>

አብይን እንዴት ታየዋለህ? “እንደ ጠያቂዬ ነዋ!”

አብይን እንዴት ታየዋለህ? “እንደ ጠያቂዬ ነዋ!”

 ደረጄ ደስታ 
 አብይን እስኪበቃው ደብድቦ ወይም ቃል እስኪያጥረው ክቦ ከሚያናግረኝ ሰው እምጋተር ጅልም አይደለሁም። ኢህአዴግን ጠልቶ አብይን እየወደደ መከራውን እንደሚበላ “ከመረቁ አውጡልኝ ከሥጋው ጾመኛ ነኝ” እንደሚልም ሰው ረቂቅ አይደለሁም። አብይ እስካሁን ባጠፋው ሳይሆን ወደፊት ሊያጠፋ ይችላል ብሎ በትንቢትና በቀብድ እንደሚቃወም “አላልኳችሁም? አልሰማ አላችሁኝ እንጂ ነግሬያችሁ ነበረ…” እሚልባትን ያቺን የተባረከች ቀን በጉጉት እንደሚጠባበቅ ውድቀት ናፋቂ ዓይነት ነብይም አይደለሁም።  ይሄ ሰውዬ በትግርኛ ተናገረ ብለው እንዳበዱት በአማርኛ ተናገረ ብለው እንደፈነጠዙት ወይም ነገ ደግሞ ምናልባትም ሱሪ ለበሰ፣ ሸሚዙን አስተካክሎ ቆለፈ፣ ሻሂ ቡናም ሲጠጣ ታየ ብለው እንደሚገረሙት “ምን ብዬ ላንድቅሽ!” ዓይነት ሰዎችም አይደለሁም። እስኪ ከኢህአዴግ የተለየ ምን ነገር አለው? ምን አድርጓል? ፖሊሲው ህገመንግስቱ መቸ ተቀየረ? ዴሞክራሲያዊ ተቋማት መች ተገነቡ? የፕሬስ ነጻነት መች ተከበረ? አገሪቷን የመዘበሩት መች ለፍርድ ቀረቡ? የፍትህ ነጻነት የት አለ ተተተ ደደደ…እያሉ በሰከንድ 300ሺ መሠረታዊ ጥያቄዎችን እንደሚያንበለብሉ ፕሮፌሽናል ፖለቲከኞችም፣ ፖለቲካው ገብቶኝ መንገዱ የጠፋኝ ተቃውሞ ገብቶኝ ተቃዋሚ ያጣሁኝ ከርታታ አይደለሁም። ይሄ ሰው ለኦሮሞው ምን አድርጓል ብለው እንደሚበሳጩት? አገሩን ሁሉ ኦህዴድ በኦህዴድ ሊያደርገው ነው እንዴ ብለው እንደሚሰጉት? አማራውን አፈናቅሎ ጨረሰ ብለው እንደሚከሱት ወይም አገራችን ከ27 ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እሚል መሪ አገኘች ብለው “ኢትዮጵያዊነት” ሰበር ዜና መስሏቸው እንደሚያወድሱት፣ ወይም የአገር ሀብት ይሸጥ አለ፣ ድንበር ቆርሶ አገር ገምሶ ሰጠ እያሉ እንደሚከሱት ወዲያና ወዲህኞች አይደለሁም።
እንደው አሜሪካኖቹ ከጀርባው ቢኖሩ ነው እንጂ ይሄ ሁሉ አብይ አይደለም ሊሆንም አይችልም ብለው በኢትዮጵያዊነ ተስፋ እንደቆረጡት፣ ወያኔዎቹ በጥንቃቄ የተከሉት አሳምረው እሚጫወቱት ድራማ ነው ብለው ደደቢቶቹን ከሼክስፒር በላይ በፈጠራ ችሎታቸው የታወቁ ጸሐፊ ተውኔት አድርገው እንደሚያደንቁ ሤራ ናፋቂ፣ ውለታ ደፋቂ፣ ጥረት አዋዳቂ፣ ጠርጣሪ መንጣሪም አይደለሁም። አቅማቸውንና ልባቸውንና ሳይመዝኑ፣ ከምኑም ከምኑም ሳይሆኑ፣ ይሄ ሰውዬ መደገፍ አለበት ወይስ የለበትም እያሉ ባልተጻፈ ህገመንግሥታቸው አንዱን በከጂነት አንዱን በነጻ አውጪነት ፈርጀው ስሜት እንደሚቀጡ ስም እንደሚወቅጡ አድማ ጨማቂ፣ ትግሉን ከነጣቂ ጠባቂ አድርገው ራሳቸውን እንደሾሙ ዜጎችም ምርጥ ዜጋ ነኝ ብዬ አላስብም።
ከላይ ከዘረዘርኳቸውና አይደለሁም ካልኳቸው ውስጥ አንዷን መዘው፣ አንተ ማለት ይህኛውን ነህ ብለው እንደሚመድቡኝ፣ ከአብይም አንዷን ነገር መዝዤ እንዲህ ናቸው ብዬ ለማለት፣ በላዩ በላዩ እሚያደርጉት ነገር እየፈጠነብኝ ተቸግሬያልሁ። ሰውየው ለኔ ድንገት ናቸው። አገር ሳይዘጋጅ ኢህአዴግም ተቃዋሚም፣ ህዝቡም ሳይዘጋጅ ድንገት ዱብ ያሉ፣ ያልተጠበቁ ክስተት ይመስሉኛል። ገና አንገዋለን ያልጨርስናቸው ተዘጋጀተን ያልጠብቅናቸው ጊዜውን ይውለዱት ወይ ጊዜው ይፍጠራቸው ወይ ጊዜውን ይጥለፉት ጊዜው ይጥለፋቸው ገና አልገባኝም። የገባኝ አንድ ነገር ቢኖር ሰውየው አገርና ሰው እያነጋገሩ ነው። ሰውየው ሰው ቢሆኑም ባሁኑ ይዞታቸው ግን ምክንያትና ክስተት እንጂ ራሳቸው ሰው ሆነው የታዩ አልመሰሉኝም። አብይ አጀንዳ ናቸው። ሰው “ለውጥ አለ ወይስ የለም?” እያለ መነጋገሪያ አድርጓቸዋል? የተስፋ መልዕክት ይዘው የመጡ መልዕክተኛ እንጂ እሳቸው ራሳቸው ተስፋ አይደሉም። አብይ አጋጣሚ ናቸው። እሳቸውም፣ ተቃዋሚም ሆኑ ደጋፊዎቻቸው ይህን አጋጣሚ ቢያውቁት ጥሩ ይመስለኛል። ያወቀ ይደራጅበታል። አገሬን ያለ አገሩን ፍቅር ያለ ፍቅሩን አንድነት ያለ አንድነቱን ይሰራበታል። መጠርጠር የግድ ከሆነና አስፈላጊ ከሆነ ግን ደካማዎችና መሠሪዎች ጠልፈው ይጥሉታል ብቻ ሳይሆን አብይ ራሳቸውም ቢሆን ምክንያት መሆናቸን ዘንግተውት ደካማ ሰው መሆን የጀመሩ ቀን ራሳቸውን ጠልፈው ሊጥሉ ይችላሉ ብሎ መዘጋጀት ይጠቅማል። ውግዘት ብቻ ሳይሆን ያልተገራ ውዳሴም ሰው መጣሉ መች ይቀራል። በኛ መካከል ይቅር እንጂ እኛም እኮ የፈጠርነውን አሳብጠን በመጣል ማን ይችለናል። ሰውየው ዋጋ መክፈል አለመክፈላቸው ሊያከራክር ይችላል ይሁን እንጂ ግን  በአንድም ሆነ በሌላ በኩል ብዙዎች በየፊናቸው ታግለው ያገር ዋጋ የተከፈለባቸው ውድ አጋጣሚ መሆናቸውንም አለመዘንጋት ነው። እንግዲህ እኔ እንዲህ አልኩ እናንተ ምን ይመስላችኋል?
Filed in: Amharic