>

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ምሥረታ ተበሰረ!!! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

እዚህ ማኅበራዊ የብዙኃን መገናኛ ነው አሁን ስገባ ዜናውን የሰማሁት፡፡ አርማውም ይሄ ከታች የምታዩት የንስር አሞራና ጋሻ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ከአቀላለሙ በስተቀር ንስሩ የአሜሪካንና የግብጽን ብሔራዊ አርማ ነው የሚመስለው፡፡ አርማውን ለምን እንዲህ እንዳደረጉት አላውቅም፡፡ የምናወራው ስለአማራ ማንነት ከሆነ አማራ ከቀዳማዊ ምኒልክ ጀምሮ ለሦስት ሽህ ዓመታት የቆየ ብሔራዊ አርማ አለው፡፡ እሱም የአንበሳ ምልክት ነው የወፍ አይደለም፡፡
ይህ ብሔራዊ ምልክት እስከ ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ድረስ ብሔራዊ ምልክት ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከዚህም የተነሣ የመንግሥት ድርጅቶች አንበሳን ማዕከል ያደረገ የተለያየ ዓይነት አርማ ነበራቸው፡፡ ደርግ ሲመጣ አንበሳውን “የፊውዳል ነው!” በማለት ከብሔራዊ ምልክትነት አስወገደው፡፡ ይሁንና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ከቴሌ ኮሚውኒኮሽን (ከርሑቀ ግንኙነት) ፣ ከአውራ ጎዳና ከመሳሰሉት መንግሥታዊ ድርጅቶች አርማ ላይ ግን አላስወገደውም ነበረ፡፡
ወያኔ ሲመጣ ነው ከእነኝህ መንግሥታዊ ድርጅቶች ያስወገደው፡፡ ከአየር መንገድ ግን እንደምታስታውሱት አቶ መለስ አንድ ወቅት ላይ አሜሪካን በጎበኘ ወቅት ከኢንባሲው (ከእንደራሴ መሥሪያ ቤቱ) ውስጥ ከጥቂት ኢትዮጵያውን ጋር ውይይት ባደረገ ጊዜ “እስላም ነን!” ያሉ ወገኖች “የአንበሳው ምልክት እኛን እስላሞችን አይወክልምና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ይነሣልን!” ብለው ጠይቀው አቶ መለስ እንደሚነሣ ቃል ገብቶላቸው ማንሣቱም ተጀምሮ ነበረ፡፡
ይሁንና ግን በውጭ የሚኖሩ ምሁራን ኢትዮጵያን “የአንድ ሀገር ቅርስ በኋላ ዘመን ላይ ቅሬታ በሚያነሡ ግለሰቦች ጥያቄ ምክንያት ብቻ ይወገዳል ብሎ መወሰን ፍጹም ስሕተት ነው! የአንድ ሀገር ቅርስ ቅርስ ከሆነ በኋላ ቅርስነቱ ለሁሉም ዜጋ ነው እንጅ ለተወሰነ ክፍል ብቻ አይደለም! ይሄንን ዓለምአቀፋዊ መስፈርትና አሠራር አንቀበልም ከተባለ አይወክለንም ያሉ እንዳሉ ሁሉ ይወክለናል የምንልም አለንና ሕዝበ ውሳኔ ሳይሰጥበት እንዲወገድ ማድረግ ኢዲሞክራሲያዊ (ኢመስፍነ ሕዝባዊ) አሠራር ነውና እኛም አንቀበልም እንቃወማለን! በአየር መንገዱም አንበርም! የገበያ ማዕቀብንም እናውጃለን!” ብለው በማስፈራራታቸውና አየርመንገዱም ኢትዮጵያውያን በአየር መንገዱ ካልበረሩና ተዓቅቦ ካደረጉ ሊከስር እንደሚችል በማመልከቱ የአንበሳው ምልክት መነሣቱ ሊቀር ችሏል፡፡
እናም “የአማራ ማንነትን እንጠብቃለን! እናስከብራለን! እናስመልሳለን!” ካልን ጥንታዊና ቅርስ የሆነ አርማ አለንና እሱን ነው ልንጠቀም የሚገባው፡፡ ያለምንም አሳማኝ ምክንያት ወይም በነአሜሪካ ብሔራዊ ምልክት በመማረክ ከሌላ መቅዳት አግባብ አይደለም፡፡
ወይም ደግሞ እንዲህ የተደረገው ያልገባቸው ሰዎች ቅሬታ ተፈርቶ ከሆነ ወደ ሌላ ምልክት የተሔደው ሌሎች ስለጠሉ ብቻ የምንጥለው የምንተወው ቅርስ፣ ማንነት፣ ታሪክ ካለ መሥመር ስተናል! በተመልካች ዘንድም “አማራ ገና ትክክለኛ ወኪሉን እንዳላገኘ የሚያመላክት ነው!” የሚል መልእክት ያስተላልፋልና ዛሬ ምሥረታው የታወጀው አብን (የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ) ቶሎ የማስተካከያ ወይም የእርምት እርምጃ መውሰድ ይገባል እላለሁ፡፡
ድል ለአማራ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic