>
5:16 pm - Saturday May 24, 8464

የአሰብና የባድመ ነገር?!? (ፋሲል የኔአለም)

አንዳንድ ሰዎች “ባድመን ለኤርትራ ለመስጠት ከመወሰናችን በፊት አሰብን መደራደሪያ ማድረግ ነበረብን” በማለት ሲቆጩ አያለሁ። በአሰብ ጉዳይ ላይ ከዶ/ር ያዕቆብ ሃ/ማርያም ጋር በእስር ቤት ውስጥ ብዙ እንነጋገር ነበር። ዶ/ር ያዕቆብ አሰብን ማስመለስ የሚቻልበት የህግ እድል አለ ብሎ በጽኑ የሚያምን ሰው ነው። እንደ ዶ/ር ያዕቆብ የጠለቀ የህግ እውቀት ባይኖረኝም፣ በወሰድኳቸው የተወሰኑ አለማቀፍ የህግ ኮርሶች( International Law) ተመርኩዤ እድሉ የተዘጋ መሆኑን  እከራከር ነበር።  እስር ቤት ውስጥ በአለማቀፍ  ህግ ዙሪያ ታዋቂ  ጸሃፊዎች የጻፉዋቸውን መጽሃፎች በማስገባት ጉዳዩን በደንብ ለመመርመር ሙከራ አድርግ ነበር። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአለማቀፍ የህግ ምሁር የሆኑት ( የነበሩት- በህይወት የሉም ሲባል ስምቻለሁ)፣ አቶ ጌታቸው በወቅቱ በባድሜ ጉዳይ ላይ ያሉትን የህግ አማራጮች ከአለማቅፍ ህግ አንጻር እንድንመረምር አዘውን ስለነበር ከጓደኞቼ ጋር መጠነኛ ጥናት ማድረጋችንንም አስታውሳለሁ። በጊዜው የነበረን ትኩረት በማስረጃዎች ተገቢነትና በውሳኔው ላይ በተለይ Badme and its environs ማለት ምን ማለት ነው? እስከየት ነው የሚደርሰው በሚሉት ጉዳዮች ላይ ስለነበር ብዙ ነገሮችን እንድንጠይቅ እድል ሰጥቶን ነበር። ከዚያ በሁዋላ የተፃፉ መጽሃፎችን ለማገላበጥም ሆነ የሚቀርቡ ጥናታዊ ውይይቶችንም ለመካፈል እድሎች ነበሩኝ። ምንም እንኳ እነዚህ አጋጣሚዎች በአሰብም ሆነ በባድሜ ጉዳይ ላይ የህግ አስተያየት ለመስጠት በቂ ናቸው ባልልም፣ አለኝ የለኝም የምለው የእስር ቤት ወዳጄ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ነገር ከጎኔ ሆኖ እነዚያን የእስር አመታት አብሮኝ ያሳለፍነውን  ዶ/ር ያዕቆብን ( ጃክ) መልስ እንዲሰጥበት ለመጎንተል እንዲሁም ሌሎችም የአለማቀፍ ህግ ተማሪዎች  በድፍረቴ ተናደው እንዲጽፉበት  ይችን አጭር ጽሁፍ አቅርቤያለሁ። ደፋርና የህግ እውቀት የሌለኝ ሰው መሆኔን በጽሁፌ ማጠር ብቻ ማረጋገጥ ይቻላል። የህግ ጽሁፎችና መጻፎች ለሸክም የሚያስቸግሩ “ግብዳ” ናቸውና።  በውስን እውቀት ተመስርቼ እንዲህ አይነት የድፍረት ጽሁፍ ለመጻፍ በመነሳቴ ከውግዘት ይልቅ ይቅርታችሁን እንድትለግሱኝም እማጸናለሁ።
 በእኔ እምነት የአሰብ ጉዳይ ያለቀው  ኤርትራ በተገነጠለችበት ወቅት ኢትዮጵያ በጣሊያን ጊዜ የተፈረሙ የድንበር ውሎችን የተቀበለች ጊዜ ነው። ብዙ ሰዎች እንደሚጠቅሱት በ1964 የካይሮ የአፍሪካ አንድነት ስብሰባ የአፍሪካ አገሮች የቅኝ ግዛት ውሎችን ለመቀበል ተስማምተዋል። የተስማሙበትም ዋና ምክንያት በአህጉሪቱ ትርምስ እንዳይፈጠር በማሰብ ነው። ኢትዮጵያም ከሶማሊያ  የቀረበባትን የኦጋዴንን የይገባኛል ጥያቄ ለመቀልበስ በማሰብ ይህን ውሳኔ  ተቀብላ ብዙ ተከራክራበታለች። ይህ ህግ ብዙ የአፍሪካ አገሮች ነጻ ሲወጡ በመካከላቸው ይፈጠር የነበረውን የድንበር ጦርነት ቢቀንሰውም፣ ችግሩን ግን ሙሉ በሙሉ አልቀረፈውም። ተመድም በዚህ ስምምነት መሰረት የቅኝ ግዛት ድንበሮችን አምኖ ተቀብሏል። ኤርትራ ስትገነጠል የቅኝ ግዛት ድንበሮች ተግባራዊ እንዲሆኑ ኢትዮጵያ ተስማምታለች። ብዙዎች ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ውሉን ከመቀበል ውጭ ሌላ አማራጭ አልነበራትም ይላሉ። ይህ ግን ስህተት ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ በሰሜን እና ደቡብ ምስራቅ በኩል ከጣሊያን ጋር፣ በምዕራብ፣ ደቡብና ሰሜን ምስራቅ በኩል ከእንግሊዝና ፈረንሳይ ጋር የድንበር ውል ተፈራርማለች። ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ሱዳን  ነጻ ሲወጡ ከቅኝ ገዢዎች ጋር የተፈረሙትን  ውሎች እንዳለ ተቀብለዋል። ኢትዮጵያም ውሎችን በመቀበል  የአፍሪካ አንድነትን ስምምነት አክብራለች።  ኤርትራም ስትገነጠል ከጣሊያን ጋር የተደረጉትን  ውሎች መውረሷ ከህግ አንጻር ትክክል ሊመስል ይችላል። ይሁን እንጅ ይመስላል ማለት ነው ማለት አይደለምና ፣ ለምን ትክክል እንደማይሆን ሁለት ምክንያቶችን ላቅርብና ልከራከር። አንደኛ በአለማቀፍ የውል ስምምነት ( the law of treaties) መሰረት በሁለት መንግስታት መካከል ያለው  የድንበር ውል ስምምነት  አንደኛው አገር በተዋዋዩ አገር ላይ ወረራ ካካሄደ ህጉ ይፈርሳል። ጣሊያን በ1928 ዓም ኢትዮጵያን ስትወር ከጣሊያን ጋር የተፈረሙት የቅኝ ግዛት ውሎች በሙሉ ዋጋ አልባ ይሆናሉ። ኤርትራ ስትገነጠል ኢትዮጵያ የጣሊያንን ወረራ በማንሳት ከኤርትራ ጋር  እንደ አዲስ የውል ስምምነት ማድረግ ትችል እንደነበር ይሰማኛል። የአሰብንም ጉዳይ ብትፈልግ ልትደራደርበት ትችል እንደነበር አምናለሁ። ይህ ብቻ ሳይሆን ሶማሊያም ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ ኢትዮጵያ ከሶማሊ ጋር ያለውን  የድንበር ውል አልቀበልም ማለት ትችል ነበር። በዚያ አካባቢ ወደብ ብትፈልግ  ኖሮ ብዙ ርቀት መሄድ ትችል ነበር ብዬ አስባለሁ።  ጊዜው የቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ስለነበር  ኢትዮጵያ የአሜሪካንን ጫና ተቋቁማ እንደማታስፈጽመው እረዳለሁ።  በኤርትራ ጉዳይ ግን፣  መለስ ዜናዊ የቅኝ ግዛት ውሎችን አልቀበልም ቢል ኖሮ፣ ኢትዮጵያ ቢያንስ የአሰብን ወደብ ለማግኘት ትችል ነበር። መለስ ዜናዊ ለተመድ ድብዳቤ ከጸፈ በሁዋላ፣ ከዚያም አልፎ በባድሜ ጉዳይ የቅኝ ግዛት ውሎችን እንደሚቀበል ካረጋገጠ በሁዋላ  አሰብንም ሆነ ባድሜን የኢትዮጵያ አካል ለማድረግ የነበሩት ጠባብ እድሎች ሁሉ የመከኑ ይመስለኛል።
ከባድመ ጦርነት በሁዋላም ቢሆን  አለማቀፍ የገላጋዮች ፍርድ ቤት ከባድመ ጥያቄ በፊት ወረራውን ማን ጀመረው በሚለው ጥያቄ ላይ ውሳኔ ቢሰጥ ኖሮ፣ ውሳኔውም ኤርትራን ጥፋተኛ ቢያደርግ ኖሮ፣ ኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ውሎችን አልቀበልም የማለትና እንደገና የመደራደር መብት ይኖራት ነበር ብዬ አስባለሁ። “ጦርነቱን ማን ጀመረው?” ከሚለው ጥያቄ በፊት ግን የባድመ የባለቤትነት ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶት ባድመ ለኤርትራ ተወሰነ። ኢትዮጵያም የቅኝ ግዛት ውሎችን በድጋሜ እንደምትቀበል አረጋገጠች። ኢትዮጵያም   አሰብን  መልሳ የምታገኝበት እድል ዘጋች፤ ከእግዲህ እነዚህን ቦታዎች መልሳ የምታገኝበት የህግ እድል ይኖራታል ብዬ ለማመን እቸገራለሁ።   ሌሎች የማላውቃቸው ከወደብ አጠቃቀም ጋር የሚኖሩ አለማቀፍ ህግጋት ሊኖሩ ይችላሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ያነበቡ ሰዎች ሃሳባቸውን ቢያካፍሉን ደስ ይለኛል።
ከእንግዲህ አሰብን መጠቀም የምንችለው፣ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ ወረራ እስካላካሄደች ድረስ ( ታደርጋለች የሚል እምነት የለኝም)   ከኤርትራ ጋር ወዳጅነት በመመስረት ብቻ ይመስለኛል። የህግ አማራጮችን ሁሉ መለስ ዜናዊ ቀብሯቸው ሄዷል ።  አዎ ኤርትራኖች ይፈልጉናል፣ እኛም እንፈልጋቸዋለን። ለሁላችንም የሚሆን ምርጥ የፖለቲካ ስርዓት ከመሰረትን  እንደ አውሮፓ ህብረት ድንበር የለሽ አገር መፍጠር እንችላለን።  ከእንግዲህ የሚያዋጣው  የጉልበትና የህግ ሳይሆን አብይ እንዳለው የፍቅርን መንገድ መከተል ብቻ ይመስለኛል። ከዚህ ውጭ ለአገሬ የሚጠቅማት ሌላ አማራጭ ካለ ተግባራዊ ለማድረግ በተጠንቀቅ መቆሜን አስታውቃለሁ።
Filed in: Amharic