>

የአብይ መንግስት አፋጣኝና ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጥባቸው የሚገባ ጥያቄዎች!!! (ፋሲል የኔአለም)

የአብይ መንግስት አፋጣኝና ግልጽ ማብራሪያ ሊሰጥባቸው የሚገባ ጥያቄዎች!!!
ፋሲል የኔአለም
አገራችን ነዳጅ ማውጣት መጀመሯ ጥሩ ዜና ነው። ነገር ግን ለህዝብ ግልጽ ያልሆኑ ብዙ ጥያቄዎች ያሉ በመሆኑ የአብይ መንግስት አፋጣኝ ማብራሪያ እንዲሰጥባቸው አንዳንዶችን ማቅረብ እፈልጋለሁ።
1- ከቻይና ጋር የተደረገው የኮንትራንት ስምምነት አብይ ከመምጣቱ በፊት እንደተከናወነ ይታወቃል። በስምምነቱ መሰረት የቻይና ድርሻ ስንት ነው? የኢትዮጵያስ? ቻይና ከሌሎች አገሮች ተለይታ ኮንትራቱን እንዴት አሸነፈች? ጨረታ ተካሂዶ ነበር ወይ? ከተካሄደስ ግልጽ ነበር ወይ?  ኮንትራቱ የሚቆየውስን ለምን ያክል አመታት ነው? ማብራሪያ የስፈልጋል።
2- ምንጊዜውም ከነዳጅ ጋር የሚመጡ የደህንነት እና የፖለቲካ ስጋቶች አሉ፣ በዚህ ዙሩያ የተደረገ ጥናት አለ ወይ?
3- የአካባቢው ህዝብ ተወያይቶበት  ፈቃዱን ገልጿል ወይ? ድርሻስ አለው ወይ? በሁዋላ እንደሚድሮክ ወርቅ እንዳይሆን።
4    የነዳጅ  ፍለጋው ሲካሄድ የአካባቢው ህዝብ ተቃውሞውን በማሰማቱ ብዙ ጉዳቶች ደርሰዋል። ለጥያቄያቸው መልስ ተሰጥቷል ወይ? ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች፣ ለወደፊቱ ካሳ ያገኛሉ ወይ?
5 የአካባቢ ጥናት ተካሂዷል ወይ? ጥናቱ ለህዝብ ይፋ ሆኗል ወይ?
6  አብዲ አሌን የመሰሉ  ነፍሰ ገዳዮች ከነዳጅ የሚገኘውን ገንዘብ በስልጣን ለመቆየት አይጠቀሙበትም ወይ? እንዴት ነው ለመከላከል የታሰበው?
7 ነዳጅ ዋነኛ የሙስና ምንጭ ነው። እንዴት ነው መንግስት ከነዳጅ ጋር በተያያዘ የሚፈጠረውን ሙስና ለመከላከል ያቀደው?
8 ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በእያንዳንዱ ሂደት ውስጥ ይሳተፋሉ ነው?
9 ከነዳጅ የሚገኘው ገንዘብ በአገሪቱ ባጀት ላይ የሚኖረው ድርሻ ምን ያክል ነው?
በእነዚህና በሌሎችም ጥያቄዎች ዙሪያ መንግስት በአፋጣኝ ማብራሪያ ቢሰጥ ወይም ከባለሙያዎች ጋር ውይይት ቢያደርግ ነገ ለሚፈጠሩት ችግሮች ዛሬ የመፍትሄ ሃሳቦችን አዘጋጅቶ ማስቀመጥ ይቻላል። የአብይ መንግስት ግልጽነትን እንደሚያሰፍን ቃል በገባው መሰረት በነዳጁ ዙሪያም ግልጽ መረጃዎችን በፍጥነት እንዲሰጠ እጠይቃለሁ።
Filed in: Amharic