>

ግን ግን ይቺ "...አገር ትፈርሳለች" የምትለው ያረጠች ማስፈራሪያ አላስደሰተችኝም!??! (ዳንኤል ተፈራ)

…. እሁድን በበቀለ ገርባ ስንወዛገብ አሳለፍነው፡፡ እረጅሙ እሁድ ላፍ ነው ያለው፡፡ አቶ በቀለ ገርባ ሰጠው የተባለው አወዛጋቢ እና ብዙ የፖለቲካ ነጥብ የሌለው አስተያት ላይ ሁለት አይነት አስተያየቶችን ለማስተዋል ችያለሁ፡፡
1. ጋሽ በቀለ እማ እንደዚህ አይነት ዝቅ ያለና የወረደ አስተያየት አይሰጥም የሚሉ፤
 2. በቀለ ገርባ ከዚህ በፊት ሲያራምድ የነበረውን ነው ያራመደው እንጂ አዲስ ነገር የለም የሚሉ ናቸው፡፡
ነገርዮውን ስንመረምር ሦስተኛ ነጥብ አይጠፋም፡፡ ጋሽ በቀለ በኦዴግ እና ሌንጮ ለታ ተበሳጭቷል፡፡ የፖለቲካውን ሚዛን እነ ሌንጮ ከነበቀለ ገርባ ነጥቀው ዋና ተደራዳሪ ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ህዝቡን እንዴ! የምታስብል ካርድ መምዘዝ እና የተኛ የሚመስለውን ብሔርተኝነት መቀስቀስ አስቦ መሰለኝ፡፡ ግን ግን ይቺ አገር ትፈርሳለች የምትለው ያረጠች ማስፈራሪያ አላስደሰተኝም፡፡
ይልቅስ የሁለት ወሯ የአብይ ፖለቲካ መሳጭ ነች፡፡ ፖለቲካ ሲመስጥ እስቲ አስቡት!! ያው እንዳክተሩ ነው፡፡ እንደ ፖለቲካው ተጨዋች፡፡ የሀይለማሪያም የ‹‹ራዕይ አስቀጣይነት›› ፖለቲካ አስጠሊታ ነበር፡፡ ምንም ህይወት የሌለው ነበር፡፡ አስቀያሚ ነበር፡፡ ራቁት ነበር፡፡ ገና ኃይሌ ፈገግ ብሎ(ያው ሃይሌ ፈገግታው ያምራል የሚሉ አሉ ሃሃ) ‹‹እሳቸው የጀመሩትን ራዕይ…›› ሲል ‹‹ቀይሩት፣ ቀይሩት›› ይላል አባወራ…. ልጅ ሆየ ፈጠን ብሎ ወደ ቃና፡፡ ኢቲቪ እንኩዋን ቀን ከወጣለት ሁለት ወር አለፈው፡፡
ታዲያ አሁን ምን ተገኘ? …. ምንም አይባልም፡፡ የሆነ ነገር እማ አለው፡፡ በቅንነት እንመልከተው ከተባለ በ2 ወር ብቻ ለታሪክ የሚበቃ ስራ የከወነ መሪ ዶ/ር አብይ አህመድ ነው፡፡ ጊዜውን እና ሁኔታዎችን በአግባቡ ይጠቀማል፡፡ ተጋፊነቱም ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ቀላል ይጋፋል እንዴ! ‹‹በፈረሰ ሃገር ካለ ጀኔራል፣ ሀገር ያለው አስር አለቃ ይሻላል!›› ጀኔራል ሳሞራ የኑስ በትክክል ነው አስተያየት ጠሚውን ሲመለከት ነበር፡፡
በእርግጥስ ግርምታችንን ከፍ ያደረገው ምንድን ነው?
እውነታው በፖለቲካ ባህላችን ውስጥ እድሉን ያገኙ ገዥዎች ህዝቡ ጫንቃ ላይ እግራቸውን ጭነው በማንቀጥቀጥ ሲገዙ ስለኖሩ ነው፡፡ አብይ ይህንን ቀንብር ሊሰብርልን እየሞከረ መሰለኝ፡፡ ፖለቲካችንም ቢሆን የገዳይና ተገዳይ፤ የአሳሪና ታሳሪ፤ የአሰዳጅና ተሰዳጅ ነው፡፡ በፖለቲካችን ውስጥ የተለየ ሃሳብ ያለውን ጠላት ብለው ሲፈርጁ በኩራት ነው፡፡ በመፈረጅ ብቻ አያበቁም መጥፋት አለበት ብለው ያምናሉ፡፡ ተፈትቶ፣ ተፈትቶ… አላልቅ ያለው እስረኛ ብዛት አስልተው እና አስበው፣ አስበው እነ መለስ የደረሱበት የጠላትና ወዳጅ ፖለቲካቸው ውጤት ነው፡፡
ኢህአዴግ አሁን እያየን ያለነውን ለውጥ ያመጣው በፍላጎቱ አይደለም፡፡ ፈልጎም አያውቅም፡፡ የእነሱ ፍላጎትማ ተጨማሪ ማሰሪያ ቤቶችን መገንባት ነበር፡፡ ህዝቡ ግን ይህ ይሆን ዘንድ አልፈቀደም፡፡ ቄሮው እና ፋኖው መፈናፈኛ ሲያሳጣቸው፤ ወጣቱ ሞት የማይፈራ መሆኑንና ከአፈሙዝ ፊትለፊት ለመቆም የማይሰስት መሆኑን ሲያዩ ደንግጠው ፖለቲካ ማሻሻያ እንደሚያደርጉ ፍንጭ አሳዩ፡፡ በዚህ መሃልም ከውስጣቸው የድርጅታቸውን አካሄድ የተጠየፉ እና የነቀፉ ተራማጆች ተፈጠሩ (ቲም ለማ፣ በአድር ባዮች የተከበቡት ገዱና ንጉሱን መጥቀስ ቻላል) የህዝብ ቁጣ ጉልበት ሆኗቸው የሆነው ሁሉ ሆነና ዶ/ር አብይ ወደ ጠቅላይነት መጣ፡፡
የአብይ ብቃት፤ ድፍረትና እንኩሮውን የሀገሬ ፖለቲካ መልክ ለማስያዝ እያደረገ ያለው ጥረት ቀላል ግምት የሚሰጠው አይደለም፡፡ ይህንን ተስፋ ወደ ተጨባጭ እውነት መቀየር ዳር ሆኖ ከመተቸት እና ከማጣጣል የተሻለ ነው፡፡ አቃቂር ማውጣት ፖለቲካ አይደለም፡፡ ፖለቲካ የሚሆነው ከአብይ ተስፋ ተነስቶ የተሻለ አማራጭ ሃሳብ ማቅረብ ነው፡፡ የለውጡን ተስፋ በአግባቡ በመጠቀም የአብይ ብቻ ዕዳ ሳይሆን ተቃዋሚው ትከሻ ላይ የወደቀም ነው፡፡
ሰውየው መንገዱን ለማስተካከል የቆረጠ ይመስላል፡፡ ጀኔራል ሳሞራ የኑስን ፊት ለፊት አስቀምጦ ‹‹ለአይቀሬው ለውጥ ተዘጋጁ›› ሽማግሌዎቹን ‹‹ስራ ፈለግላችኋል እና አላስራችሁም›› ብሏል፡፡ የለውጡ ባቡር ፈጣን ይመስላል፡፡ ስለዚህ ከአቃቂረኝነት ተመልሰን ቢያንስ ለልጆቻችን የሚሆን ስርዓት መገንባቱ ላይ እናተኩር ለማለት ነው፡፡ የተቋማት ጉዳይ እንዳይዘነጋ ዋናው መልዕክቴ ነው፡፡
ዜጎችን ከቀያቸው የሚያፈናቅሉትን ግን ጊዜ ወስደው ቶሎ መፍትሄ ይስጡት፡
Filed in: Amharic