>

የበረኸኛው ያሬድ ዘለሳ  (ወሰን ሰገድ ገ/ኪዳን)

ልብ በል “ዘለሰኛ” አላልኩም፡፡ ብትለውም ያስኬዳል፡፡  “ዘለሳ” ነው ያልኩት፡፡
“ዘለሳ” የሚለውን ቃል ከሳቴ ብርሃን ተሰማ አማርኛ መዝገበ ቃላት እንዲህ የሚል ፍቺ ይሰጠዋል፦
.
➊ የወታደር፣ የሰልፈኛ፣ የቀን ግስገሳ፤ የለሊት ዘለሳ ማለት ቀን ሲገሰግስ ውሎ ለሊት ዝልስ ብሎ የሚተኛ፤
➋ ወታደር ፣ ዝልስ ብሎ እየወደቀ የሰልፍ ትምህርት መማር፤
(ከ.ብ.ተ መዝገበ ቃላት ገፅ ፦ ሺህ 14)
.
በረኸኛውም ያሬድ ልክ እንደዛው ነው፡፡  ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያውያን የተሻለ ሕይወት ለማምጣት  በርሃ የገባ ታጋይ ነው፡፡ ሊያውም አሁን የሀገሪቷ የሥልጣን መንበር ከተፈናጠጡት በርኸኞች ጋር፡፡ ለስድስት ዓመት ያህልም አብሮአቸው ነበር፦ እየተፋለመም፣ እየተፋለማቸውም፡፡
.
ነገር ግን አብሮአቸው አልዘለቀም፡፡ ለስደት ተዳረገ።
.
ለስደት ተዳርጎም ባለበት ሆኖ ከመታገል አልታቀበም፦ በብዕር፡፡ የሀገሪቱን የፖለቲካ ሁኔታ እየመዘነ፣ ሕውሐትና ጀሌዎች “እንዲህ ሊያደርጉ ይችላሉ” ቀድም እየተነበየ፤ ሊደረግ የሚገባውን ወይም መደረግ ያለበትን እየጠቆመ መታገሉን ቀጠለ፡፡
.
ለምሳሌ ያህል ከበርሃ የአብሮነት ልምዱ ተነስቶ፣ በሕወሐታውያን ላይ ካስተዋለባቸው ባሕርይ ጋር አስተያይቶ፣ ኢትዮጵያና ኤርትራ ወደ ጦርነት ሊገቡ እንደሚችሉ የተነበው “የኢህአዴግ ጣምራ ባሕርያት ኢትዮጵያ ወዴት?” በሚል ርዕስ ግንቦት 1989 በከተበው ፅሁፉ ነው፡፡ “የተነበየው” አልቀረም በ1992-93 ጦርነት ውስጥ ተዘፈቀን፡፡
.
ሌላ ምሳሌ ልጥቀስልህ፦ ስለ ወልቃይት ጉዳይ የከተበውን፡፡
.
“በ1971 እና በ1972 ዓም  ወልቃይት ውስጥ አርሶ አደሩን በማደራጀት ስራ ላይ ስለተሳተፍኩ በጉዳዩ ላይ ዕውቀት አለኝ። ወልቃይቴ ራሱን በትግሬነት አያይም። ትግሬኛና አማርኛን እኩል ይናገራል፤ በትግርኛና ማልቀስና መዝፈን አይቻለውም” ይልሀል በወታደርነት ወድቆ እየተነሳ ያየውን፣ በፖለቲካ ምሁርነት ጠልቆ ካስተዋለው ጋር እያሰናሰነ፡፡ እናም የወልቃይት ጉዳይ እየከረመ  በሃገሪቷ ፖለቲካ ውስጥ ሌላ ጣጣ ሳያመጣ መፍትሄ ይበጅለት ሲል አብዝቶ ይሟገታል፡፡
.
ትንቢት በሚባል መልኩ ሌላም ሌላም ፖለቲካዊ ጭብጦችን እያነሳ ስለ  “ጋራ ቤታችን” ይጮኻል፡፦ በረኸኛው ያሬድ (በበረሃ ስሙ ጌታቸው)
.
ይህንን የምልህ ያለ ምክንያት አይደለም፡፡  ትናንት በመቶ ሺህ የሀገራችን ልጆች መስዋዕትነት የከፈሉባት ባድመ በይፋ ለኤርትራ እንደምትሰጥ በሰማሁ ጊዜ ያሬድ ጥበቡ አስቀድሞ ሊመጣ ያለውን ነገር ያስጠነነቀንን ወደ ኋላ መለስ ብዬ እንዳስታውስ ስላስገደደኝ ነው፡፡
.
እናም ወዳጄ፦
ያሬድ ጥበቡ የበርካታ ዓመታት ፅሁፎቹን በአንድነት አስጠርዞ ባለፈው ወር ለህትመት ያበቃውን “ወጥቼ አልወጣሁም” መፅሐፍ አንብበው፡፡ (ወደፊት  ሰፋ ያለ ዳሰሰ የመፃፍ ዕቅድ ስላለኝ ነው በአጭሩ የምነግርህ)
ትደመማለህ! ትቆጫለህ!
ሀገራዊ ውድቀታችንን ታይበታለህ!
ወድቆ መነሳትን ትማርበታለህ!
ያለፈውን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን ሀገራዊ ፖለቲካ ትቃኝበታለህ!
አንብበው! “ወጥቼ አልወጣሁም”ን አንብበው!
ታተርፍበታለህ!
Filed in: Amharic