>

ታላቁ አሊ ሑሴንም  ምስጋና የሚገባቸው  የአማራ ድምጽ ናቸው! (አቻምየለህ ታምሩ)

በትናንትናው እለት የአማራ አገር አቀፍ ንቅናቄ በባህር ዳር ከተማ የመመስረቻ ጉባኤውን ሲያደርግ አማራ በፋሽስት ወያኔና  በርዕዮተ ዓለም አጋሮቹ ግፍና መከራ ሲደርስበት ድምጽ የሆኑለት ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም   ተመስግነዋል። ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም የምንጊዜም የግፍ አባት የሆነው ፋሽስት ወያኔ በአማራ ላይ ጥቃት ሲፈጽም ለተጎዱት ወገኖቻቸው  ቀድሞ  ደራሽ ናቸው። ከፍ ያለ ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል። በባህር ዳሩ ጉባኤ የተደረገው የዶክተር ያዕቆብ ምስጋና  አማራ ውለታ የማይረሳ፣ የበላበትን ወጭት የማይሰብር፣ የክፉ ቀን ደራሾቹን የማይዘነጋና የዋሉለትን በጎ ተግባር ትልቅ ትንሽ ሳይል ሲያስታውስ  የሚኖር  ሕዝብ መሆኑን በዚህ ዘመን በልጆቹ  ማስመስከሩን እንደ ማሳያ ተደርጎ የሚቀርብ ነው።
ልክ እንደ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ሁሉ በአማራ ላይ  ፋሽስት ወያኔና የርዕዮተ ዓለም አጋሮቹ  ያደረሱበትን ግፍና መከራ በመመስከርና በሚያስደምም ግጥሞቻቸው ለአማራ  ድምጽ የሆኑ  ሌላ የጉራጌ ተወላጅ ኢትዮጵያዊ አሉ። ስማቸው አሊ ሑሴን ይባላሉ።  አቶ አሊ ሑሴንም ልክ እንደ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ሁሉ ለአማራ ድምጽ ስለሆኑ ምስጋና ይገባቸዋል። ከዚህ በፊት ስለ አሊ ሑሴን በጻፍሁት  አንድ ትንሽ ማስታወሻ ለወገናቸው ድምጽ ስለሆኑ ማመስገኔን አስታውሳለሁ።
አቶ አሊ ሑሴን ባሁኑ ሰዓት ካናዳ የሚኖሩና «ኢትዮጵያ» ብለው ትግል  በማድረጋቸው  «አማራ ነህ» ተብለው  በሞቃድሾ የአማራን ግፍና በደል  የተቀበሉ ሰው ናቸው ። ይህንን ግፍና በደልም ዶክመንተሪ ሰርተው፤ መጽሐፍ ጽፈው፤ በተለያዩ ቦታዎችም ንግግር በማድረግ ለአለም ሁሉ አሳውቀዋል።
እነ መለስ ዜናዊ ሞቃድሾ ጽሕፈት ቤት ከፍተው ኢትዮጵያን ሲያጠቁ በሲያድ ባሬዋ ሶማሊያ እስር ቤቶች ውስጥ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይና አማርኛ አስተርጓሚ ሆነውም ይሰሩ ነበር። አቶ አሊም ከደርግ እስር ሸሽተው ወደ ሶማሊያ ተሰደው ሞቃዲሾ እስር ቤት በገቡበት ወቅት በነመለስ ዜናዊ ጥቆማ «አማራ ነህ» ተብለው በተለየ እስር ቤት እንዲታሰሩ ተደርገው የተፈጸመባቸውን ግፍ፤ በሌሎች «አማራ ናቸው» በተባሉ ላይ የተካሄደባቸውን አሰቃቂ ጭፍጨፋ፤ በሴት እህቶቻችን ላይ የደረሰውን ከአእምሮ በላይ የሆነ ዘግናኝ ጭካኔ ዝርዝር በሰሩት ዶክመንታሪና በመጽሀፋቸው ነግረውናል። በተለያየ ጊዜ በሰጡት ቃለ መጠይቅም አቶ አሊ ሶማሊያ ውስጥ «ሸለምቦት» በተባለ ቦታ «የአማራ» ተብሎ በተከለለው እስር ቤት ውስጥ ስለተፈጸመው ግፍ ዛሬም ድረስ ህመሙ እየተሰማቸው ይናገራሉ።
እኒህ የአማራ ባለውለታ ላለፉት ሰላሳ በላይ አመታት ስለ አማራ ሲጮሁ ኖረዋል። ከነቤተሰቦቻቸው በአማራ ላይ የተፈጸመውን ግፍና በደል ተናግረው አይደክሙም! «ኢትዮጵያዊ ነኝ» በማለታቸው «አማራ ነህ» ተብለው የደረሰባቸው ግፍና በደል የአማራ ድምጽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል! በየተገኙበት መድረክ ሁሉ አጥንታቸው ድረስ የሚሰማቸውን የአማራ ግፍና በደል ከፍ አድርገው ይናገራሉ!
በደልና ግፍ የሕይወቱ ገጽታ የሆነው አማራ ጠላቱን ፋሽስት ወያኔን  «መንግሥቴ» ብሎ  ካራጁ ኋላ እየተከተለ ላለፉት ሀያ አስምት አመታት ዝም በማለቱ ይነሳ ዘንድም ከአመታት በፊት እንዲህ ሲሉ ተቀኝተው ነበር፤
የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳ ነበረ ተረቱ፣
ምነዋ ዘንድሮ ተወጊው ሲረሳ ወጊ አለመርሳቱ፤ 
ከዚያም አልፎ ተርፎ የተወጊው ጉዳይ የከበደው ነገር፣
በደሉን ረስቶ የወጋውን ጩቤ ልሶ ስሞ ማደር!
አቶ አሊ ዛሬም ስለ አማራ መናገራቸውን አላቆሙም። በ2007 ዓ.ም.  በለንደን  በአንድ ክብረ በዓል  ተገኝተው  «እንቁፍቱ» እና  «ፈርዶበት አማራ!»  በሚል ያቀረቧቸውን ግጥሞች ከዚህ በፊት አትሜያቸው ነበር።
ለማታውቁት «እንቁፍቱ»  ሐረር ውስጥ   የሚገኝና  አማራ ከነነፍሱ በፋሽስት ወያኔና በኦነግ ሰው በላ ወታደሮች የተጣለበት የማይሞላ ገደል ነው።
ልክ እንደ ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ሁሉ  ድምጽ አልባ ለሆነው አማራ ድምጽ የሆኑትን  የታላቁ  አሊ ሑሴንን ውለታም  አማራው  ዘወትር ሲያስታውስ ይኖራል። ድምጽ ሆነው ለወገናቸው የዋሉትን ውለታ መቼም  የማይዘነጋውና  ከባለውለታወቹ  ተርታ  ቀዳሚው  በመሆናቸው ሁል ጊዜም እናመሰግናቸዋልን።
Filed in: Amharic