>
5:33 pm - Monday December 5, 1374

በማንነታቸው ከሰራዊቱ የተባረሩ አማራ ጀኔራሎች (በላይ ማናዬ)

በአስር አመት ውስጥ ከ13 በላይ ጀኔራሎች፣ ከ45 በላይ ኮረኔሎች፣ ከ250 በላይ ሻለቆች  ከ21 ሺህ በላይ ከመስመራዊ መኮንን እስከ ተራ ወታደር ብሔራቸው አማራ ስለሆኑ ተባርረዋል። ከዛ በፊት 20 ሺህ ወታደሮች ተባርረዋል።  በአጠቃላይ ከ41 ሺህ በላይ የአማራ ተወላጆች ከሰራዊቱ ተባረዋል።
1)  ብ/ ጀኔራል ተፈራ ማሞ
በተለያዩ የውጊያ ቦታዎች ላይ ሰራዊቱን መርቶ ተዋግቷል፣ ሰራዊቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመሪነት ቦታ የሚያየው ሰው ነው። ጀኔራል  ተፈራ የህወሃት የበላይነትን ከበረሃ ጀምሮ  በመታገሉ “ነፍጠኛ፣ ትምክተኛ፣ ፊውዳል”  እየተባሉ ፍረጃ ሲሰጣቸው ከነበሩት መካከል ቀዳሚው ነው።
ከ1998 ጀምሮ አማሮች ከሰራዊቱ በማንነታቸው ሰበብ እየተፈለገ “በዲሲፕሊን” እየተባሉ ሲባረሩ  ጀኔራል ተፈራ “በዲስፕሊን አይደለም”  ብሎ ተከራክሯል።  ከሰራዊቱ ለተባረሩት ድጋፍ ደብዳቤ በመፃፉ፣ በግምገማ ወቅት ስለህወሓት ጀኔራሎች ሙስና በመናገሩ ጥርስ ውስጥ ገብቷል።
የአማራ ተወላጅ የሆኑ የሰራዊት አባላት “ጀኔራል ተፈራ፣ ከጀኔራል ኃይሌ ጥላሁን ጋር ሆኖ መለስ ዜናዊን ለማስገደል እያሴረ ነው” ብለው በሀሰት እንዲመሰክሩበት ተገድደው በሀሰት አንመሰክርም  በማለታቸው ከእስር ተርፎ ነበር። በመጨረሻም በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ክስ እድሜ ልክ ተፈርዶበት 9 አመት ታስሮ በቅርቡ ተፈትቷል። ብ/ጀ ተፈራ ማሞ  ከሙስና የፀዳ በመሆኑ በሰራዊት  ዘንድ “ድሃው ጀኔራል”  በመባል ይታወቃል።
2) ብ/ጀኔራል አሳምነው ፅጌ
~”ትምህርት ቤቱ ይፈርሳል እንጂ አማራ አይማርበትም”  ጀኔራል ሳሞራ የኑስ
አሳምነው የላስታ ወረዳ አስተዳዳሪ ነበር። ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በኋላ የጀኔራልነት ማዕረግ አግኝቷል። የህወሃት የበላይነት በሰራዊቱ ውስጥ መኖሩን በመረጃ በመሞገት ሀረር በተደረገ 1993 መድረክ ላይ በመድረኩ ተሳታፊዎች ስምምነት እንዲደረስ አድርጓል።
ብ/ጀኔራል አሳምነው አሜሪካ ሀገር ለአንድ አመት ወታደራዊ ትምህርት ተምሯል። በ1997 ሀገራዊ ምርጫ ጊዜ “ቅንጅት ነው” ተብሎ ተፈርጆ ነበር።
አሳምነው መከላከያ ዩኒቨርሲቲን በብቃት መርቷል። ሆኖም ተቋሙን በሚመራበት ወቅት የህወሓት ሰዎች “አሳምነው አሜሪካ ሄዶ ያመጣው ነገር አለ” በሚል ያዋክቡት ነበር። አሳምነው ወደ መከላከያ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች (ወታደሮች) በፈተና እንዲገቡ በማድረጉ ጥርስ ውስጥ ገብቷል። በፈተናውም ብዙ የአማራ ልጆች በማለፋቸው የበለጠ አሳምነው ከህወሓት ሰዎች ጋር ተካረረ። እንዴት ብዙ አማራዎች ፈተናውን ሊያልፉ ቻሉ በሚል ሲጠየቅ አሳምነው ለእነ ጀኔራል ሳሞራ “ውጤቱን ካላመናችሁ ፈተናውን ራሳችሁ አውጥታችሁ ፈትኗቸው” ብሏቸዋል። እንዲያውም ጀኔራል ሳሞራ የኑስ “እንዲህማ አይሆንም፣ ትምህርት ቤቱ ይፈርሳል እንጂ አማራ አይማርበትም” እስከማለት ደርሶ ነበር።
ጉዳዩ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደርሶ በመጨረሻ በወታደራዊ ትምህርት ቤቱ የተነሳው መካረር አድጎ ጀኔራል አሳምነው እንዲታገድ ተደርጎ አለፎም እጂጉ የሚባል የህወሓት ሰው ሲተካ ዩኒቨርሲቲው ማስተማሩን ቀጠለ።
ጀኔራል አሳምነው ፅጌን ከሰራዊቱ ሲያባርሩት ማዕረጉን አንስተው ነበር። ጀኔራሉ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ክስ እድሜ ልክ ተፈርዶበት በቅርቡ ከ9 አመታት እስር በኋላ ተፈትቷል።
3) ጀኔራል  ኃይሌ ጥላሁን 
~”ከበደ  እናገመቹ የት ሄዱ? ሀጎስና ገብረክርስቶስ በዙ!”
ኢህአፓ አሲምባ ላይ ጦር ሲመሰርት አባል ነበር። አየር ኃይል አዛዥ ሆኖም ሰርቷል።  ባህርዳር ላይ በነበረውና ኃይሌ በመራው የሰራዊት ኮንፈረንስ የህወሓት የበላይነት አለ የሚለው ላይ መተማመን ላይ ተደርሷል። የህወሓት ሰራዊት አባላት የህወሓት  የበላይነት አለ በመባሉ መድረክ ረግጠው ሲሄዱ “ለትግራይ ሕዝብ ቆምን ትላላችሁ እንጅ የትግይራ ህዝብ የብብት ቅማል ናችሁ” በማለቱ በህወሓት የሰራዊት አባላት ተጠምዷል። በህወሓት ትእዛዝ ኮንፈረንሱ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
 ለማዕረግ የታጩ ወታደሮችን ስም ዝርዝር አይቶ “ከበደ  እናገመቹ የት ሄዱ? ሀጎስና ገብረክርስቶስ በዙ!” በማለቱ በህወሓት የጦር ሰራዊት አባላት ጋር የከረረ ጠብ ውስጥ ገብቷል። የአማራ ተወላጅ የሆኑ ሁለት የሰራዊቱ አባላት ጀኔራል ተፈራ ማሞ ጋር በመሆን አቶ መለስ ዜናዊን ለማስገደል ሙከራ አድርጓል ብለው በሀሰት እንዲመሰክሩበት ቢገደዱም  በሀሰት አንመሰክርም ብለው ሳይመሰክሩበት ቀርተዋል።
ጀኔራል ኃይሌ””የኢህአፓ ርዝራዥ” የሚል ስም ተሰጥቶት  በኋላ ቤቱን ቀምተው፣ ጥቅማጥቅሙን ነጠቁት። ጦር ሀይሎች ትሰራ ከነበረችው ሀኪም ባለቤቱ  ጋር በተመሳሳይ ቀን ከስራ አባረውታል። ሰብዕናውን ከገደሉ በኋላ ሰላም አስከባሪ ልከውት መሞቱ ተሰምቷል።
4) ጀኔራል  ተመስገን አበበ
 የተሻለ ትምህርት  አላቸው ከሚባሉት ጀኔራሎች መካከል አንዱ ነው። በእድሜም ወጣት ጀኔራል ሲሆን  ወታደራዊ ኢንዶክትርኔሽን ውስጥ ሰርቷል። የምዕራብ እዝ አስተዳደር ኃላፊ ነበር። ቅንጅት ተብሎ ከተባረሩት መካከል ነው። ጀኔራል አብርሃ ወ/ማርያም (ኳርተር) ግምገማ ላይ “አንተ ቅንጅት ነህ” ብሎ በግልፅ ነግሮታል።
5) ጀኔራል ባዬ ወንድአፍራሽ
~ስዬና ፃድቃን ጨምሮ ሰራዊቱን ወታደራዊ ሳይንስ ያስተማረ
በደርግ ዘመን ሩሲያ አምስት አመት ወታደራዊ ሳይንስ ተምሯል።  እነ ስዬ እና ፃድቃንን ጨምሮ ጦሩን ካርታ ገለፃ ያስተማረ ነው። የምስራቅ አፍሪካ ብርጌድ አዛዥ ነበር። የመከላከያ ስታፍ ስልጠና ክፍል ነበር። የወታደራዊ ሳይንስ ኤክስፐርት ነው። በማንነቱ ምክንያት ከሰራዊቱ ተባርሯል።
6) ጀኔራል ምስጋናው አለሙ
– ህክምና ተነፈጎ ከሰራዊቱ የተገፋው ጄኔራል!
ጀኔራል ምስጋናው ከ1974 ጀምሮ የታገለ፣ የክፍለ ጦር አዛዥ ነበር። ጄኔራል ምስጋናው አለሙ አሁን ላይ በቂ ህክምና አጥቶ ህመም ላይ ይገኛል። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ባድሜ ግንባር ተሰልፎ ተዋግቷል።
ጀኔራል ምስጋናው አለሙ በማንነቱ ምክንያት ከሰራዊቱ ተገፍቶ እንዲወጣ ተደርጓል።
7) ጀኔራል ወንዶሰን ተካ
ከሰራዊቱ ከተባረሩት የአማራ ተወላጅ ጀኔራሎች መካከል ወጣቱ ነው። በምስራቅ እዝ ስር የምትገኘው 32ኛ ክፍለ ጦር መሪ ነበር። በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ቡሬ ግንባር 39ኛ ክ/ጦር አዋግቶ ጥሩ ድል ያስመዘገበ፣  ሞቃድሾ ጦር የመራ ጀኔራል ነው። በመፈንቅለ መንግስት ተጠርጥረው  ከታሰሩት ከእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ ጋር ግንኙነት አለህ ተብሎ ከሰራዊቱ ተባርሯል።
8)ጀኔራል ስዩም ሀጎስ
“አማራ ነኝ!” ጀኔራል ስዩም
 ጀኔራል ስዩም የምዕራብ እዝ አዛዥ ሆኖ ሰርቷል። መጀመርያ የህወሓት ታጋይ የነበር ሲሆን “አማራ ነኝ” ብሎ ኢህዴንን ተቀላቀለ። ስዩም ትውልዱ ኮረም ሲሆን የህወሓት ሰዎች አማራ ነኝ ስለሚል ቤተሰቦቹ ድረስ ሄደው አነጋግረዋል። እነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተጠርጥረው ከታሰሩ በኋላ ግንኙነት አለህ ተብሎ ተባርሯል።
9) ሌ/ጀኔራል አበባው ታደሰ
ሌ/ጀኔራል አበበው ታደሰ የማዕከላዊ ዕዝ አዛዥ ነበር። በወታደራዊ አሰራር በማዕረጉ ከጀኔራል ሳሞራ ቀጥሎ “ሲኒየር” በመሆኑ ቀጣዩ ኢታማዦር ሹም ሊሆን ይችል ነበር። ጀኔራል አበባው ጀኔራልነት ማዕረግን ሲያገኝ በእድሜ ትንሹ ጀኔራል ነበር። አበባው በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት ባድመ ግንባር 108ኛ ጦርነት እየመራ ጀብድ ፈፅሟል።
ሌ/ጀኔራል አበባው በ2006 ዓም ከመከላከያ ሰራዊት ተባርሯል። አበባው በህዝብ ላይ የሚፈፀመውን በደል በግልፅ የሚቃወምና የህወሓት የበላይነት ላይ ጥያቄ ባያነሳም  ማንነቱ ከመገለል አላዳነውም።
10) ጀኔራል አለሙ አየለ:_
የመከላከያ ስታፍ ሆኖ ሰርቷል። እንደ ሌሎቹ የአማራ ተወላጅ ጀኔራሎች በህወሓት የበላይነት ላይ በግልፅ ተቃውሞ ባያነሳም በማንነቱ ምክንያት ከሰራዊቱ ውጭ ተደርጓል።
11) ጀኔራል አበራ ድኩል:_ 
76 ኢህዴንን የተቀላቀለ፣ የሰሜን እዝ አስተዳደር የነበረ። በማንነቱ ምክንያት ከጦሩ እንዲሰናበት ተደርጓል።
12) ጀኔራል አከለ አሳዬ ጀኔራል:_
ኢትዮ ኤርትራ ጊዜ ኮር አስተዳደር፣ በኋላም ብሄራዊ ተጠባባቂ ኃይል ኃላፊ ነበር፣ ባድሜ ግንባር ተሳትፏል። ገና ወጣት ጀኔራል ነው። በማንነቱ ምክንያት ከሰራዊቱ ተባርሯል።
(ጀኔራሎቹ ከ1997 ዓም በኋላ ከቅንጅት ጋር፣ እንዲሁም ከ2001 ዓም በኋላ ከእነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ ጋር ግንኙነት አላችሁ እየተባሉ ከጦሩ ተባርረዋል)
Filed in: Amharic