>

"ምን ታመጣላችሁ?" ለሚለው ፉከራችሁ መልሳችን ፍቅርና ፍቅር ብቻ ነው፤ ፍቅር እናመጣለን! (ደረጄ ደስታ)

“ምን ታመጣላችሁ?” ለሚለው ፉከራችሁ መልሳችን ፍቅርና ፍቅር ብቻ ነው፤ ፍቅር እናመጣለን!

ደረጄ ደስታ
“ሎሚና ትርንጎ ሞልቶ በአገልግልህ 
እምቧይ ታሸታለህ የደሀ ነገርህ” ይባላል
አገሬዎቻችሁ ሲተርቱ – ነገር የፈለገ ለአምባሻም ወጥ ይጠይቃል – ይላሉ። ሀገርና አህጉራዊ ፍቅርና ሰላምን በምንዘምርበት በዚህ ጊዜ ላንዳንዶቻችን ኤርትራም ሆነ ትግራይ ሆነን በኩርማን መሬት የተነሳ ጥላቻ መወነጫጨፍ አይጠቅመንም። የትግራይ ወንድሞቻችን የባላንጣነት ሰልፉን ትተው ከኤርትራ ወንድሞቻቸው ጋር ያለው ግንኙነት በልጦ ኤርትራውያንም ትግራይን ተራምደው ወደ ኢትዮጵያ  የመዝለቁን አጉል እልህ አስቀርተው ሁለቱም  አስመራ መቀሌና አዲስ አበባ ላይ መንቀባረር ሲችሉ እልህ ተጋብተው ሁላችንንም ወደ ችግር ባይከቱን እንለምናለን። “እናስጠነቅቃለን” አላልንም “እንማጸናለን” ነው ያልነው። በቃ የተሸነፈ ሰው አይገባችሁም? ፍቅር አሸንፎናል። በፍርሃትም ከተረጎማችሁት ይሁን በቃ በወንድሞቻችን መሞትም ሆነ ወንድሞቻችንን መግደል እማንፈልግ ፈሪዎች ነን ብንል ምን ታመጣላችሁ? ተስፋ ግን አንቆርጥም፣ የሰላም መስመሩ ገብቶናል። ከኛ ወገን የድንቁርና ጀብደኝነትና ጀግንነትን ለይተው እሚያውቁት ልጆቻችንን አሸንፈው እንደወጡ ሁሉ፣ ከናንተም እንዲሁ አስተዋዮች ፈክተው በዝተውና አሸንፈው እስኪወጡ በትዕግስት እንጠባበቃለን! እንግዲህ ከኛም ወገን እንደናንተው እሚፎክሩ ጥቂት እብዶች ቢኖሩብንም፣ ብዙሃን የሆነው እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ይህን ብለናል፣ ለዚህ ሀሳብም ለመሰለፍ ተዘጋጅተናል። እንግዲህ እናንተስ ታዲያ ምን ታደርጉን – ትጨርሱን? “ምን ታመጣላችሁ?” ለሚለው ፉከራችሁ መልሳችን ፍቅርና ፍቅር ብቻ ነው። ፍቅር እናመጣለን!
Filed in: Amharic