>
5:30 pm - Wednesday November 1, 0389

አብን (NMA) ለብአዴን እየመጣለት ነው ፤ ወይስ እየመጣበት?  (በቹቹ  አለባቸው አበበ)

 (የግል አመለካከት)
አብን (NMA) ለብአዴን እየመጣለት ነው ፤ ወይስ እየመጣበት? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ሊመለስ የሚችለው አብን ብአዴንን እንዴት ይመለከተዋል? ብአዴንስ አብንን እንዴት ይመለከተዋል የሚሉትን ቁም ነገሮች በጥልቀት በመመልከት ነው፡፡ ባለፈው እንዳልኩት በአማራ ክልልና በተቅላላ በአማራህዝብ ዘንድ፤ የቀጣዩ ፍልምያ በማንና በማን መካከል እንደሚሆን ፤በዚህ ፍልምያ አሸንፎ ለመውጣት ወሳኝ ጉዳዮች ምን ምን እንደሆኑ ማንሳቴን ታስተውሳላችሁ፡፡ ይህ ፖለቲካዊ ፍልምያ በሁለት ወንድማማቾች፤ ግን ደግሞ ፍጹም ተጻራሪ አመለካከት ባላቸው ወንድማቾች መካል እንደሚካሄድ ጠንካራ ፍልሚያ መሆኑን መቸም ቢሆን አንዘንጋ፡፡
በዝች አጭር መጣጥፌ ላነሳ የፈለግኩት ዋናው ቁም ነገር፤ በዛሬው እለት አብን( አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ)፤ በትናንትናው ዕለት ሊቀ መንበሩን መርጦ ዛሬ ደግሞ 12/ከዛ በላይ የሚሆኑ  አመራሮችን በመምረጥ  ጉባኤው በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ ስለሚሰጡት አስተያቶች እኔም እንደ አንድ አማራ የግሌን ስሜትና አስተያየት ለመግለጽ በመፈለጌ ነው፡፡ በሚዲያ እንደተከታተልነው፤ አዳራሹ ጢም ብሎ  ሞልቶ፤ ቆሞ የታደመው ሳይደክም  የአዲሱ የአማራ ፓርቲ መቋቋሙን  ሲመለከት የነበረው ስሜት ይገርማል፡፡ በዚህ አዳራሽ እንዲህ ያለ ሌላ በደስታ የተሞላ መድረክ ተካሂዶ ስለማወቁ ቡዙም ትዝ አይለኝም፤ በተለይም በብአዴን የፖለቲካ መድረኮች ፤ ከክልል እስከ ዞንና ወረዳ አመራር የሚሳተፍበት አመታዊ ግምገማዎችን ስናደርግ ካልሆነ በስተቀር፤
እንዲህ ያለ ፊቱ በደስታ የፈካና በሙሉ ስሜ የፖለቲካን አጀንዳ ሚከታል የተሰብሳቢ ብዛት አይቸ አላውቅም፡፡ ምን አልባት በዚህ 2 አመት ውስጥ ነገሮች ተሻሽለው ካልሆኑ በስተቀር፤አባል ለመሰብሰብ እንኳን በሚፈለገው መጠን (ቁጥር) ማግኘት ከባድ መሆኑን ነው የማውቀው፡፡ የዛሬው ገራሚ ነው፤ በርግጥ ይህ ፓርቲ አዲስ በመሆኑ ተስፋ ያደረጉት በብዛት እንዲህ በደስታ የተሞላ ተሳታፊ ቢታይበት ገራሚ አይደለም፤ ጥያቄው እሄንን ዛሬ በደስታ ተሞልቶ መድረኩን የተከታተለውን ደጋፊ እስከዘለቄታው ከድርጅቱ ጋር እንዴት አብሮ ማዝለቅ ይቻላል ነው፡፡ የብአዴን መድረኮች  ዛሬ እንዲህ ሳስተው ቢታዩ አይፈረድባቸውም፤ የአባላት ለረዥም ጊዜ ከድርጅቱ ጋር መቆየትና በድርጅቱ አሰራር ደስተኛ ያልሆኑ አባላት መበራከት፤ እንዲሁም በድርጀቱ ላይ ተስፋ የመቁረጥ ዝንባሌ እየታየ ስለመጣ ሊሆን ይችላል መድረኮቹ ያን ያክል ሳቢ እያልሆኑ የመጡት፤ ሁኖም በአንድ ወቅትም ቢሆን በብአዴንም እነዲህ አይነት ደማቅ መድረኮች ነበሩ፡፡ ፡፡
ወደ ተነሳሁበት ቁም ነገር ልመለስ፡፡ አብን ለብአዴን መጣለት ወይስ መጣበት ፤የሚው አባባሌ፤ ሁለቱ ድርጅቶች ( ማለትም አብንና ብአዴን )፤ካሁን በኃላ እንዴት ይተያዩ ይሆን? እንዴትስ ነው አንዱ ሌላውን መመልከት ያለበት በሚሉት ነጥቦች ዙሪያ የግል አስተያየት ለማቅረብ ወድጃለሁ፡፡ እናንተም ወዲህ በሉና እንወያይበት፡፡ እኔ እንደማምነው፤ ካሁን በፊትም እንደገለጽኩት አብን ለብአዴን ” መልካም አጋጣሚና ስጋትም ” ነው ይዞለት የመጣው፡፡ እንዴት ስጋት ሊሆን እንደሚችል ባለፈው ስላስብራረሁ አሁን ስጋቱን ገጽታ አልደግመውም፤ በዚህ ክፍል የአብን መምጣት ለብአዴን ያለውን በጎ ገትታና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ብቻ ማትኮሩን መርጫለሁሁ፡፡
አብን እንዴት ለብአዴን እንደ ጥሩ አጋጣሚ ሊታይ ይችላል? በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ ፤ የአማራ ህዝብ ደግሞ በተለይ፤ በኢህአዴግ እንደ አጠቃላይ፤ከአማራ አንጻር ደግሞ በተለይ በብአዴን ላይ የነበረው እምነቱ እቀነሰ መጥቷል፤ በስርአቱ  ላይ ደስተኛ አይደለም፤ እሄ ምንም ምርምር አያስፈልገውም፤ ኢህአዴግና ብአዴንም በድፍረት የተናገሩት ሀቅ ነው፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ይህ ማለት የኢትዮጵያ ህዝብ በአጠቃላይ፤ በተለይም ከእኛ አንጻር ደግሞ የአማራ ህዝብ የስርአት ለውጥ ይፈልጋል ማለት ነው፤ ይህ የለውጥ ፍላጎት ደግሞ ጥገናዊ አይመስለኝም፤መሰረታዊ ነው፡፡ መሰረታዊ ነው ስል ምን ማለቴ ነው? ኢህአዴግንና ብአዴንን ከምድረ ገጽ ማጣት ማለት ላይሆን ይችላል፤ ይልቁንስ አሰራራቸውን ሙሉ በሙሉ ህዝቡ በሚፈልገው መንገድ መቀየርም ሊሆን ይችላል፤ ይህ ለውጥ ግን የድርጅቶቹን ሙሉ በሙሉ አንፈልግምመ እስከማለትም የመሄድ እድሉ ዝግ አይደለም፡፡ ለጊዜው እኔ እንደማስበው ኢህአዴግም ሆነ ብአዴን በለውጡ ውስጥ የራሳቸው የሆነ ወሳኝ  ድርሻ እንደሚኖራቸው ፡፡
ወሳኙ ጥያቄ ግን፤ ብአዴን የዚህ የለውጥ አካል ሁኖ በአማራ ፖለቲካ የሚቀጥል ከሆነ ( ለጊዜው የመሪነት ሚናውንም ይዞ ሊቀጥል ይችላል) ፤ አዲሱን፤ በወጣት ሙህራን የተመሰረተውን አማራዊ ድርጅት (አብንን) እንዴት ሊያስተናግደው ይገባል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡ እንግዲህ በኢህዴን /ብአዴን ቆየት ያልን ታጋዮች እንደምናውቀው፤አብዮታዊ ዲሞክራሲን ስንጠመቅ፤የስርአቱ ምሰሶዎች፤ ደጋፊዎችና፤ወላዋዮች ፤እንዲሁም አደናቃፊፊዎች የሚባሉ መደቦች ነበሩ፤ ለነገሩ አሁንም አብዮታዊ ዲሞክረሲ የኢህአዴግ መርህ ስለሆነ የመደብ ፍረጃው እንዳለ ነው፡፡ ሌሎቹን መደብ ፍረጃዎች ለጊዜው ልተዋቸውና ፤ ለዛሬው በአብዮታዊ ዴሞክራሲ መስፈርት መሰረት የወላዋዩን መደብ ሁኔታ ላንሰ፡፡ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ የወላዋይ መደብ ውስጥ የሚመደቡት በከፍተኛው ሙህርና በከፍተኛው ባለሀብት ዙሪያ ተሰባሰቡት ወገኖች ናቸው፡፡ አሁንም ለዛሬው ሀብቱን ልተወውና የወላዋዩን ሙህር ጉዳይ ላንሳ፡፡ እንደ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እምነት፤ የሙህሩ መደብ በሁለት ተከፍሎ ሊታይ ይገባል፤ አብዮታዊ( ተራማጅ) እና ወላዋይ ፡፡ ወላዋዩ  ሙህር  በአብዛኛው የከፍተኛውን ሙህር መደብ ይወክላል፡፡
በዛሬው እለት ፤ ስለ ሙህሩ ወላዋይነትና አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለማንሳት የፈለግኩት፤ ዛሬ የአብን አመራር ናቸው ተብለው የተመረጡት ሁሉም አመራሮች  ፕሮፋይል ስመለከት፤ ሁሉም ማለት ይቻላል፤ የትምህርት ደረጃቸው ከማስተርስ ዲግሪ( የአሲስታንስ ወይም ተባባሪ ፕሮፌሰርነት) ደረጃ የደረሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ወንድሞቻችንን ደግሞ በአቢዮታዊ ዲሞክረሲ መነጽር ስመለከታቸው ፤ የከፍተኛውን ሙህር ደረጃ የተላበሱ ሁነው አገኘኃቸው፡፡ ያላወቅኩትነገር ቢኖር፤ እነዚህ ወጣት ሙህራን፤ ከአብዮታዊው ሙህር መደብ ናቸው ወይስ  ከወላዋዩ? እነሱው ይመልሱት፤ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ እይታ ግን ግን ከሁለቱ አንዱን ናችሁ፡፡ አይ አሁንስ የእኔም መደብ ሊምታታብኝ ነው፡፡ እኔ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ስጠመቅ፤ የ8ኛ ክፍል “ሙህር” ነበርኩ ፤ስለሆም ከዝቅተኛው መደብ ስለምመደብ ስለ ወላዋዮቹ ስዘረጥጣቸው ብውል አይከብደኝም ነበር፤ ምን አገባኝ እኔን በወቅቱ አይመለከተኝ፤ በል የተባልኩትን ማለት ነበረብኝ አልኩት፡፡ አሁን ደግሞ እሄ ከፍተኛ ሙህር የሚባለውን ነገር ልረግጠው ነው  መሰለኝ፤ ከየትኛው የሙህር መደብ እንደምፈረጅ ግን እስካሁን አላወቅኩትም(ተራማጅ ወይስ ወላዋይ እሆን ይሆን)? እስኪ ቲንሽ ልቆይና እወሰናለሁ፡፡ በርግጥ እኔ ደረጃየን እስክወስን ድረስ አብየታዊ ዲሞክረሲ በአገራችን ቁሞ ካልተበቀኝ፤ እራሴንን መመደብ አይጠይቀኝም፡፡
ለሁሉም እናንተ አብን ወጣት የአማራ ሙህራን ፤በናንተ ድርጅት በኩል እንዲህ የሙህራን ፍረጃ ደንበር አለው እንዴ? እስኪ መረጃ ወዲህ በሉ፤በእኛ ቤት ግን ሙህርን እንዲህ ነበር የምንፈርጀው፡፡ የፖለቲካ ፍልስፍናችሁስ ምንድን ነው? Social democracy? Liberal Democracy ? Revolutionary Democracy? ( yekereta), ወይስ ሌላ? ነገራችሁን ወዲህ በሉና እንተቻችሁ፡፡ መቸም ወጣት ትችት አይፈራ፤ ለነገሩ እንኳን የኔ ቢጤውን ደካማ ስብስብ ትችት፤ሌላም መአት ቢመጣ፤ የመጣውን ጣጣ ሁሉ ለመቀበል ወስናችሁ አይደል አብንን መመስረታችሁ፤ እንዴው እኔ መጠየቅ ለምዶብኝ አንጅ፡፡ መቸም  ዝም ብየ ባላውቃችሁም፤ በሩቁ ስመለከታችሁ፤ አያያዛችሁን ስመለከተው፤ ዝም ብየ ያለ መረጃ በአንድ ነገር እርግጠኝነት ይሰማኛል፤ እሄውም እናንተ ወላዋይ ሙህር ሁናችሁ፤ የአማራን ህዝብ ዳግም አንገት እንደማታስደፉት፤ እናንተ ወጣት ሙህራን አማራ የአማራ ልጅ አይደላችሁ? አዎን አማራ ደግሞ እንዲህ ይላል ” የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ” ፤ አይደል እንዴ? ስለሆነም ለአማራ ህዝብ የገባችሁትን ቃል እንዴት እንደምታከብሩ ልንከታተላችሁ ነው፤ ቃል እዳ ነው፡፡
እኔ እንደማምነው፤ ይህ አሁን እያነሳሁት ያለው ነጥብ ለብአዴንም ሆነ ለ አብን ትልቅ መልእክት አለው፡፡ ሰውን እንደ ሰው በአመለካከቱ ከመታገል ይልቅ የትምህርት ደረጃውን መሰረት አድርገን በመፈረጅ ከጎናችን ለማሰለፍ የሚደረገው ጥረት የሙህር ድሀ ሊያደርገን ይችላልና ፤እረጋ ተብሎ እንደገና ቢፈተሸ ጥሩ ነው፡፡ አዲሶቹ የአማራ ሙህራንም አብዮታዊ ዴሞክራሲን ሙህራዊ ፍረጃ እንዴት proof or disproof  “እንደምታደርጉት ልናያችሁ ነው፡፡ ለነገሩ  አማራ አንድ ነገር ሊሰምር እንደሚችል ሲጠረጥር  “የሚያድግ ጥጃ ከገመዱ ይላያል ይላል” ብሎ ይተርታል፤ የነዚህ ወጣቶች አያያዝም ወላዋይነት ከባድ ፈተና የሚሆንባቸው አልመሰለኝም፡፡ ሁኖም እንዳንቸኩል ቲንሽ እንታዘባችሁ፤ ሁናችሁም አሳዩን፤ያኔ ደግሞ ትዝብታችንን እንሰጣለን፡፡
እንግዲህ ዛሬም ብአዴን ካወቀበት፤ በእኔ እምነት  የአብን  መወለድ ለአማራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ለብአዴንም እጅግ ይጠቅመዋል፡፡ ለምን?  እንዳልኳችሁ በአሁኑ ወቅት የአማራ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል፤ የለውጥ ፍላጎቱ ደግሞ ጥገናዊ ሳይሆን መሰረታዊ ለውጥ ነው፤ ይህ ማለት ግን ብአዴንም የለውጡ አካል መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤ እንዴውም ብአዴን ቅን ከሆነ የለውጡ ግንባር ቀደም መሪ የመሆን አቅምና ችሎታ ይኖረዋል፡፡ ችግሩ ግን ፤ካሁን በኃላ ብአዴን የአማራ ህዝብ የሚፈልገውን ሁለንተናዊ ለውጥ ለብቻው ለማምጣት አይችልም፤ ይከብደዋል፤ በሂደትም አቅመሙ እየተጠናከረ ከመሄድ ይልቅ እየተዳከመ መሄዱ አይቀርም፤ እሄን የምለው እኔ በወቅቱ ብአዴንን ስላኮረፍኩት አይደለም፤ በፍጹም አይደለም፤ ለወደፊቱም በኩርፊያ ያልሆነ ነገር አልልም፤ ነገር ግን  አሁን በአገሪቱም ሆነ በተለይም በአማራ ክልልና በአማራ ህዝብ ዘንድ ያለው  እተከሰተ ያለውና ለወደፊቱም ተጠናክሮ የሚከሰተው ነባራዊና ህሊናው ሁኔታ፤  የኢህአዴግና የብአዴን ነገር እንደዛ እንደሚሆን ያለ ጥርጥር ስለሚያመላክት ነው፡፡ ስለሆነም አሁን ባለው ሁኔታ ብአዴን ለጊዜውም ቢሆን ከጎኑ አብሮት የሚሰራ አጋዥ ወንድመ/ እህት  አማራዊ ድርጅት ያስፈልገዋል፡፡ለዚህ ጉዳይና መጣኙ ደግሞ ለጊዜው ብቸኛው  አማራጭ አብን ሁኖ መጥቷል፡፡ ስለሆነም ብአዴን ሆይ፤አብንን እንደ መጣልህ ወንድም/ እህት እንጅ እንደመጣብህ ባላንጣ እንዳትመለከው፤ በበጎ ተመልክተህ ተቀበለው፤ እንኳንም ደስ አለህ በለው፤ በፍጹም አብን ላንተ ጠቃሚ ነው፤ ከቡዙ ጉድ ሊገላግልህ ይችላል፤ ቡዙ ችግሮችህን ሊያቃልልህ ይችላል፡፡
ነገር ግን ብአዴን እሂንን ወርቃማ እድል ሳይጠቀምበት ካሳለፈው፤ ከማንም በላይ ትልቁ ተጎጅ የሚሆነው እሱው  እራሱ ነው፡፡ብአዴን አብን ን  በደስታ ተቀብሎ፤በነጻ ምርጫ ያሸነፈ አማራን ያስተዳድር ብሎ ከወሰነና ይህን በተግባር ካጋገጠ፤ብአዴን ቢያንስ እስከዛሬ የሰራቸውን ስህተቶች አረመ፤ከአማራ ህዝብ ጋርም ለመግባበት መንገድ ጠረገ ማለት ነው፤ በአማራ ታሪክም አንድ ድንቅ አማራዊ ታሪክ ጽፎና  አስመዝግቦ አለፈ ማለት ነው፡፡ ይህንን በጎ ነገር ማድረግ ካልቻለ ግን፤ ብአዴን አወዳደቁ ልክ እንደ ህውሀት እንደሚሆን አትጠራጠሩ፡፡ ዛሬ ህውሀት እንዲህ ወዳጅ አልባ ሁኖ የቀረው ለምንድን ነው? ሲነግሩት ባለመስማቱና ከኔ በላይ ለአሳር በማለቱ አይደለምን? እና ብአዴን እሄን አሸማቃቂ ታሪክ በራሱ ላይ ደርሶ መመልከት ይፈልጋል ? መሆን የለበትም፡፡ ãለ እንዴውም  ዘነጋሁት እንጅ ህውሀት ይሻላል፤ ህውሀት እኮ ቢያንስ ሽማግሌዎች አሉት፤ አይዞህ ይሉታል፤ያላቅሱታል፤ያጽናኑታል፡፡ ብአዴን እኮ ሽማግሌዎቹም ጥለውት ሂደዋል፡፡
ስለሆነም የብአዴን ብቸኛ እድል ከአብን ጋር የአማራን ወጣት መጋራት/ መጫረት ነው፤ የአማራን ወጣት ከአብን ጋር ለመጋራት ደግሞ፤ ብአዴን ፍጹም የሆነ  ዴሞክራሲያዊ የውድድር መድረክ መፍጠር አለበት፤ እሂንን እድል በመፍጠር ዛሬም ብአዴን በአማራ ፖለቲካ የመቆየት እድሉ (እንደ ለመደውና እንደድሮው በብቸኝነት  እንደ ዋርካ ተንሰራፍቶ የመቀጠል እድሉ እጅግ የጠበበ ቢሆንም)፤  ዛሬም ቢሆን እነደሚኖር መገንዘብ ይገባል፡፡ እሂንን እድል ብአዴን መጠቀም ካልቻለ ግን አወዳደቁ ጥሩ ላይሆን  ይችላል፡፡ ስለሆነም ደጉ የአማራ ህዝብና መሬት አይደለም ብአዴንንና አብንን ሌሎች አማራዊ ድርጅቶችንም የማስተናገድ ብቃትና ችሎታ ስላለው፤ መግባባት የሰለጠነና የተረጋጋ ፖለቲካዊ ባህል በክልለቸን እንዲሰፍን ብአዴን የቀዳሚነት ድርሻ ውን ሊወጣ ይገባል፡፡ብአዴን እሂንን እርምጃውን መጀመር ያለበት ደግሞ አሁኑኑ አብንን እንኳንደህና መጣህ ብሎ በመቀበልና በሂደት አስፈላጊውን መንግስታዊ ድጋፍ በመሰጠት ጭምር ሊገለጥ ይገባል እለለሁ፡፡
የአብን ሰዎችስ እንዴት ናችሁ? ሰላም ነው፤መልካም ፤ እናንተስ ብአዴንና የብአዴንን አባለት እንዴት ነው የምትመለከቷቸው? ለወደፊቱስ በምን መልኩ ነው ልትቀርቧቸው የተዘጋጃችሁት? እንዴው ለመሆኑ እናንተስ ለብአዴን “እንደመጣችሁለት ነው፤ ወይስ  እንደመጣችሁበት የምታስቡት ?”
ከላይ ብአዴን ላይ ሰፋ አድርጌ የገለጽኩት እንደ ትልቅ ወንደም ፤ አደራውና እዳው ከናንተ ይለቅ  እሱ ላይ ጠንከር ማለት ይገባዋል ብየ ስለማምን ነው፡፡ ይሁን እንጅ እናንተም በልካችሁ የሚጠበቅባችሁ ነገር እንዳለ ማስገንዘብ እፈልጋለሁ፡፡ ብአዴን የናንተው ወንድሞቻችሁና አህቶቻችሁ ስብስበ ነው፤ መቸስ የብአዴንን ፖለቲካው ብትጠሉት፤ ከ1.5 ሚሊየን በላይ የሚሆኑት የብአዴን  ልጆች ግን የጎንደር፤የጎጃም፤ የወሎ፤ የሽዋ፤ የአዲስ አበባ፤ ወዘተ አይደሉ? እናንተ ከወዴት ናችሁ? ከዚሁ ፡፡ እንዴው የፈለገ ብአዴንን ብትጠሉ( የተማራችሁ ስለሆናችሁ ጥላቻ አያሸንፋችሁም ብየ አምናለሁ፤ እንዴው ለወጉ ነው)፤ እጣት ” ገማ ተብሎ ተቆርጦ አይጣል” የሚለውን አማራዊ ተረት እንዳትረሱት፡፡ ሲሆን ሲሆን ፤ ካመናችሁኝ ሁሉም የብአዴን አባለት በዚህ መልኩ የሚፈረጁ እንዳልሆኑ ማረጋገጥ እችላለሁ፤ ካላመናችሁኝ በሂደት ታዩታላችሁ፡፡ ስለ እውነት ግን አብዛኛው የብአዴን አባላት በተለይም ታችኛው እናንተ ከምታራምዱት አመለካት፤ በተግባር የተለየ አመለካት አለው ብየ አላምንም፤ ልዩነቱ አንድ ነው፡፡
 ብአዴን ውስጥ ጥብቅ የድርጅት ዲስፕሊን አለ፤ይህ ማለት አባላት የመሰላቸውን አመለካከት በነጻነት ማራመድ ገደብ አለባቸው ማለት ነው፤ ስለሆነም የብአዴን አባላት ብአዴን ውስጥ ሁነው፤ከድርጅቱ ዲስፕሊን ውጭ ነጻ ሃሳብ በአደባባይ ሊራምዱ እድሉ የላቸውም( ጠባብ ነው፤ በተለይም ከአዳራሽ ውጭ) ፤ በናንተ  ሁኔታ ግን እሄ በነጻነት ሰው የመሰለውን የመናገር ሰፊ እድል እንዳለው ይገባኛል፡፡ ይህ ሁኔታ በናንተና በአብዛኛው የብአዴን አባላት መካከል ያለውን የአመለካከት መመሳሰል ግልጥ ብሎ እንዳይታይ ግርዶሽ መሆኑን አውቃለሁ፤ እናንተም አባሉ እንዲህ በአደባባይ ሲቃወም ስለማትሰሙት ሁሉንም ባንድ ሙገጫ አሰገብታችሁ ትወግጡታላችሁ፤ እውነቱ ግን ያልከችሁ ነው፡፡ በናንተም ግን እንዲህ የብአዴንን አባል ብትመለከቱት አልፈርድም፤አባሉ በአዳራሽ የሚናገረውንና የሚያምንበትን ነገር ሁሉ፤ በግለጽና በአደባባይ ሲናገር ካልሰማችሁት፤ በጎ ምስክርነት ለመስጠት ጠንቋይ አይደላችሁ፡፡
የኔ ምክር አጭርና ግለጽ ነው፡፡ የብአዴንም ይሁን የአብን አባላት ባመኑበት ድርጅት ይታገሉ፤ከአንዱ ወጥቶ ከሌላው መሄድም ሊለመድ ይገባል፤ ቁም ነገሩ ሁለቱ ድርጅቶችና አባላቶቻቸው፤ በጠላትነትና በጎሪጥ መተያየት የለባቸውም፤ ሁሉም መነሻውና መዳረሻው የአማራን ህዝብ  እውነተኛ ጥቅም ማስጠበቅ ከሆነ፤ ምን በጎሪጥ የሚያስተያይ ነገር ይኖራል? የፖለቲካ ልዩነቱን በአማራ ህዝብ ፍርድ ቤት ማስፈረድ ይቻላል፤ ከዚህ ዘሎ ሂዶ አንዱ አንዱን አማራ የሚከስበት፤የሚያስርበት፤በክፉ የሚመለከትበት ሁኔታ ምን አመጣው? ካሁን በኃላ ይችን መንገድ የሚደግም ወገን ካለ መነሻና መድረሻው የአማራ ህዝብ ጥቅም ሳይሆን ሌላ ነገር አለ ማለት ነው፡፡
ትግላችን በእውነትም ለአማራ ህዝብ ሁለንተናዊ ጥቅም መረጋገጥ ከሆነ፤ ሰልጡንና ዳኝነት የሚችል ህዝብ አለን፤እሱ ፍርዱን እየሰጠ ልጆቹን ዙፋን ላይ ያውጣ፤  በሆነ ወቅት ከዙፋን የወረደ ደግሞ እነደገና በአማራ ባህልና ወግ መሰረት ምህረት ጠይቆ ከተፈቀደለት ዳግም ወደ ዙፋን ሊመለስ ይችላል፤ ካልተፈቀደለት ደግሞ  ከዙፋን እንደራቀ በአማራነቱ ብቻ ተደስቶ ይኖራል፤ በቃ እንዲህ በማድረግ አርያ እንሁን፤ ምክሬ እሄ ነው፡፡ ካሁን በኃላ ማንኛውም አማራዊ ድርጅት( ብአዴንን ጨምሮ)፤ በዚህ ህግና መርህ አልመራም፤ ካለ የአማራን ወጣት ” ያዝ ኩሊ ብየሀለሁ” ፡፡ ያዝ “ኩሊ” ማለት ምን ነበር፤ አስተውሱኝማ፡፡
መቻቻል፤ መደማመጥ፤ መከባበር፤ የወንድማማችነት ስሜት  የነገሰበት ዘመን ይምጣልን፤ አሜን በሉ፡፡
Filed in: Amharic