>
5:31 pm - Friday November 13, 3114

የማኪያቬሌን ጥበብ የተላበሰው አብይ  እና አባዱላ ገመዳ !!! (ፋሲል የኔአለም)

 ስለአባዱላ ገመዳ ሙሉ የፖለቲካ ህይወት፣  ስለ አነሳሱም ሆነ ስለ አወዳደቁ፣ መናገር አልችልም፤ ስለማላውቅ። ላካፍላችሁ የወደድኩት በቅርቡ በኢህአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ በአባ ዱላ ዙሪያ ስለተፈጠረው ነገር ነው። በሰማሁት ልክ እነሆ።
ያን ሰሞን ጠ/ሚኒስትር ማን ይሁን በሚለው ጥያቄ ዙሪያ ኢህአዴጎች በከፍተኛ ሁኔታ ይሻኮቱ ነበር።። ብአዴን፣  ኦህዴድ ጠ/ሚኒስትርነቱን መያዝ አለበት የሚል አቋም ሲያራምድ፣ ኦህዴድ ደግሞ፣ ሙሉ ድጋፍ አላገኝም በሚል ስጋት፣ ደመቀ ጠ/ሚኒስትር  መሆን አለበት የሚል አቋም ይዞ ነበር።። በሁለቱ ድርጅቶች መካከል በተደረገው ውይይት ኦህዴድ በመጨረሻ ቦታውን ለመረከብ ተስማማ። ወግ አይቀርምና ሃይለማርያም እና ሽፈራው ደግሞ በጎን፣ ስልጣኑን ኦህዴድ ይውሰደው ነገር ግን እነ ለማ ከሚሆኑ፣ እንደልባችን የሚታዘዛውን፣ አባዱላን እናድርገው ብለው መከሩ ፣ ህወሃትንም አማክረውት ምርጫውን ተቀበለ። አባዱላንም ቤተ መንግስት ጠርተው ነገሩት።  አባ ዱላ በጣም ደስ አለውና ድጋፍ ለማሰባሰብ ወደ እነለማ ሄደ። አባዱላ ለማን “ጠ/ሚኒስትር ልሆን ነውና ድጋፍ ስጠኝ” ሲለው፣ ለማ በቁጣ “ አርፈህ ተቀመጥ” ብሎ ቅስሙን ሰበረው። ለማ ጠ/ሚኒስትር እንደማይሆን ስለሚያውቀው ከአብይ ጋር የድርጅት ሊ/መንበርነት ቦታ ተለዋወጡና አብይን ለቦታው አዘጋጀው። አባዱላ አኮረፈ። ህወሃት ፊቱን ወደ ሽፈራው ሽጉጤ ያዞረው ከዚህ በሁዋላ ነው።
የጠ/ሚኒስትር ምርጫ ከመካሄዱ የተወሱ ቀናት በፊት ፣ ሀይለማርያም አባዱላን ጠ/ሚኒስትር ትሆናለህ ብሎታል የሚል አጀንዳ  ምክር ቤቱ ውስጥ ተነሳ። “ሃይለማርያምና ሽፈራው ንጉስ ሿሚና ሻሪ ሆናችሁዋል፣ በየትኛውን የኢህአዴግ ባህል ነው እንዲህ ያደረጋችሁት?” የሚል ጥያቄ  ቀረበ። ሃይለማርያም ደመቀ እንዳይመረጥ ውስጥ ውስጡን ሲሰራ ስለነበርና ደመቀም ሴራውን ዘግይቶ በመረዳቱ በእጅጉ አዝኖና ተቆጥቶ፣ እነ ሃይለማርያምን ወጥሮ ያዛቸው ። ወጣቶቹ የብአዴን አባላትም ተረባረቡባቸው። ኦህዴዶችም የእሳት ነበልባል የተፉ ጀመር። ሃይለማርያምና ሽፈራው ለማንም አልተናገርንም ብለው ሸመጠጡ።  አባዱላ ጉድ ፈላበት። ወይ እነ ሃይለማርያምን ወይ ራሱን ማዳን አለበት። በላብ ተጠምቆ፣ “ሃይለማርያምና ሽፈራው ቤተመንግስት ጠርተው ጠ/ሚኒስትር ልናደርግህ አስበናል” ብለው እንደነገሩት አጋላጠ። ሃይለማርያምና ሽፈራው መሬት ተከፍታ ብትውጣቸው በወደዱ። በመጨረሻ ግለሂሳቸውን አውርደው ውይይቱ ቀጠለ።
በሰብሳቢው ደመቀ፣ በብአዴንና በኦህዴዶች ወጣት አመራሮች ትግል አብይ ጠ/ሚኒስትር ሆኖ ተመረጠ። ፤እንደተመረጠም አባዱላን የጸጥታ ጉዳዮች አማካሪ አደርጎ ሾመው። ሰውዬው በኦሮምያ በዘረጋው ኔትወርክ ችግር እንደሚፈጥር ያወቀ ይመስለኛል። ትንሽ ቆይቶም አባዱላ በጡረታ መሰናበቱን ሰማን።
 አባዱላ የደህንነት አማካሪ ከሆነ በሁዋላም አርፎ እንዳልተኛ እሰማ ነበር።  አባዱላ፣ ግርማ ብሩና ኩማ ደመቅሳ ፣ የሙክታር ከድርን ከስልጣን መውረድና የለማን መሾም ከመጀመሪያውም አልተቀበሉትም ነበር ይባላል። ለምን? ለማን እንደሙክታር እንደፈለጉ ማዘዝ ስለማይችሉ። በህዝባዊ አመጹ ወቅት፣ ከህወሃት ጋር በመሆን፣  በክልሉ ተደጋጋሚ  ግጭት እንዲነሳ ያደረጉት እነሱ ናቸው የሚል ውንጀላ ይቀርብባቸው  ነበር። አብይ ወደ ፊት ከመጣ በሁዋላ አርፈው ይቀመጡ አይቀመጡ አላውቅም ነገር ግን ለማ በቅርቡ ቀልባሾች ሙሉ በሙሉ እንዳልተመቱ መናገሩ ምናልባትም እነ አባዱላንና ግርማ ብሩ አርፈው አለመቀመጣቸውን ለማሳየት ይሆናል። ከዚህም አልፎ በእነ ለማ ላይ ከውጭም ከውስጥም ለሚሰነዘረው ትችት እነ አባዱላ ከጀርባ አሉበት የሚል ነገር ሰምቻለሁ።  ከአባዱላ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ባለሃብቶችና ግለሰቦች ለወደፊቱ ችግር ሳይገጥማቸው የሚቀር አይመስለኝም።
 ለማንኛውም አብይ አባዱላን አቅርቦ ካቀዘቀዘና ወንበሩን ካደላደለ በሁዋላ የወሰደው እርምጃ ከሆነ  ይህን ሰው የማኪያቬሌን ጥበብና የማንዴላን ፍቅር የተላበሰ ሰው አድርጌ እንድቆጥረው ወይም በአገራችን ታሪክ የሚኒልክ ወይም የራስ አሊ ሁለተኛ ጥበብ ወራሽ አድርጌ እንድወስደው እገደዳለሁ። ።  ከአብይ  ጀርባ ያሉት ሶስቱ ሚኪያቬሎች ( ደመቀ፣ ለማና ገዱ) ከእያንዳንዱ የአብይ እንቅስቃሴ ጀርባ እንዳሉ ሳልዘነጋ ነው።
Filed in: Amharic