በቀጣዩ ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ ሰላማዊ ስልፍ የምናደርግበት የመጀመሪያ ምክንያት ዴሞክራሲያዊ መብታችን ስለሆነ ነው። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 30 መሰረት ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን በሰላም የመሰብሰብ፥ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው። በተለይ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ይህ መብት ሙሉ በሙሉ ተገድቧል። መስቀል አደባባይ ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ የወጡ ዜጎች ፍፁም ጭካኔ በተሞላው መልኩ ተደብድበዋል፣ ታስረዋል፣ ተንገላተዋል። በመሆኑም ቅዳሜ ዕለት በተመሳሳይ ቦታ ሰላማዊ ሰልፍ የምናደርገው እንዲህ ያለ በደልና ጭቆና መቅረቱንና ዴሞክራሲያዊ መብታችን መከበሩን በተግባር ለማረጋገጥ ነው።
2ኛ፡- ሃሳብና አመለካከታችንን ለመግለፅ ነው!
በመሰረቱ ዜጎች ሰላማዊ ሰልፍ የሚያደርጉት ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት ለመግለፅ ነው። በዚህ መሰረት በቀጣዩ ቅዳሜ በመስቀል አደባባይ በምናደርገው ሰለማዊ ሰልፍ ሃሳብና አመለካከታችንን በነፃነት እንገልፃለን። ባለፉት አመታት በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሀገራችን ዜጎች ሃሳብና አመለካከታቸውን በነፃነት በመግለፃቸው ብቻ ለሞት፥ እስራት፥ ስደት፥ እንግልት፥ የአካልና ስነ-ልቦና ጉዳት፥… ወዘተ ተዳርገዋል። በመሆኑም ቅዳሜ ዕለት በምናደርገው ሰላማዊ ሰልፍ ለሃሳብና አመለካከት ነፃነት የታገሉ የመብት ተሟጋቾችን እናወሳለን፥ እናወድሳለን፣ የራሳችንን ሃሳብና አመለካከት በነፃነት በመግለፅ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን በተግባር እናረጋግጣለን።
3ኛ፡- ይቅርታና ምህረትን ለማበረታታት ነው!
የዜጎች መብት፥ ነፃነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በተለያየ መንገድ የታገሉ ፖለቲከኞች፤ የመብት ተሟጋቾች፥ ጋዜጠኞች፥ ፀሃፊዎች፥ ምሁራን፥… ወዘተ ከእስር ተፈትተዋል፣ ከስደት ከሚኖሩበት ሀገር መመለስ ጀምረዋል። በተለያዩ ሀገራት እስር ቤቶች በስደት ላይ የነበሩ ኢትዮጲያዊያን ተፈትተው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ተደርገዋል። በዚህ መሰረት፣ በሀገር ውስጥ ላሉ የፖለቲካ እስረኞች ይቅርታ በማድረግ፣ በውጪ ለሚገኙት ደግሞ ምህረትን በመለመን የተሰራው ሥራ በጣም አበረታችና ሊደነቅ የሚገባ ነው። በመሆኑም በቅዳሜው ሰላማዊ ሰልፍ ይቅርታና ምህረትን ከማስፈን አንፃር የተሰራውን ስራ እናደንቃለን፣ ወደፊትም ቀጣይነት እንዲኖረው እናበረታታለን። በተቃራኒው ቂምና በቀልን እናወግዛለን። ¸
4ኛ፡- ለውጥና መሻሻልን ለመደገፍ ነው!
ከላይ ከ1-3 በተገለፀው መሰረት የዜጎችን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነፃነቶች ከማረጋገጥ፣ እንዲሁም ይቅርታና ምህረትን ከማስፈን ካለፉት አመታት በተለየ አንፃራዊ ለውጥና መሻሻል መኖሩን በተጨባጭ ማረጋገጥ ይቻላል። በመሆኑም ከዴሞክራሲ ስርዓት እና ብሔራዊ መግባባት ከማስፈን አንፃር የተጀመረውን ለውጥና መሻሻል እናበረታታለን። በዚህ መልኩ የተጀመረው እንቅስቃሴ ቀጣይነት እንዲኖረውና በዜጎች ሕይወት ላይ ተጨባጭ ለውጥና መሻሻል እንዲያመጣ ድጋፍና ትብብር እናደርጋለን።
5ኛ፡- ፀረ-ለውጥ እንቅስቃሴዎችን ለመቃወም ነው!
ከላይ በተጠቀሰው መልኩ በሀገራችን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ላይ ለውጥና መሻሻል የማምጣት የሚደረገውን ጥረት የሚያደናቅፍ ማንኛውም ዓይነት እንቅስቃሴን በጥብቅ እንቃወማለን። በተለይ ላለፉት ሁለት አስርት አመታት በሀገሪቱ ላይ ተንሰራፍቶ የነበረውን አፈና እና ጭቆና ዳግም ለመመለስ የሚንቀሳቀሱትን ወገኖች እናወግዛለን። የሀገራችንን ሕዝብ በቋንቋና ብሔር በመከፋፈል ሁከትና ብጥብጥ ለማስነሳት የሚደረገውን አፍራሽ እንቅስቃሴ እንቃወማለን። በተቃራኒው ስለ ወደፊት አብሮነትና አንድነት እንዘምራለን።