>

መዲናችን አ.አ የኢትዪጵያ ብሄርተኝነት መፈልፈያ የችግኝ እርሻ ሆኖ መተው ይኖርበታል!!! (ያሬድ ጥበቡ)

ኦፌኮ በምርጫ ኦህዴድን ለመዘረር የሚያደርገው ሩጫ አሳሰቦኛል። ቢሳካለት አንድምታው ምንድን ነው? የአትላንቲክ ካውንስል ስብሰባ ላይ የተገኙ ወገኖች እንዳጫወቱኝ በበቀለ ገርባና እስክንድር ነጋ መካከል ልዩነቱ እጅግ ጎልቶ የወጣበት አንድ ጉዳይ ቢኖር የቀጣዩ ምርጫ ጥያቄ ነው። በቀለ ምርጫው የጊዜ ሰሌዳውን ጠብቆ እንዲካሄድ ግፊት ሲያደርግ የእስክንድር ትኩረት ደግሞ ሁሉን አቀፍ ጉባኤ እንዲጠራ ነው። ጥያቄው፣ ለምን እነበቀለና ኦፌኮ ለምርጫ መጣደፉን መረጡ የሚል ይመስለኛል።
ፍርሃታቸው፣ ሁሉን አቀፍ ጉባኤ ከተካሄደ መሠረታዊ ህገመንግስታዊ ጉዳዮች ተነስተው ወደ ድሮዊንግ ቦርዱ ወይም ሰኔ 1991 የሽግግር ጉባኤ ይመልሰናል የሚል ፍርሃት ስለሚሰማቸው ይሆን? ወደ ሽግግር መሰል ሁኔታ ብንመለስ ለምን ይፈራሉ? ህገመንግስቱን አሻሽሎ፣ አርሞ፣ አስተካክሎ ወደ ምርጫ መሄድ ለምን ያስፈራቸዋል? ይህስ ፍርሃታቸው የወያኔ እቅፍ ውስጥ እንደማይጥላቸው ምን መተማመኛ አለ?
ለማስተዳደር አስቸጋሪ ከሆኑ ዘጠኝ ክልሎች ይልቅ የባህልና ቋንቋ ፍላጎታቸውን ሳያዳክም እንደ አዲስ አነስ አነስ አድርጎ የአውራጃ ፌዴራል አስተዳደሮችን በማቆም በተሻለ መንገድ ማዋቀር ለእድገት ሊያመች ይችላል። ለምን በወያኔ ጥብቆ ልክ በተሰፋ የክልል አጣብቂኝ ውስጥ መኖር መገደድ አለብን? ዛሬ ያለው ክልል እኮ አምስት ሚሊዮን ህዝብ ያለውን ትግራይና 28 ሚሊዮን ህዝብ ያለውን አማራ ወይም 34 ሚሊዮን ህዝብ ያለውን ኦሮሚያ እንደ እኩል ነው የሚያየው። ለአማራ ክልል ዋና ከተማ የሚደረገውን ያህል ለመቀሌም ይደረጋል። ይህ ሊቀጥል አይችልም። የአማራ ክልል ለትግራይ የሚደረገውን ስድስት እጅ የበለጠ ሲደረግለት ብቻ ነው ሥርአቱ ፍትሃዊ ነው የሚባለው። ይህ እንዲሆን ደግሞ የአማራው ክልል ለማስተዳደር ምቹ ወደሆኑ ፌዴራል አውራጃዎች ሲከፋፈል ለፍትሃዊ አስተዳደር በር ይከፍታል። ለምሳሌ አንድ ፌዴራል አውራጃ በአማካይ ሁለት ሚሊዮን ህዝብ ቢኖረው ትግራይ ሶስት ፌዴራል አውራጃዎች (ምሥራቅ፣ ምዕራብና ማእከላዊ)፣ አማራ 14 አውራጃዎች (ምናልባት የኃይለሥላሴ ዘመንን አውራጃዎች ተከትሎ)፣ ኦሮሚያ 17 ፌዴራል አውራጃዎች (ምናልባት የቀድሞ የጎሳ አደረጃጀቱን ይዞ ኢቱ፣ ቦረና፣ ከረዩ ወዘተ አያለ) እንደገና ሊዋቀር ይችላል።
አዲስአበባም ለ27 ዓመታት ተነፍጎ የቆየውን የፌዴራል መንግስቱ አባልነት መብቱን አስከብሮ፣ አንገቱ ላይ የተንጠለጠለበትንም የኦሮሞ ብሄርተኝነት ሰይፍ አስወግዶ፣ በመቶ ስንትስ ዓመታት ታሪኩ የሁሉም ብሄረሰቦች የገንዘብ፣ የጉልበት፣ የፍቅር፣ የእንባ ሃብት ፈሶበት የተሠራ የኢትዮጵያችን መዲና በመሆኑ የኢትዪጵያ ብሄርተኝነት መፈልፈያ የችግኝ እርሻ ሆኖ መተው ይኖርበታል። ይህም ከኦሮሞ ብሄርተኝነት ጋር በየጊዜው እንዳያላትመውና የቁርሾ መንስኤ እንዳይሆን፣ አዲስአበባ አሁን ካለውም የመሬት ይዞታ ሰፋ ብሎ መከለል ይኖርበት ይሆናል። የማእከላዊ ኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ተብሎ። በአማርኛም ላይ አፋን ኦሮሞን ተጨማሪ ቋንቋው አድርጎ ሊቀበል ይችላል፣ የኦሮሞ ብሄርተኞች የላቲኑን ቁቤ ትተው የግእዙን ኢትዮጲስ ፊደል ለመቀበል ፈቃደኛ ከሆኑ።
የኦሮሞ ብሄርተኞች በአንድ ሃገር ሁለት ፊደል መጠቀም አዳጋች መሆኑን መቀበልና፣ ላቲኑን አስር ጊዜ የሚያስከነዳው የግእዝ ፊደል አፋን ኦሮሞን ለመግለፅ የበለጠ አቅምና ክህሎት እንዳለው ሊቀበሉ ይገባል ። የኢትዮጵያ ቅኝ ተገዢ ስለሆንን የተለየ ፊደል ያስፈልገናል ተብሎ የገባው የላቲን ቁቤ ዛሬ ኢትዮጵያዊነቱን ብቻ ሳይሆን የማእከላዊ መንግስት አስተዳደሩን ለተረከበው ኦሮሞ ቁቤ አይመጥንም። አውሮፓውያን ለጥቁር ህዝቦች ዝቅተኝነት ዓይነተኛ መከራከሪያቸው “ተመልከቷቸው ፊደል ያለው ቋንቋ እንኳ የላቸውም” የሚል በመሆኑ፣ የግእዝ ፊደልን ወደተቀረው አፍሪካ ይዘን መሄድ ሲገባን  ኢትዮጵያ ውስጥ መቀበል ቢያቅተን ራስን ሰድቦ ለሰዳቢ የመስጠት ያህል ነውር ነው።
የኦሮሞ ብሄርተኝነት አፋን ኦሮሞን የኢትዮጵያ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ ማድረግ ከፈለገ፣ ኢትዮጵያዊ ለሆነው ግእዝ ያለውን ጥላቻ ማቆም አለበት። ሥልጣን ይዘናል የፈለግነውን ማድረግ እንችላለን ብሎ የሚያስብም ከሆነ ወያኔ ለ27 ዓመታት ከሄደበት የጡንቸኝነትና የህዝብ ጥያቄ እምቢተኝነት ጋ ተመሳሳይ ስለሚሆን ሄዶ ሄዶ የወያኔ እጣ ነው የሚደርሰው። ወያኔ የወደቀው ከአነስተኛ ብሄረሰብ የወጣ ስለሆነ አይደለም፣ አስተሳሰቡ ጠባብና እብሪተኛ ስለነበር እንጂ። ወያኔ ባለፉት ሁለት ወራት ዶክተር አቢይ ያሰማቸውን የፍቅር መልእክቶች እያሰማና የህዝብን የልብ ትርታ እያደመጠ ቢሄድ ኖሮ ትግሬነቱም ሆነ አናሳነቱ ችግር ባልሆነ፣ በአጋዚ ሳይሆን በቄጠማ  መግዛት በተቻለው ነበር። የኦሮሞ ብሄርተኝነት ከዚህ የወያኔ አካሄድና አወዳደቅ ሊማር ይገባዋል።
ወደጀመርንበት ወደ የፌቡ ወዳጄ ዶክተር ገረፋ ቱሉ ወዳነሳው የኦፌኮ የምርጫ ዝግጅት ጉዳይ ስንመለስ፣ ዛሬ ኢትዮጵያችን ለምርጫ ፖለቲካ ዝግጁ አትመስለኝም። የማገገሚያ ወቅት ያስፈልጋት ይመስለኛል። ምናልባት የምርጫውን ወቅት ተጨማሪ ሁለት አመታት ሰጥቶ የዶክተር አቢይን አስተዳደር እንደ ሽግግር ዘመን ሥልጣን ለማየት መነጋገር ይኖርብን ይሆናል። ምናልባትም በጎማ ማህተሙ ፓርላም ምትክ ልክ በሰኔ 1983 አቶ መለስ ይመሩት የነበረውን ዓይነት የሽግግር ምክርቤት ያስፈልገን ይሆናል። የኢህአዴግ አስተዳደርና የሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች ምክርቤት ቅይጥ ። እንዲህ ዓይነት እሳቤ ለፈረንጆቹም ሆነ የነርሱን ቃል እንደ አስርቱ ትእዛዝ ለሚያንበለብለው ምሁር ባእድ ሊሆን ይችላል።  ሆኖም ከኢትዮጵያ አፈር የሚነሳ ለአለም የምናበረክተው የፖለቲካ ሳይንስ አበርክቶም ሊሆን ይችል ይሆናል። በህዝብ መድረክ ላይ እያሰብኩ ነው። አዲስም ነው። አታውግዙት፣ ተወያዩበት። ተጨንቀን፣ አምጠን እኛነታችንን እስቲ እናግኝ። አይዞን!
Filed in: Amharic