>
5:21 pm - Saturday July 21, 2694

ግልፅ ደብዳቤ ለኢህአዴግ ባለስልጣናት (ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ)

 

ጉዳዩ– ባድመን አስመልክቶ አምባሳደር ስዩም መስፍን እውነትን ስለመናገራቸው

ውድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ሆይ

በቅርቡ በተካሄደው ልዩ ስብሰባችሁ ላይ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋራ ለመታረቅ ባድመን፣ ዛላንበሳን፣ ኢሮብን፣ ፆረናን እና በጠቅላላው 17 ግዛቶችን ለኤርትራ ለመቸር ማቀዳችሁን በዜና አደመጥኩ። እባካችሁ ይሄ እንዴት ሊሆን ይችላል? የዛሬ 18 ዐመት አካባቢ የባድመ ጦርነት አልቆ፣ የመሬት ይገባኛሉ ሙግት ለዐለምእቀፍ ፍርድቤት ቀርቦ ለኢትዮጵያ እንደተፈረደላት ለኢትዮጵያ ህዝብ አብስራችሁ ነበር። በዛን ወቅት የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አምብሳደር ስዩም መስፍን በዐለምአቀፉ ፍርድቤት ኢትዮጵያ ማሸነፏን ያበሰሩን እናንተን ኢሀአደጎችን እና የወቅቱን ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊን ወክለው መሆኑ ግልፅ ነው። መቼም አቶ ስዩም መስፍን የመንግሥታቸውን ድምፅ ከመንግሥታቸው ታዘው ያንፀባርቃሉ እንጂ ከራሳቸው አንደበት ብቻ አፍልቀው አይናገሩም። ዳሩ ግን ይሄን ሰሞን አምባሳደር ስዩም ስለባድመ ዋሽተዋል፣ በአልጅርስ የተሰየመው ፍርድቤት ባድመን እና ዙሪያውን የሰጠው ለኤርትራ ነው፣ የሚል ወሬ ይናፈሳል። ይህ ወሬ እናንተን እና እናንተን ወክለው ኢትዮጵያ ተበየነላት ብለው ያበሰሩንን አምባሳደር ስዩምን ዋሾ ያደርጋል።

አምባሳደር ስዩምን የመሰሉ ትልቅ ሰው ይዋሻሉ ብዬ አላስብም። እናንተ ኢህአደጎችም ትቀጥፋላችሁ ብዬ ሸክ እይገባኝም። ቃላችሁ እውነት መሆኑን አልጠራጠርም። የላዩን ለመድገም፣ እናንተን ወክለው የተናገሩትን አምባሳደር ስዩም መስፍንን ይዋሻሉ ማለት እናንተም ሃሰተኞች ናችሁ ማለት ነው። አምባሳደር ስዩም መስፍን በአንድ ቃል የአሉት ”የጫካ ህግ በደንብ ህግ ትሸንፏል። ኤርትራ ያቀረበችውን የመሬት ጥያቄ የዐለምአቀፉ ፍርድቤት ለኢትዮጵያ በይኗል” የሚል ነው። ለማስረጃ፣ የተናገሩበትን ሺዲዮ ማየት ነው። ሺዲዮው በእየ ፌስቡኩ ላይ ተሰራጭቷል።

ከቡራን ኢህአደጎች ሆይ! 
በእናንተው አፈቀላጤ በአቶ ስዩም አፍ እንድሰማነው፣ ባድመ እና ዙሪያው የኛ መሆናቸውን የዐለምአቀፉ ፍርድቤት በይኖልናል። ስለእዚህ እነዚህ መሬቶች የኢትዮጵያ ናቸው። እንደምታስታውሱት፣ ባድመንና የአካባቢውን ዳር ድንበር ለማስክበር ከ 70 ሺ በላይ ወጣት ኢትዮጵያውያን አልቀዋል። በተለይ የአማራ እና የኦሮሞ ልጆች በተቀበሩ ፈንጂዎች ላይ በአምካኝነት እንዲንደረደሩ ተደርገው እምሽክ ብለው እንደ አለቁ የማይዘነጋ ነው። አገራችን ትግራይ በኤርትራ ተወረረች ሲባል ወይ እገሬ ብሎ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለነፍሱ ሳይሳሳ ለትግራይ ደርሶላት አጥንቱን እየከሰክሰ ደሙን እየረጨ እንደተሰዋላት የትግራይ ህዝብ አይዘነጋም። ታዲያ እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ እናንተ እንዴት ባድመን እና ዙሪያውን ለእርቅ ስንል እንሰጣለን ትላላችሁ? የ ሰባ ሺው ኢትዮጵያውያን ደም አይፋረዳችሁምን? ደግሞስ ለ 18 ዐመታት ሙሉ ለምን ይሰጥ አላላችሁም? ይህንን ጉዳይ ለ ኢትዮጵያ ህዝብ ባጠቃላይ፣ ለ ትግራይ ህዝብ በተለይ፣ እንዲሁም ለፓርላማ አቅርባችሁ አከራክራችሁ ስምምነት ላይ ደርሳችኋልን?

ከአቶ ኢሳያስና ኤርትራ ጋራ መታረቁ እጅግ መልካም ቢሆንም፣ በሌሎች ነገሮች ተደራደሩ እንጂ ደም እና አጥንት የተክፈሉበትን መሬት እንዴት በነፃ ታድላላችሁ? ሌሎቻችሁ ይህ ነገር ባይቆረቁራችሁም እንኳን እንዴት ህወሀት ዝም እለ? ህወሀት (ህዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ) ስሙ እንደሚያውጀው 17 ዐመታት ሙሉ በዱር በገደሉ አጥንቱን የከስክሰውና ደሙን ያፈሰሰው ትግራይን ነፃ ለማውጣት እንጂ ነፃ ያወጣውን መሬት ለባእድ ሃገር ሊያስረክብ ነውን? ህውሃቶች ሆይ የደማችሁለትን መሬት አድኑ። በዳር ድንበርህ ላይ የማትደራደረው በኢትዮጵያ ስንደቅአላማ ተጠቅልለህ የምትቀበረው የትግራይ ህዝብ ሆይ መሬትህን ጠብቅ። ህወሀት አቅም እንሶት ከሆነ መሬቱን ያድን ዝንድ ክጎኑ ቁምለት። “አይዞህ፣ አለንልህ፣ ስንዝር መሬትም እንኳን ከእኛ አይነጠቅም” በሉት። አንተም 17 ዐመት ሙሉ በዱር በገደሉ እና በባድመ ጦርነትም ልጆችህን የገበርከው የትግራይ ቅንጣት መሬት አንዳይወሰድ ነውና በርታ። የኤርትራ መንግሥት የከጀለው መሬት ቢሰጠውም እንኳን ካሳ ካልተጨመረልኝ እልታረቅም ሊል ስለሚችል መሬት ማደሉ አስተማማኝ እርቅን ስለማይፈጥር ጉዳዩ ክወዲሁ እንዲታሰብበት ያሻል።

በመ ጨረሻ ደግሞ ክቡር ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድን የማሳስበው ኤርትራ ለኔ ይገባኛል የምትለውን መሬት ሁሉ በዐለምአቀፉ ፍርድቤት ለኢትዮጵያ እንደተፈረደ አምባሳደር ስዩም መስፍን ባረጋገጡልዎት መሰረት ባድመ እና ዙሪያዋ የኢትዮጵያ መሆንዋን አውቀው ይታቀቡ እንጂ የኢትዮጵያን መሬት አርስዎ በፊርማዎ አፅድቀው ለኤርትራ እንዳይሰጥዋት ይጠንቀቁ። በታሪክና በህግም ያስጠይቆታልና። እርስዎ ለብቻዎ መወሰን ከአቃተዎት ነገሩን ለኢትዮጵያ ህዝብና ለፓርላማ ያቅርቡት። ትግራይ በተወረረች ጊዜ ህወሀት የድረሱልኝ ጥሪውን ያቀረበው ለኢትዮጵያ ህዝብ ስለነበርና የኢትዮጵያ ህዝብም ደርሶለት በደሙ እና አጥንቱ ዳር ድንበሩን ስለአስከበረለት ይህ ነገር የኢትዮጵያ ህዝብንም ይመለከተዋልና ጉዳዩ በአስችኳይ ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ እንዲደርስ ተገቢ ነው።

Filed in: Amharic