>

ግልጽ ደብዳቤ ለክብር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አቢይ አህመድ (ከቀድሞ የኢትዮጵያ ሠራዊት አባል የተላከ) 

ክቡር ጠ/ሚ የሀገር ባለውለታ የሆነውን የቀድሞውን ሰራዊት ከወደቀበት ያንሱ ክብሩን  ይመልሱ?!? 

ግልጽ ደብዳቤ

ለክብር ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አቢይ አህመድ

ለክብር ፕሬዘዳንት ለማ መገርሣ ቲም (ቡድን)

በቅድሚያ እናንተን ወደዚህ የሥላጣን እርካብ ላመጣችሁ ለቸሩ እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይገባል፡፡ አሜን!
ከሃያ ሰባት አመት በኃላ ኢትዮጲያ ኢትዮጲዊነትን ጽንሰሀሳብ መሰረት በማድረግ ህዝባችን ስለአንድነት ስለትብብር ማሰብ እንዲችል ማስቻል ምንያህል ርቀት እንደተጓዛችሁ፣ ምንያህል ከባድና እልህ አስጨራሽ ፈታኝ ትግል ውስጥ እንዳሳለፋችሁ መረዳት ይቻላል፡፡ ለዚህም ነው ቋንቋን መሰረት ባደረገ ዘር በሐይማኖት መከፋፈላችን የሚያስደስታቸው ኢትዮጲያዊነት እትዮጲያ ብሎ ማሰብ የድርግ ተሸናፊ አስተሳሰብና ሀሳብ ነው ሲሉ የሚደመጡት፡፡ የሚገርመው ህዝባችን መከፋፈልና በጥርጣሬ ከመተያየት ወጥቶ አንድ አስተሳሰብ መታየት መጀመሩ ምንኛ እንደሚያኮራን በቃላት መግለጽ ይከብዳል፡፡ እውነትም ኢትዮጲያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤ ልመናዋን ጸሎቷን ሰምቶ ምላሽ በመሆናችሁ የሚያረጋግጥ በመሆኑ ለፈጣሪያችን ዳግመኛ ክብር ምስጋና ይገባል እላለሁ፡፡
ዛሬ በእናንተ ቆራጥ አመራርና መሰዋእትነት የእርስ በርስ የጭፍጨፋ ጥንስሱ ከንቱ መሆኑ ወዳጆቻችንን የሚያስደስት፣ ጠላቶቻችንን የሚስቆጭ ቢሆንም በህዝባችን ልብ ውስጥ ሀውልት የተከላችሁ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ የኢትዮጲያ ህዝብ ከጎናችሁ በመሆኑ ለኢትዮጲያ አንድነት ሕይወታችንን ለመስጠት የተሰለፍን፣ የደማን፣ የቆሰልን፣ ደማቸውንና አጥንታቸውን የከሰከሱ ሰማእታት ዓላማ ህያው መሆኑን አስረግጣችሁልናልና…፡፡ ዳግመኛ የትላንቷ ርዋንዳ፣ ዳግመኛ ሱማሌ፣ ዳግመኛ ሊቢያ ምንግዜም ምንግዜም ኢትዮጲያ አትሆንም ልትሆንም አትችልም፡፡ ቆራጥ ሂሊና ባላቸው የኢትዮጲያ ልጆች የጠላትን እኛ ከሞትን ስርዶ አይብቀል ምኞታቸው ምኞት ብቻ ሆኖ እንዲቀር አድርጋችኃል፡፡ ልንኮራባችሁ ይገባናል፡፡
ኢትዮጲያ እግዚአብሔርን ተደግፋ የምትኖር አገር ነች፤ ድንገት በባንዳ ልጆች መዳፍ ውስጥ ወድቃ ለሃያ ሰባት አመታት ተንገላታለች፣ ተደፍራለች፣ ታርዛለች ልጆቿም ተገለዋል፣ ታስረዋል፣ ተሰደዋል፡፡ ይኸው ዛሬ በቁርጥ ልጆች መስዋእትነት የኢትዮጲያዊነት ጎዳናን መጓዝ ጀምራለች በዚሁ እንደምትቀጥል አልጠራጠርም፡፡ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል በቋንቋ ላይ የተመሰረተው ዘረኝነት፣ ጎሰኝነት ያውም ኃላቀሩ የዘረኝነት ፖለቲካ እያበቃለት እንደሚገኝ ብዙ ማሳዎች እየታዩ ነው፤ ምንም እንኳን ብዙ ብዙ መሰራት ቢኖርበትም፡፡ ይህች ናት እምዬ ኢትዮጲያ !!!
ወደ ተነሳሁበት የደብዳቤዬ ሀሳብ ልመለስ፡፡ በቅድሚያ እራሴን ለማስተዋወቅ እወዳለሁ፤ እኔ የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት አባል ከሆለታ ገነት የመኮንኖች ማሰልጠኛ የ41ኛ ኮርስ ምሩቅ ነኝ፡፡ በዓለም ዘንድ ክብር ሲሰጠው በነበረው የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት ወታደራዊ ስልጠናና አደረጃጀት ውስጥ ያለፍኩና የሻምበልነት ማእረግ ከነክብሩ ያለኝ ሲሆን ከተገዳላይ ከወያኔ ሰራዊት ጋር በግዴታ ያለውዴታ ለድፍን 5 አመት እስከ 1988ዓ/ም አብሬ ሰርቻለሁ፡፡ ይህ ማለት ወዳጆቼን ወያኔን ከግንቦት 19 ቀን 1983ዓ/ም ምሽት ጀምሮ በቅርበት እድንተዋወቅ ረድቶኛል ማለት ነው፡፡
ይህ በእነዲህ እንዳለ የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት ሁለ ነገሩ ያሳስበኛል፤ ይቆጨኛል፤ ያንገበግበኛል፡፡ ለምን ቢባል በወታደር እጅ ተወልጄ፣ አድጌ፤ተምሬ ወታደር ሆኜ በመፈጠሬ ነው፡፡ የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት ለኢትዮጲያ አንድነት፣ ለሰላም፣ ለባንዲራችን፣ ለዳርድንበራችን፣ ለነፃነታችን ደሙን ያፈሰሰ አጥንቱን የከሰከሰ ለኢትዮጲያ ሕይወታችንን ወደን ፈቅደን ለሀገር ክብር ለሕዝባችን መስዋእት ለመሆን ቃል የገባንና ዝግጁ የሆን የማህበረሰቡ አካል ነን፡፡
ስለዚህ ተሳስቼ እንደሆነ አላውቅም እንጂ በእርሶ በጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ለማ ቲም አንድም ቀን ስለ የቀድሞ ሰራዊትን በተመለከተ የተነገረ፣ የተባለና የተወሳ በግሌ ከአንደበታችሁ ሲነገር፣ ሲባል ባለመስማቴ በቁጭት የተሰማኝን ሁሉ ለማውጣት፣ አቤት ለማለትና ለመጠየቅ ተገድጃለሁ፡፡ ምክንያቱም እኛ የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ከአብራካችን የወጡ ልጆቻችን፣ የትዳር አጋሮቻችን እኛን ያፈሩ ወላጆቻችንን ጨምሮ ለኢትዮጲያ አንድነት ስለተዋደቅን ማንነታችን ተገፎ ተሳዳጅ ሆነን አንገታችንን ደፍተን እንድንኖር ተደርገን በመቆየታችን ነው፡፡
እኛና ልጆቻችን፣ ባለቤቶቻችን ጨምሮ በእውቀታችን፣ በትምህርታችን፣ በልምዳችን መጠን ሰርተን በሀገራችን እንዳንኖር በተለያየ ተቋም በተሰገሰጉ አባሎቻቸው ክትትል ከአመት አመት ተሳዳጅ ተፈናቃይ ሆነን ኑሮአችንን እየገፋን እንገኛለን፡፡ ሳይወዱ ከእኛ አብራክ የተገኙ ልጆች የእጣው ተቋዳሽ ለምን እንደሆኑ ባይገባንም የገፈቱ ቀማሾች ሆነው ይገኛሉ፡፡
በመሰረቱ እኛ ለወያኔ ባለውለታ ነን ከውስጥ ልብሳችን እስከ ኑሮአችን አውርሰናቸዋል፡፡ ያሰብነውን ያህል መልክ ባይኖረውም የወያኔ የሰራዊት ተቋማት ትንሽ መልክ እንዲኖረው እያንዳዳችን የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት አባላት የበኩላችንን አስተዋፅኦ አድርገናል፡፡
ሰራዊቱን በዘመናዊ ሰራዊት መልክ ያደራጀው ማነው? እግረኛውን በማደራጀት፤ መካናይዝዱን በማደራጀት፣ የውጊያ መሃንዲስን በማደራጀት፣ ሲግናሉን መገናኛውን በማደራጀት፣ ሆስፒታሎችን በማደራጀት፣ ሎጀስቲኩን በማደራጀት፣ ወታደራዊ ማሰልጠኛን በማደራጀት ወዘተ አንድም የወያኔ አደረጃጀት ውስጥ ያለ የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ውጪ ሊታሰብ አይቻልም፡፡ ኢትዮ ኤርትራን ውጊያ በየፈርጁ የመራው ማነው? የወያኔ ሠራዊት በዘመናዊ መልኩ ሲስተሙን የዘረጋውና ያደራጀው የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት አባላት መሆኑን እነሱም ያውቁታል በታሪክ በደጋፊዎቻቸው እየተዘገበም ይገኛል፡፡
ይህንን እገዛ አድርጎ ሳለ የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት አባላትና ቤተሰቡን ጨምሮ ከአመት አመት የማያባራ ተሳዳጅና የተፈናቃይን ኑሮ እንዲገፋ ተደንግጎበታል፡፡ ይህ ሰራዊት አባል ነው በየበረሀው ታርዞና ተርቦ ሀገሩን ዳር ድንበሩን ሲጠብቅ ኢትዮጲያ! ስለአለ ብቻ ኑሮው በላቲክ ተጠልሎ ከነቤተሰቡ እንዲኖር የተፈረደበት፡፡ ሂሊና ላለው ያማል፡፡
ሁሉም የቀድሞ ሰራዊት አባላት በሰራዊት ውስጥ በየፈርጁ በተሰማራበት ሁሉ እግረኛው፣ መካናይዝዱ፣ ሀኪሙ፣ መሀንዲሱ ወዘተ ለኢትዮጲያ ኢትዮጲያዊነት የተዋደቀ በመሆኑ ነጻነቱ መብቱ እንዲጠበቅ ከተሳዳጅ እና ከመፈናቀል ተጠብቆ በአክብሮት መያዝ አለበት ስል እንደ አንድ ኢትዮጲያዊ ዜጋ ልጠይቅ እገደዳለሁ፡፡
‘ክብር ለሚገው ክብር ይሰጠው!!! እላለሁ’
ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጲያ ኢትዮጲያ ሆና ሕዝቦቿ በክብር በነጻነት እንድንኖር ሀገራዊ የሰራዊቱና የደህንነቱ አደረጃጀት በአዲስ አደረጃጀት Reformation ሊኖር ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ እጅግ አስፈላጊም ነው፡፡ የሰራዊቱ አደረጃጀት እንደቀደሙ ጠዋት ተመርቶ ከሰዓት መርካቶ የሆነ አደረጃጀት ሳይሆን በወታደራዊ ሀ ሁ የሰለጠነና የበለጸገ፣ በእውቀት፣ በትምህርት የዳበረ ከምንም በላይ በወታደራዊ ዲሲፕሊን የታነጸና የበቃ ሰራዊት ነው ሀገራችን ኢትዮጲያ የሚያስፈልጋት፡፡ ጭካኔ ወታደራዊ እውቀት አይደለም፡፡ ጥዪት ተኩሶ ወገን መግደል ወታደራዊ እውቀት አይደለም፡፡ ወታደራዊ እውቀት ከእርምጃ ከአረማመድ ጀምሮ የአካል፣ የፀጉር፣ የአልባሳት ጽዳትን ጨምሮ የበታች ለበላዩ ታዛዥ የበላይ የበታቹን አክባሪ ለሀገሩ ድንበር ለሕዝቡ ለባንዲራው ሲል ሕይወቱን አሳልፎ ሊሰጥ ዥግጁ የሆነ ርህሩህ ጀግና ማለት ነው ወታደራዊ እውቀት፡፡
ይህ በስልጠና የሚመጣ እንጂ በወኔ እንዳው ከሜዳ የሚገኝ አይደለም፡፡ በስልጠና ለመሆኑ አንድ ምሳሌ ላስቀምጥ፤ የቀድሞ ሰራዊት ምሽግ ውስጥ ውሎ አድሮ ነበር ከወያኔና ከሻቢያ ጋር ለኢትዮጲያ አንድነት ሲል ሲዋጋ የነበረው ሆቴል ተቀምጦ እንዳልሆነ መቼም እውን ነው ግን አንድም ተባይ በሰውነቱ ወይም በጸጉሩ ላይ አይገኝበትም ነበር፡፡ ሌላ መሳሪያ ከነጥይቱ ከፊቱ ደርድሮ ወደ አገሩ መመለሻ ሳንቲም ወገኑን ሲለምን የነበረው በአግባቡ የሰለጠነ በመሆኑ የውንብድና የዘራፊ አእምሮና ፍላጎቱ ስላልነበረው ነው፡፡ ይህንን ባህሪውን ኬት ተካነው/ አገኘው ቢባል ከወታደራዊ ስልጠና ነው፡፡ ይህ ባይሆን ኖሮ የፈለገውን ዘርፎ የፈለገውን አስገድዶ የፈለገውን ይዞ በሔደ ነበር፡፡
ስለዚህ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ቀደም ሲል የወታደራዊ እውቀታችን እንዳለ ሆኖ በአካዳሚክ ትምህርት የመጀመርያ ድግሪ፣ የሁለተኛ ድግሪና ከዚያ በላይ ይዘን የምንገኝ በሺዎች የምንቆጠር በብቃት ከመንግስት ዩኒቨርስቲዎች ተምረን እንጂ ገዝተን ወይም አሰርተን ያልሆን የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት አባላት ስላለን በሰራዊቱ አደረጃጀት ውስጥ ልንካተትና አገራችንን ልንገነባ ይገባናል፡፡ የትኛውም የሰራዊቱ ተቋም የጢቂቶች እዳጋ/ገበያ ሊሆን አይገባም፡፡
ከዚያ በመቀጠልም በዚህ ውስጥ መካተት ያልቻሉ የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት አባላት እንደየፈርጁ እና እንደ አግባብነቱ ልጆቻችን፣ ባለቤቶቻችንና ወላጆቻችን የሕክምና የጡረታ ኢንሹራንስ መብትን አስመልክቶ የዜግነት መብታችን ሊጠበቅልን ይገባል እላለሁኝ፡፡
በማጠቃላዬ ክብር ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ለማን ቲም እና ለውጥ ፈላጊና አራማጅ መሪዎቻችንን በአጽንኦት የምጠይቀውና የማመለክተው እንደማንኛውም የኢትዮጲያ ማህበረሰብ እንደወጣቱ፣ እንደነጋዴው ወዘተ የኢትዮጲያ የቀድሞ ሰራዊት አባላት መድረክ ተዘጋጅቶልን በአገራችን፣ በነጻነታችን፣ በመብታችን ወዘተ ጉዳይ መወያየት ባንችል እንኳን ትኩረት ቤተሰቦቻችንን ጨምሮ ሊሰጠን ይገባል ስል በአክብሮት አመለክታለሁኝ፡፡
ኢትዮጲያ ተከብራ በነጻነት ለዘላለም ትኑር !
ኢትዮጲያ ትቅደም፡፡
Filed in: Amharic