>
5:13 pm - Thursday April 18, 2746

ወታደራዊ  ጉዳዮች... (በጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

1- ኃይለማርያም ደሳለኝ ሥልጣን ከመልቀቁ ጥቂት ቅናት ቀደም-ብሎ አራት የሙሉ ጄነራልነት ማዕረግ እንደ ፀበል  ከመረጨቱም በዘለለ፣ በሀገሪቱ ወታደራዊ ታሪክ የማይታወቅ ሶስት የምክትል ኤታ-ማዦርነት ሹመት ተሠጥቶ እንደነበር አይዘነጋም። ዛሬ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ይህንን መዋቅር ሳይገለው ቀብሮታል (ድምፅ ሳያሰማ አፍርሶታል)። በዚህ መሰረትም አንደኛው ምክትል ሳዕረ መኮንን “ጡረታ” ተብሎ ፎጣ የተወረወረለትን ሳሞራ የኑስን ተክቶ ዋና ተደርጎ ሲሾም፤ ሌላኛው ምክትል አደም መሀመድን ደግሞ ብሔራዊ ደህንነትና መረጃ በመመደብ መስሪያ ቤት ጭምር አስቀይሮታል። ብቸኛ ምክትል ሆኖ የቀረው ብራሃኑ ጁላ ነው ማለት ይቻላል (በነገራችን ላይ መከላከያ አምባሰደር ፊት-ለፊት የሚገኘውን ዋና መስሪያ ቤት በመልቀቅ ወደ ምድር ኃይል ግቢ እንደሚዘዋወር ታውቋል)
2- ኢትዮጵያ ከትላንት ማታ ጀምሮ የአየር ኃይል አዛዥ የላትም፤ አዛዡ ጄነራል አደም የሰላዮች አለቃ ጌታቸው አሰፋን በመተካት ከደብረ ዘይት ወደ አዲስ አበባ ተዟዙሯልና። በእኔ ግምትም በ2006 ዓ.ም ከሳሞራ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ከቦታው የተነሳው እና በቅርቡ የማዕረግ ዕድገት ያገኘው የህወሓቱ ሌፍተናንት ጄነራል ሞላ ኃይለማርያም ተመልሶ ይሾምበታል።
3- ጌታቸው አሰፋ ትላንት ጡረታ በወጣው አባዱላ ገመዳ ቦታ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ተደርጎ እንዳይሾም አጥብቄ እመክራለሁ። ጅምሩን ሊያደናቅፈው ይችላልና።
4- የ’ሚሊቴሪ ካውንስል’ የሚባለው መዋቅርም ፈርሶ በደርግ ዘመን ጡረታ በወጡ ጄነራሎች መቋቋም እንደሚኖርበት ለማስታወስ እወዳለሁ። በሌሎች ሀገራት ተመሳሳዩ ነው የሚደረገው። በዚህ መንገድም ተቋሙን ከፓለቲካ ገለልተኛ የማድረግ እንቅስቃሴ ለመጀመር ያስችላል።
5- የብሔር ተዋፅኦን ለማመጣጠን በሚል የብርጋዴል ጄነራልነት ማዕርግ ከህዳጣን ክልል ለተገኙ የሠራዊቱ አባላት ሊሰጥ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ከአፋር እና ከጋምቤላ ኮለኔል የደረሱ መኮንኖች ሲኖሩ፤ ከኢትዮጵያ ሶማሌ እና ከቤንሻንጉል ሻለቃን ያለፈ ስለመኖሩ አላውቅም። ከዚህ አስፈንጥሮ ጄነራል ካደረጉ ደግሞ ለተቋሙ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ዲያቢሎስ ብቻ ነው የሚያውቀው። እውነት ለመናገር ግን ውትድርና ሀገርን ከጠላት መከላከልና የሕዝብን ሰላም ማስጠበቅ እንጂ ህዳር 29 ተሰባስቦ ባሕላዊ ጭፈራ አለማሳየት በመሆኑ እንዲህ አይነቱ አሰራር በፍፁም አይመከርም።
6- መከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረው ለአለቆች የማሸርገድና ጠርዝ-የረገጠው ፍርሃት እየተሸረሸረ ይመስላል። በርግጥም ይህ አይነቱ መነቃቃት የሚበረታታ ነው። ምክንያቱም ወታደር ዲስፒሊን ማጥበቅ እንጂ አዳህሪና ፈሪ መሆን እንደሌለበት ባለሙያዎች ይመክራሉና። በቅርቡ ግዳጇን ጨርሳ ከዳርፉር የመጣች አንድ የሻለቃ ሰሞነኛ ድፍረትን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል። ሻለቃዋ ከአምስት መቶ በላይ የሰው ኃይል ያላት ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት በሜ/ጄ ሹሜ አብደታ መሪነት የግዳጅ አፈፃፀምን በተመለከተ በሁርሶ ማሰልጠኛ ለግምገማ በተቀመጠችበት ወቅት ከአበል ክፍያና ከሌሎች አስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ በተነሱ ምልልሶች ጠንከር ያለ-ጭቅጭቅ ውስጥ እንደከረመች እና አዛዦቿንም እስከ መዝለፍ እንደደረሰች ተሰምቷል። በመጨረሻም አለመግባባቱ በመካረሩ አምስት አባላት ያሉት ተወካዮች ተመርጠው ፊርማ በማሰባሰብ አዲስ አበባ በመምጣት ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዳናገሩና በሁለት ሳምንት ውስጥ መልስ ይሰጣቸዋል እንደተባሉ ታውቋል።
ስኔ  1/2010
Filed in: Amharic