>

አገር ለድጋፍ ነቅሎ ቢወጣስ? (ደረጄ ደስታ)

የወያኔ ሃርነት ትግራይን መግለጫ አነበብኩት። የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀበት አገር ይህን ሲያይ ምን ይል ይሆን? ንድድ አለኝ። አደባባይ እማልጽፈውን ይህን ቁጣ በውስጤ አጉተመተምኩ። ደግሞ አሁን ምን ሆን ልትሉ ነው?
ኢትዮጵያ እሚለው ስም ደጋግሞ መጠራት አንገሸገሻችሁ?
የእስረኞች መፈታት እናንተን መልሶ አሰራችሁ?
የሰላም የእርቅና የይቅርታ ጥሪው የጦርነት ነጋሪት መስሎ ታያችሁ?
እናንተ ተዋግታችሁ ተሰውታችሁ ያስገነጠላችሁትን ህዝብ ሌላው በፍቅር ቢመልሰው ቀፈፋችሁ?
27 ዓመት ሙሉ ተቧድናችሁ የዘረፋችሁት የቀጣችሁት የበደላችሁት ህዝብ ይቅር ብያችኋለሁ ቢል አነሳችሁ?
አጋፋሪዎቻችሁ ከችሎት ይልቅ ከወግ ማዕረግ አደባባይ ቆመው ኒሻን በኒሻን ሲሆኑ በአደባባይ የተሰቀሉ መሰላችሁ?
አብራችሁ የወሰናችሁትንና ያልካዳችሁትን አሁንም ያልሻራችሁትን ውሳኔ አብይና ለማ በሚባሉ ትናንት በመጡ ልጆች ልታሳብቡ አማራችሁ? እስኪ ከአሁኑ መግለጫችሁ እንኳ አልቀር ያለውን ይህን ሐቅ ትኩር ብላችሁ  ተመልከቱት
የኢትዮጵያና የኤርትራን ጉዳይ አስመልክቶ የወሰነው ውሳኔ በመሰረቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ በኢህአዴግ የሚመራዉ መንግስት ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም በአጠቃላይ ለሁለቱ ሃገራት ወንድማማች ህዝቦች በተለይ ሲባል ስምምነቱን ያለቅድመ ሁኔታ በመቀበል ህዝባችንና መላዉ አበላችንን በማወያየትና በማሳመን እንድሁም ዓለም አቀፉን ማሕበረሰብ ከጎኑ በማሳለፍ ለተግባራዊነቱ ያላሰለሰ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በተለያዩ ምክንያቶች ላለፉት 18 ዓመታት ዘላቂ ሰላም ማረጋገጥ አልተቻለም። ስለሆነም የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያሳለፈዉ ዉሳኔ በመሰረቱ ከሰላም ፖሊስያችን ጋር የተጣጣመ መሆኑን በማረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል ዉሳኔ መተላለፉ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ደምድሟል።
ታዲያ እንዲህ ደምድማችሁ ስታበቁና ይህን ካላችሁ በኋላ ለመሆኑ ምን አንተባተባችሁ? አፈጸጸሙ -ለሚዲያ መነገሩ…በጥልቀት በመገምገም.. ትኩረት አድርጎ ማየት አለመቻሉ…ለጊዚያዊ መፍትሔዎች ቅድሚያ መስጠቱ…
-ስለሚሸጡ ድርጅቶችም ያላችሁት ይህንኑ ነው። ተመልከቱ-
“የኢህኣዴግ ስራ ኣሰፈፃሚ ኮሚቴ አሁን የገጠመንን ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመፍታት እንዲቻል ከመንግስት የልማት ድርጅቶችን መካከል ቴሌ፣ ኤሌክትሪክ ማመንጨዎች፣ ሎጀስቲክስና የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ከፍተኛዉ ድርሻ በመያዝ የግል ባለሃበቶችን ለማሳተፍ እንዲሁም የቀሩትን የልማት ድርጅቶች በከፊል ወይም በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ለማስተላለፍ የወሰነዉ ውሳኔ ከፕሮግራማችንና ፖሊስዎቻችን ጋር የማይጋጭ፣ ባለፉት ጉባኤዎቻችን እየተወሰነ የመጣና ወቅታዊ መሆኑን በማረጋገጥ ተቀብሎታል። “
ታዲያ ያልተቀበላችሁት የትኛውን ውሳኔ ነው? ህዝብ የተቃወመው ሽያጩን እንጂ አፈጻጸሙን አለመሆኑን አሳምራችሁ ታውቃላችሁ።
ለነገሩ ሶስት ቀን ቤት ዘግታችሁ የዶለታችሁትና በመግለጫችሁ ያልነገራችሁን አንድ ሤራ  አለ – የመግለጫችሁ ፍሬ ነገር እዚህ ውስጥ ተቀብራለች…  “ወቅታዊ ሁኔታዉን በፍጥነት ለማየት እና ለመገምገም የኢህኣዴግ ስራ አስፈፃሚ እና ምክር ቤት አስቸኳይ ሰብሰባ እንዲጠራ የህወሓት ማእከላዊ ኮሚቴ ይጠይቃል።”
በዚያ ስብሰባ ምን ልትሉ፣ ምን ልጥሉ፣ ምን ልታነሱ ምን ልትመልሱ ነው?
አገር ይህን ሤራ በዝምታ ሊያየው አይገባም። ሰላም ወዳድና የመጣው ለውጥ ተስማምቶኛል፣ ከለውጡ መሪዎች ጋርም እቆማለሁ እሚል የኢትዮጵያ ህዝብም በአስችኳይ ድጋፉን በሰልፎችና በስብሰባዎች በያለበት ሆኖ መግለጽ ይኖርበታል። የቄሮም ሆኑ የፋኖ ጀነራሎች ወይም የለውጡ አካል ነን እሚሉ የኢህአዴግ ሰዎች ሳይቀሩ አገርን ለሰልፍ ጠርተው ይህን ሤራ በድጋፋቸው ቢያከሽፉት የተቀመመውን መርዝ ቢያረክሱት ምን ይመስላችኋል? “አብይ ሊደገፉ ይገባችኋል” እያላችሁ ስታስቸግሩ የነበራችሁትስ ምን ትላላችሁ?  የአብይ ግማሽ መንገድ ያልተዋጠላችሁስ ብትሆኑ ያቺኑ 50 ከመቶ ልታጡ አይደል? መፍትሔው የፖለቲካ ብልህነት እና ህዝባዊ ድጋፍ ይመስለኛል። ኋላ ይቆጫል! ሰዎቹ እንደሁ ይሉኝታ እሚባል አልፈጠረባቸውም።
Filed in: Amharic