ፣ በመስቀሉ እና በጠበሉ ያለው የእግዚአብሔር ኃይል እስከሆነ ድረስ በኃይል/በዱላ መጠቀም እንኳን መንፈሳዊው ሥፍራ በየትም ቦታ ተገቢ አይደለም፡፡ በርግጥ አንዳንድ ሕሙማን ኃይል በመጠቀም ወደጠበሉ ላለመቅረብ (በመወራጨትና በመንፈራገጥ) የሚያስቸግሩ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ እነዚህን ሕሙማን በሚመለከት ከአባቶች ወይም ሕሙማኑን ለማስታመም አብረዋቸው ካሉ ዘመዶቻቸው ጋር በመመካከር ለዚሁ አገልግሎት  የተሠማሩትንና በአካል ጠንከር ያሉትን መርጦ በመተጋገዝ ዱላ/ድብደባ ሳይጠቀሙ ሕሙማኑን ወደጠበል ማድረስ ያስፈልጋል፡፡ ተቸግሮ እግዚአብሔር ደጅ የወደቀን ሕመምተኛ ማሰቃየት ከክርስትናው የወጣ ሥነ ምግባር ብቻ ሳይሆን በሕማም ላይ ሕማም መጨመር ነው፡፡ ስለሆነም የጠበል ጥምቀት በሚፈጸምባቸው መካናት ኹሉ በቅርብ ከሚገኙት አድባራትና ገዳማት አስተዳደሮች ጀምሮ በየዕርከኑ የሚገኙ የቤተክህነት አካላት ይህን ሕገ እግዚአብሔርንና ሥርዓተ ቤ/ክርስቲያንን የሚቃረን ድርጊት ሥርዓት ማስያዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ጠበልተኛ ምእመንና እነርሱን ለመራዳት በየጠበሉ የሚገኙ ግለሰቦችን በማስተማርና ለእገዛ በቋሚነት የሚገኙ ግለሰቦችን ማንነት መለየትና መዝግቦ መያዝ ተገቢ ይመስለኛል፡፡

6.2/ ሕሙማን ምእመናንን ዕርቃናቸውን እንዲቀርቡ ማስገደድ

        ከከተማ ወጣ ባሉ የማጥመቂያ ቦታዎች ወንድና ሴትን ከመለየት ውጭ ባብዛኛው በጅምላና ዕርቃን በመሆን የሚፈጸም ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ከሕመማቸው ለመፈወስና በረከት ለማግኘት ወደየጠበል ቦታው የሚሄዱ ክርስቲያኖች በሚያዩት (እንደ መንጋ የመተራመስ ትእይንት) ሁኔታ በእጅጉ በመደናገጥ ሳይጠመቁ የሚመለሱት ቊጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ካህናት አባቶች ባሉበትና የማጥመቁ ሥርዓት አንድ ላንድ የሚፈጸም ሲሆን ዕርቃንን መቅረቡ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላል፡፡ በዘመናዊው ሕክምናም ይህንን እንፈጽማለንና፡፡ የተዋሕዶን መሠረተ እምነት (ዶግማ) እና ሥርዓት በመጠኑም እንኳ የማያውቁ፣ ሕመምተኞችን ለማገዝ የተሠማሩ÷ ራሳቸውን የሾሙ ‹‹ጨዋዎች›› በስሚ ስሚ ወይም በራስ ፈጠራ የቦታው ወይም የቅዱሳኑ ቃል ኪዳን ይህንን ወይም ያንን አይፈቅድም እያሉ ‹ሕግ አውጭዎች› እና ‹ሥርዓት ደንጋጊዎች› ሆነዋል፡፡ አልፎ ተርፎም በብዙ ድካምና ውጣ ውረድ የመጡ ታማሚ ምእመናንን ዕርቃናችሁን ካልገባችሁ አትጠመቁም (ተራ ሲጠብቁም መጠባበቂያ ልብስ አትለብሱም) እያሉ ክፉ ከመናገር ጀምሮ ለዱላ የሚጋበዙ ጉልበተኞችን ሥርዓት ማስያዝ ያስፈልጋል፡፡ አንዳንዶችም ጤነኛ ለመሆናቸው ምንም ዋስትና የለም፡፡

   ለሕሙማን ክርስቲያኖች ተገቢውን ክብር ልንሰጥ ይገባል፡፡ እነዚህ ወገኖቻችን ከደዌያቸው ተፈውሰው ነገ ለአገር ለወገን የሚጠቅሙ አለኝታዎቻችን መሆናቸውን መዘንጋት የለብንም፡፡ ተጨንቆ የመጣን ሕሙም ኀፍረትሕን ካልገለጥህ አገልግሎት አታገኝም በማለት ክቡሩን የሰው ልጅ ማሸማቀቅ ክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር አይደለም፡፡ ባይሆን ኀፍረትን መሸፈኛ የውስጥ ልብሳችንን በዚህ ጽሑፍ ቊጥር 4.2 እንደገለጽነው ንጹሕ አድርገን (ከተቻለም ቅያሪ ይዘን) መቅረብ ተገቢ ነው፡፡

Filed in: Amharic