>

ጉደኛው መሪያችን  (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

ዶ/ር አብይ አህመድን ምን እንላቸዋለን? ከአሁን በፊት መሪዎቻችንን ለመግለፅ የተጠቀምንባቸውን ቃላት ሁሉ የሚያልፉ ሆኑብኝ። ጉደኛ የሚለውን ቃል የመረጥኩት፥ ያልተለመደና ያልታየ ነገርን ስለሚገልፅ ነው። በሌሎች ስንቀና የኛም ተራ ደርሶ ይሆንን? ደቡብ አፍሪካ ማንዴላ ነበራት፤ ሕንድ ማህተመ ጋንዲ ነበራት፤ አሜሪካ ጆርጅ ዋሽንግተን ነበራት። ኢትዮጵያ ዶ/ር አብይ ደረሰውላት ይሆን?

ፋታ እንስጣቸው እያልን ስናወራ፤ እርሳቸው በድርጊታቸው አንዱን ሳናጣጥም ሌላ እየጨመሩ በመልካምነት ፋታ አሳጡን።

ቀድመው ያሞገሱትን ማማት ይቸግራል ብለን፤ ተስፋን በስጋት ሰንቀን ዳር ቆመን በጥርጣሬ የምናይ ሁሉ ጉድ ፈላብን። ዛሬ ዛሬ ተስፋ ስጋትን እያሸነፈ ከአጥናፍ እስከ አጥናፍ ለዶ/ር አብይ ድጋፍ እየጎረፈ ነው። ትላንት እንዳንጨራረስ እየፈራን ከዚህ አጣብቂኝ ማን ያወጣናል ስንል ነበር። የማይታለፍ የለም ያ ታለፈና፤ አሁን ዶ/ር አብይ በፍቅርና በይቅርታ ሁሉንም እየማረኩና እያስደመሙ፤ በደስታም እያሰከሩ በሚገርም አዲስ አካሄድ ኢትዮጵያን እያሻገሩ ይገኛሉ። ግን ቆም ብሎ ለሚያስተውል፤ ይህ ትዕይንት ከስጋና ደም ስራ በላይ ነው። የኢትዮጵያ አምላክ በምህረት እርሱ ራሱ ምድራችንን በፈውሱ እየጎበኘ እንደሆነ ለአስተዋይ ሰው ምንም ጥርጥር የለውም። አምላክ ደግሞ በስራ ላይ ሲሆን፤ ጠላት ለማሰናከል ሙከራ ያደርጋል እንጂ ፈጣሪን ያደናቅፈዋል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው።

ያልተጠበቀው የኢትዮጵያዊነት ውበት ነገ እጅግ ደምቆ ሲበራ ልናይ ከሆነ፤ የማይጨበጥ ሕልም የሆነብን ዲሞክራሲ ነገ እንደ እለት እንጀራችን የምንመገበው ዕውነታ ሊሆን ከሆነ፤ ዛሬ የሚገፋፉትና የሚጠላለፉት ፖለቲከኞች ሁሉ በጠረጴዛ ዙሪያ ሆነው በወንድማማችነት መንፈስ የአስተሳሰብ ፍጭትና ፍትጊያ ሲያደርጉ አይተን ለመሆኑ እንዲህ ያሉ ድንቅየዎች ከየት መጡ እስክንል ድረስ የሚያስገርሙን ከሆነ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሜዳውም ይሄው ፈረሱም ይሄው በሐቅ መሪህን ምረጥ ተብሎ ጉድ የሚባልበት ጊዜ ሊመጣ ከሆነ፤ እኛስ የየራሳችንን የኑሮ ብልሃታችንን እንደለመድነው ከዚህ በሁዋላ ማስኬድ እንዴት ይቻለናል?

ዛሬ አይደርስ መስሎን ራሳችንን ለኢትዮጵያ የተዘጋጀን እንደሆነ ለመጠየቅ ሀሳቡም የለንም። ዛሬ ዓይናችንን ዶ/ር አብይ ላይ አተኩረን ራሳችንን ከሃላፊነት አሰናብተናል። ቁምነገሩ ኢትዮጵያ ልትነሳና ልትደምቅ፤ ይህንንም መቀልበስ በማይቻል ጎዳና ላይ ዶ/ር አብይ በብልሃት የተሞላ የጥድፊያ ጉዞ ላይ ያሉ ይመስላል። ታዲያ ለዚህ የመታደስ ዘመን ራሳችንን በመስዋዕትነት ለመስጠት እያሰብን ነን ወይ? ኢትዮጵያ የሚሞትላት ሳይሆን በመስዋዕትነት በመኖር ለችግሯ ሊደርስላት የሚችል ዜጋ የምትፈልግበት ጊዜ እየመጣ ነው። ለመልካም ኑሮ ሀገራችንንና ምድራችንን ትተን የተሰደድን ሁሉ፤ ለምድራችን ፈውስ ለመሆን ምቾትን ንቀን፥ ከሕዝባችን ጋር መከራ በመቀበል የደስታው ተካፋይ ለመሆን ለኢትዮጵያ ዝግጅት ማድረግ የምጀምርበት ወቅት ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትም ቢሆኑ በፅድቅና በእውነት ለሕዝብ አገልጋይ በመሆን ራስን ከምቾት አፋተው ራሳቸውን አሳልፈው በመስጠት የደስታው ተካፋይ ለመሆን ለኢትዮጵያ ዝግጅት የሚያደርጉበት ጊዜ ነው።

ዶ/ር አብይ ለኢትዮጵያ እየሰሩ ያሉትን እየወደድንና እያወደስን ባለበት በዚህ ወቅት፤ ለዶ/ር አብይ ኢትዮጵያ ራሳችንን በማዘጋጀት እንዲሆን ፈጣሪ ይርዳን። በመስዋዕትነት በምድረ ኢትዮጵያ በስራ ተጠምደን፤ የሀገራችንን ታሪክ በራሳችን ትውልድ ዘመነ ጊዜ ለውጠን በማየት ከዚህ ዓለም አልፈን፤ ዶ/ር አብይ እንዳሉት ያኔ እኛም በክብር ኢትዮጵያ እንሆናለን።

ዶ/ር አብይ “ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ” ብለው ሲያውጁ፤ ያኔ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ለሰማይ አደራ ሰጥተው ራሳችንን ለተዐምሩ እንድናዘጋጅ ልባችንን ማነሳሳታቸው ነበር። እንደተባለውም ፈጣሪ ኢትዮጵያን ሊባርክና ያሳለፍነውን የመከራ ዘመን ሊያስረሳን የተስፋ ጭላንጭል ከጊዜ ወደ ጊዜ ቦግ እያለ እየተጨመረ በመብራት ላይ ይገኛል። ለዚህ አስደናቂ የታሪክ ዕድል ራሳችንን ለኢትዮጵያ ለማዘጋጀት መዘርጋት የሚገባን ይመስለኛል። ዶ/ር አብይ የአምላክን በረከት ከመጥራት አኳያ በንፅፅር የንግግራቸው ማሳረጊያ አድርገው የሚጠቀሙበት ሌላ ሀሳብ አላቸው። ያም፦ “ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ ተከብራና በልፅጋ ለዘላለም ትኑር”  የሚለው ቁምነገር ነው። ፈጣሪም ልመናችንን ሰምቶ እየጎበኘን ባለበት ሁኔታ፤ ዶ/ር አብይም ታማኝ ሆነው ራሳቸውን ለተባረከች ኢትዮጵያ ራሳቸውን እየሰጡ ባለበት ሁኔታ፤ እኛስ ለኢትዮጵያ ትንሳዔ ጥረት ለማድረግ ተዘጋጅተናል ወይ?

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ። ይጎበኛታልም።

ኢሜል፦ ethioStudy@gmail.com

Filed in: Amharic