>

ጠላፊው ተጠልፏል!!! ደህንነቱስ ተጠሪነቱ ለማን ይሆን? (ደረጄ ደስታ)

የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢመደኤ) ወይም  በእንግሊዝኛው ኢንሳ እየተባለ አጥሮ እሚጠራው ይህ የጠለፋ ተቋም ሥራው ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ አገርና የአገር ጠርና ጸር የሆኑትን መሰለል ነው፡፡ ስልኩንም ኢሜሉንም እንደሳተላይት ያሉት የመገናኛ ብዙሃንንም ሆነ  ያሉትን የመረጃ ልውውጦች በሙሉ እየቀዳ እሚያቀብል ቁልፍ ተቋም ነው፡፡ በሰው ለሰው ክትትል ላይ ያተኮረው የደህንነት ተቋም እርምጃ እሚወስደው ወይም እሚያስወስደው ከዚህ ተቋም እሚያገኘውን መረጃና ከራሱ ሰዎችም እሚያገኘውን መረጃ በማቀናጀት ነው፡፡ በዚህ ዘመን አብዛኛው መረጃ እሚገኘው ቴክኖሎጂውን በመጠቀም መሆኑ የታወቀ በመሆኑ የኤጀንሲው ድርሻ እጅግ የላቀ መሆኑን አይጠረጠርም፡፡ተራ ከተራው ሰው ፣ ጀኔራሉ ከጀኔራል፣ ሚኒስትሩ ከሚንስትር ሌላው ቀርቶ ሰላዩ ራሱ ከሌላው ሰላይ ጋር እሚያወራውን ልቅም አድርጎ እሚሰማው ይህ ተቋም ነው፡፡ እዚህ ተቋም ውስት እሚሰሩ ሰዎች ብዙ ገንዘብ ፈሶባቸው በአገር ውስጥና በውጭ አገር የሠለጠኑ ባለሙያዎች ናቸው፡፡
ይህን ኤጀንሲ ለረጅም ጊዜ የመሩትን ሜጀር ጀነራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ ነበሩ፡፡ ባንድ ወቅት እሳቸው ለትምህርት ወደ ጀርመን ባቀኑበት ወቅት እሳቸውን ተክቶ ይንቀሳቀስ የነበረው ሰው ተቋሙን ባንድ እግሩ ገልብጦ አሰራሩን አቀላጥፎ ሠራተኛውን እንደገና አደራጅቶና አነቃቅቶ የተመሰገነ ተቋም ያደርገዋል፡፡ ጀኔራሉ እሳቸው በሌሉበት እሳቸውን እሚያሳጣ ሥራ መስራቱን አልወደዱትም፡፡ ከሁሉም በላያ ደግሞ እጅግ የነደዳቸው ይህ የተደረገው እሳቸው ጨርሶ በማይወዱት ሰው መሆኑ ነው፡፡ ከዚያም በፊት ቁርሾ ስለነበረባቸው ከድርጅታቸውም ሆነ ከውልደታቸው ያልሆነ ይህ ሰው ይህን ያህል ርቆ መሄዱን አልወደዱትም፡፡ ሰውየው ግን በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለነበሩት አቶ መለስ ዘንድ በአካል እየቀረበ በሳምንት ለተወሰኑ ቀናት ሪፖርት (ብሪፍ) ያደርግ ስለነበረ ወደላይ ካሉትም ሰዎች ጋር  ልዩ ቅርበት ፈጥሯል፡፡ እንደሚባለው ይህን እሳት የላሰ ጎረምሳ መለስም ሳይወዱት አልቀረም፡፡ በዚህ እጅግ የተበሳጩት ጄኔራል ተክለ ብርሃን ሰውየውን አበሳጭተውና አስመርረው እንዲሁም ወንጅለውና ዶልተው ከዚያ ቤት እንዲባረር ያስደርጋሉ፡፡ ያ የተባረረው ሰው ዛሬ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ አገርና ድርጅት እንዲመራ ተመርጧል፡፡ ጀኔራሉ የአብይን መመረጥ እንደሰሙ ጓዜን ጨርቄን ሳይሉ በገዛ ፍቃዳቸው ሥራቸውን ሲለቁ ማንም አልቀደማቸውም፡፡ እንደሜቴክ ሓላፊ እንደ ጀኔራል ክንፈ እሳቸውም ሳልቀደም ልቅደም ብለው ራሳቸውን አብረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሥራና ጥቅሙን አሳምረው እሚያውቁትን ይህን ቁልፍ ተቋም እንደገና በአዲስ አመራር ለማዋቀር አፍታም አልፈጀባቸውም፡፡ በለቀቁት ጀኔራል ምትክ የራሳቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ወዳጅ እንደሆኑ እሚነገርላቸውን የአማራው ተወላጅ አቶ ተመስገንን ጥሩነህን በሳምንቱ ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሾሟቸው፡፡ እንዲሁም የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች የነበሩትን ኮሎኔል ታዜር ገ/እግዚአብሔር፣ አቶ ቢንያም ተወልደ እና አቶ ሲሳይ ቶላን እንዳሉ አነሷቸው፡፡ በምትካቸው የኦሮምያ ብሮድካስቲንግ ኔትዎርክ (ኦቢኤን) ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ወርቁ ጋቸና  ጨምሮ እንዲሁም ዶ/ር ተፈሪ ፍቅሬንና ኮ/ል አብርሃም በላይን አምጥተው ሾሟቸው፡፡ በተለይ ኮ/ል አብርሃም በላይ እንደ ዶ/ር አብይ ሁሉ ከኢንሳ ተባረሩ ሰው እንደነበሩ ተነግሯል፡፡ አብይ ይህን ሲያደርጉ እስከዛሬ ሲቀዳ የከረመውን ፋይልና ከዛሬ በኋላ እሚታለበውን ኢንፍሮሜሽን በሙሉ ልቅም አድርገው በ እጃቸው አስግብተዋል ማለት ነው፡፡ በዚያ ላይ ኢንፍሮሜሽኑ በሙሉ በቀጥታ እሚሄደው ወደ ሳቸው ቢሮ ይሆናል፡፡ ለወዲያኛው የደህንነት ተቋም ለአቶ ጌታቸው አሰፋም እሚሄደው ኢንፎርሜሽን ተለክቶ እሚላከው በዚህ ተቋም አማካይነት እንደነበር መገመት አያዳግትም፡፡
እንግዲህ ኦህዴዶቹ እነ አቶ ለማ መገርሳም አቶ ወርቅነህ ገበየሁና ራሳቸው ዶ/ር አብይም በደህንነቱ በኢንሳው በፖሊስና በመከላከያው ተቋማት ውስጥ ከሠሩ ልምዱም ሚስጥሩም ይኖራቸዋልና የዛሬው ፖለቲካ “ተው እንጂ ስንተዋወቅ አንተናነቅ” ዓይነት ጨዋታ ሳይሆን አልቀረም፡፡ ዛሬ ዛሬማ ደህንነቱ ተጠሪነቱ ለማን ነው ከማለት ይልቅ ደህንነቱ ማነው ማለቱም ሳይቀል አይቀርም፡፡ ጀኔራል አደም ሲመጡም ሆነ እንደሚሟረተው አቶ ጌታቸው አሰፋም በደህንነት አማካሪነት ቢቀመጡ ከታች ያለውን መረጃ ሽቅብ እሚያቀብሉት ሰዎች ወሳኞች መሆናቸው አይካድም።
የፖለቲካ ነገር ግን ድንቅ ይላል። ይሆናል የተባለው ሳይሆን እየቀረ፣ ሰይጣን ሰይጣኑ እየተቀየረ፣ ውስጥ ውስጡን አድብቶ፣ ጓደኞቹን ከድቶ፣ አብይን ከመልገበጥ አፋፍ ያስቀረ ማን እንደሆነ ሲታወቅ፣ ማስደነቁ አይቀርም። አሁን ማን ይሙት ጀኔራል ሳሞራ እነ አብይ እና ለማ መገርሳ ላይ የተቃጣውን ግልበጣ አክሽፈው አስቀርተዋል? ወይስ ጨዋታው ሁሉ ያው ሸልሞ ማባረር ስለሆነ ነው? ወይስ  ባለቀ ሰዓት ታሪክ ስምን አሳምሮ እንዲጽፍ እሚነዛ ወሬ ነው? ወሬውማ እኮ እነ ስብሐት እነ አዜብን ከመቀሌ ያባረሩ ቀን እነ አዜብ አዲስ አበባ ሮጠው ለነሳሞራ ስሞታ ነግረው… እነ ስብሐት እስኪ ያንቺ ሳሞራ ሲያድንሽ እናያለን …ሲሉ ሳሞራም ተበሳጭተው ምናልባትም …ግድ የለሽም እኔ ሳሞራ ይህን ስብሐት እሚባል የከሰረ ሽማግሌ አሳየዋለሁ እያሉ…
ነገሩ ሁሉ የጅል ጨዋታ ይመስላል። ጉዳዩ ውስጥ አገር ባይኖርበት አሁን ይህን ወሬ ብሎ ማን ያወራዋል?! ግን ያው የፖለቲካችን እንቶ ፈንቶ እንዲህ ከሆነ ቤት ያፈራውን ከማውራት ውጭ የሌለው ከየት ይመጣል? ይሄን ሁሉ ጉድ እየጠለፉ እየሰሙ የአገር ሚስጥር እሚኮመክሙ የኢንሳ ሰዎች ግን ትንሽ ቢያካፍሉን አፍታተንና አጣርተን እንጽፈው ነበር። ደህንነቶችም እኮ ቢሆኑ አንዳንዴም ተጠሪነታቸው ለህዝቡ ቢሆን ምናለበት? ህዝቡም እኮ ቢሆን የደህንነቱም ሆነ የኢንሳ ተቋማት ጠቀሜታቸው የአገር ውስጥ ፖለቲካን ለማፈንና ሥርዓቱን ለመጠበቅ ብቻ ሳይሆን አገሪቱን ከውጭ ጠላቶች የመጠበቅ ኃላፊነት እንዳላቸውና ያንንም በብቃት ሲወጡ የቆዩ ባለሙያዎች ጭምር ያሉበት ተቋማት መሆኑን አይስተውም። በዚያች ላይ ደግሞ ህዝቡንም ከአፈናው ሥርዓት ግፍና በደል፣ ከነጣቂና በጣጣቂ ባለሥልጣናት እሚጠብቅ ደህንነት ቢሆን ደግሞ፣ አገር በፍቅር በወደቀለት ነበር። ተጠሪነቱ ለህዝብ የሆነ ተቋም ሁሌም ተመስጋኝ ነው።
Filed in: Amharic