>

ለመጀመርያ ግዜ ስለመቻቻል ዲስኩር ያልተሰማበት የኢድ መልክት (ራድዮ ነጋሺ)

ይህ ከታች የሚነበበው የኢድ መልዕክት ከኢትዮጵያ ጠ/ሚንስትር  የተላለፈ መሆኑ አዲስ የሚያደርገው ሆኖ ለየት የሚያደርገው ደግሞ ጉዳዩን ከሚያውቅ ሰው የቀረበ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ለወትሮው ሁሌ የሙስሊሙ በዓል ብቻ አየተጠበቀ ስለመቻቻል ይደሰኮር የነበረዉን አሰልቺ ዲስኩር ሙልጭ አድርጎ ያጠበ መልክት መሆኑ ነው::  መሆንም ያለበት አንዲሁ ነው! ኢትዮጵያ ዉስጥ መቻቻል አንዲኖር ችሎ ያሳየ ቢኖር ህዝበ ሙስሊሙ ለመሆኑ ነባራዊ እዉነታዎች ምስክር ናቸው ::  ሀገራችን ዉስጥ ሁሌም ስለመቻቻል ሲወሳ የሚጠቀሱት ቦታዎች  ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ  ሙስሊሙ በብዛት የሚኖርባቸው ክልሎች መሆናቸዉን ልብ ይልዋል:: ስለዚህ ሙስሊሙ ስለመቻቻል የሚያስተምር አንጂ የሚነገረው አይደለም, ለዚህም ነበር የሙስሊሙ በዓላት አየተጠበቀ ሆን ተብሎ ስለመቻቻል የሚደረገው ዲስኩር አሰልቺ የነበረው:: በእዉነቱ ስለመቻቻል ሊሰበክ የሚገባው በየቤተክርስታያናንቱ ነው, የመቻቻልን ሀሁ ማስተማር የሚያስፈልገው ለአክሱም ,ለላልበላና በአካባቢው ላሉ ዜጎች ነው ::  ሙስሊሙ ማህበረሰብ የመቻቻልን ምእራፍ ካለፈው ዘመናት ያለፈ በመሆኑ ዛሬ ዶክተር አብይ የሚመጥን መልእክት በማስተላለፍ ነጥብ አስቆጥረዋል::
የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶክተር አቢይ አህመድ ለኢድ አልፈጥር በአል ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት
 EBC
ቅዱሱን የረመዳን ወር በተለመደው የመረዳዳት፣ የመጠያየቅ፣ የመደጋገፍ እና የመከባበር ስሜት አገባዳችሁ እንኳን ለታላቁ የኢድ- አልፈጥር በአል በሰላም አደረሳችሁ- አደረሰን፡፡ ኢድ ሙባረክ፡፡
ኢትየጵያውያን ሙስሊሞች 1.9 ቢሊዮን ከሚደርሱ የአለማችን ሙስሊም ወገኖቻችን ጋር በድምቀት የሚያከብሩት ይህ በአል በሀገራችን ኢትዮጵያ ሲከበር የሙስሊሙ ብቻ ሳይሆን የመላ ኢትዮጵያውያን ወደመሆን የፍቅር ሰገነት ከፍ ይላል፡፡
በኢትዮጵያችን በሙስሊሙ በአል ክርስቲያኑ፤ በክርስቲያኑ በአል ዋቄፈታው፤ በኢድ- በፋሲካው- በገና በእሬቻው የእንኳን አደረሰህ፣ እንኳን አደረሰሽ ቅብብሉ መልካም ምኞት እስከታከለበት ዝይይር በሚዘልቅ የፍቅር ሸማ ተከብክቦ ይሄው ዛሬ ደርሷል፡፡
ቅዱሱ የረመዳን ወር፣ የጾም፣ የጸሎት እና ከፈጣሪ ጋር የመገናኛ ልዩ ወር እንደመሆኑ መጠን፣ ኢድ አልፈጥርም፣ የፍቅር እና የበረከት፤ የይቅርታ እና የአብሮነት ድንቅ በአል ነው፡፡
ኢድ ሙባረክ! የኢድ አልፈጥር በአል የሚውለው፣ በሸዋል ወር የመጀመሪያው ቀን ነው፡፡
የሸዋል ወር ደግሞ፣ የታወቀ የበጎ ስራ እና የልገሳ ወር ነው፡፡ በፍቅሩና መተሳሰቡ ላይ በጎ ስራው ሲታከል፣ ጊዜው ይበልጥ የተባረከ ይሆናል፡፡
ለሙስሊም የሀገሬ ልጆችም ሆነ ለመላ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ የምመኘውም ሙሉ ዘመናችን የሸዋል ወር እንዲሆንልን ነው፡፡
የአብሮነት እድሜያችን ሁሉ በሸዋል ወር በሚከቡን በረከቶች የተሞላ ከሆነ የዚህችን ሀገር ከፍታ የምናረጋግጥበት እና ወደ ታላቅነታችንም የምንመለስበት ጊዜ ፈታኝ ቢሆንም ቅርብ ነው፡፡
በተግባርም ወሩ ምድራችንን በሰማይ ጠል አረስርሶሰማያችንን በዳመና ጃኖ አልብሶ በሰላም ተሸኝቷል፡፡ መላው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም የረመዳን ወርን በሰላም አጠናቆ “ኢድ ሙባረክ…!” ከተባባለና የጾሙን ወቅት ከሸኘ በኋላ አፉን በማለዳ ምግብ አሟሽቶ አፍታም ሳይቆይ የከርሞውን ረመዳን መናፈቅ ይጀምራል፡፡
“የዘንድሮው አልቆብናል- ለመጪው ሰላም ያድርሰን…” እየተባባለ የሩቅ ተስፋን ይቀንናል፡፡
እንዲህ የሚያጓጉን፣ የምንሳሳላቸው፣ የምናከብራቸው፣ የምንወዳቸው እና መስከረም ጠብቶ አዲስ ወር በባተ ቁጥር “ሊመጡልን ነው…” በሚል ጉጉት በስስት የምንናፍቃቸው መንፈሳዊ እሴቶቻችን ሁሌም የደስታችን ምንጭ የሚሆኑት እና በአብሮነታችን ውስጥ እያደር የሚፈኩትበፍቅር የሚደምቁት ይህች ሀገር ሰላም ስትሆን ብቻ ነው፡፡
በመሆኑም መላ የሀገራችን ሙስሊሞች እና ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንደሁልጊዜው ሁሉ በረመዳን ወር የነበሩንን የሰላም፣ የመረዳዳት፣ የመከባበር እና የመጠያየቅ ባህል በማስቀጠል የሀገራችንን ሁለንተናዊ ለውጥ እና ህዳሴ ለማረጋገጥ የበኩላችሁን እንድትወጡ በዚህ አጋጣሚ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡ በመጨረሻም በአሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታ እና የአንድነት በአል እንዲሆንላችሁ ከልብ እመኛለሁ፡፡
ኢድ ሙባረክ!!
Filed in: Amharic