>
5:16 pm - Tuesday May 24, 8478

የሽግግር ጊዜ እና የሽግግር መንግስት (ግርማ ሰይፉ ማሩ)

የሽግግር ጊዜ እና የሽግግር መንግስት

ግርማ ሰይፉ ማሩ

ኢህአዴግ በህወሓት ቅርቃር ውስጥ ሆኖ ለውጥ እንዲያመጣ ሲጠየቅ፤ ሲቀርቡ ከነበሩት ጉዳዩች አንዱ የሸግግር መንግስት ምሥረታ ነው፡፡ የሸግግር መንግሰት የሚያስፈልገው በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ተግባሩን ማከናወን ሳይችል ሲቀር እና በቀጣይም ዜጎች ወደሚፈልጉት መስመር ለመውሰድ አቅም ሲያጥረው የሚደረግ አማራጭ ነው፡፡ በአብዛኛው በሥልጣን ላይ ያለው መንግሰት በሀይል (በሕዝብ አመፅ ወይም በጠመንጃ) ተወግዶ ቀጣይ በሕዝብ የሚመረጥ መንግሥት ሥልጣን እስኪይዝ ድረስ የሚኖር የሽግግር ጊዜ መንግሥት ነው፡፡ በአግባቡ ያልተጠቀምንበት አግላይ የነበረውን የ1983 የሸግግር መንግሥት እንደ አንድ ማሳያ መውሰድ ይቻላል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ የሸግግር መንግሰት እንዲኖር የሚያሰገድድ ሁኔታ ባይኖርም የሸግግር መንግሥት የሚሉ ቡድኖች እና ግለሰቦች መኖራቸው እውነት ነው፡፡ በእኔ አረዳድ ቡድኖቹ አሁን ይኑር በሚሉት የሸግግር መንግስት ሸራፊ ሥልጣን ከማግኘት የዘለለ የተሻለ ነገር እንደማያስቡ ይገባኛል፡፡ በግለሰብ ደረጃ ይህን የሚያቀርቡት ደግሞ ጉዳዩን በቅጡ ካለመረዳት ነው በሚል ለመውሰድ እፈልጋለሁ፡፡ ለምሣሌ የዛሬ የባህርዳር ሰልፍ ላይ ወ/ሮ እማዋይሽ ያደረጉት የሸግግር መንግስት ጥሪ ከዚህ የሚለይ አይመስለኝም፡፡

እውነት ነው ይህን ወቅት የሽግግር ጊዜ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የሽግግር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒሰትሩም ዶክተር አብይ እንዲሆኑ ሕዝብ ድጋፍ የሰጠ ይመስለኛል፡፡ እኔም አሁን ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድም የሸግግር ጊዜ ጠቅላይ ሚኒሰትር አድርጌ ለመውሰድ እፈልጋሉ፡፡ በዚህ የሽግግር ወቅት ማንኛውም የሸግግር መንግስት ሊያደርገው የሚችለውን ነገር እሰከ አደረጉ ድረስ ሌላ የሽግግር መንግስት የማቋቋም አባዜ ውስጥ መግባት ፍላጎት የለኝም፡፡ በአሁን ወቅት የሸግግር መንግስት ይቋቋም ቢባል ከዘጠና በላይ ፓርቲ ተብዬ የተመዘገቡ በአገር ውስጥ ተመሳሳይ ቁጥር በውጭ አገር ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦች እና አገር ወዳድ ነን የሚሉ ሁሉ ለሥልጣን ፍርፋሪ የሚዋደቁበት መድረክ ከመፍጠር የዘለለ አንድም ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ይልቁንም አንድ ትልቅ አገራዊ የእርቅና የመግባባት ጉባዔ በማካሄድ አሁን ዶክተር አብይ የጀመሩትን ለውጥ የሚያግዝ ነፃ ኮሚሽን በማቋቋም የሽግግር ጊዜውን ማገዝ ያስፈልጋል፡፡ የሽግግር ጊዜውን በእርቅ፣ በይቅርታና በፍቅር የሚጀምር አገራዊ ጉባኤ ያስፈልገናል፡፡ ጉባኤው አንድ ኮሚሽን ማቋቋም ይኖርበታል ብዬም አምናለሁ፡፡

ይህ የሚቋቋመው ኮሚሽን በቀጣይ ስልጣን ለመያዝ መንግሰት ለመሆን የሚሹ ፓርቲዎች ለህዝብ ውሣኔ የሚቀርቡበት ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ታማኝና ገለልተኛ የሆነ ምርጫ ቦርድ ምስረታን ከመንግስትና ተቃዋሚዎች ጋር በመተባበር የሚያከናውን፡፡ አሁን አለን የሚሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀመጠውን መስፈርት አሟልተው እንዲቀርቡና ድጋሚ ምዝገባ እንዲያካሂዱ ማድረግ፡፡ የሲቪል ማህበራት የተከለከሉትን በመብት ዙሪያ መስራት ስራ እንዲሰሩና በተለይ ደግሞ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የተዘራውን የጥላቻ ዘር እንዲያመክኑ ዜጎች በሃሳብ ዙሪያ እንዲሰባሰቡ የሚያስተምሩበት እንዲሆኑ ማድረግ፡፡ ሚዲያዎች በነፃነት እንዲሰሩ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ማድረግ፡፡ የደህነነትና ፖሊስ መከላከያ ወዘተ በሥልጠና እና በመዋቅር ማሻሸያ በማድረግ ይልቁንም አዲስ አባላትን በማስገባት የአገር ተቋማት እንዲሆኑ ማድረግ፡፡ የመሳሰሉትን የሚያግዙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ሌሎች ዝርዝር ተግባራት በጉባኤው ሊሰጣቸው ይችላል፡፡ በተለይ መንግሰት ለብቻው ቢያደርገው አይታመንም የሚባሉ ጉዳዮችን በተመለከተ፡፡

በአጭሩ አሁን እኛ ኢትዮጵያዊያን የምንፈልገው የሚመስለኝ ይህን የሽግግር ጊዜ ተጠቅመን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መግባት እንጂ ወደ አዲስ የሸግግር መንግስት ምስረታ ቁማር መሆን የለበትም፡፡ የሽግግር መንግስት የምትጠይቁ ቡድኖች አሳማኝ የሆነ ነጥብ ንገሩን፡፡ ዶክተር አብይ አህመድ የማይሰጡን የሸግግር መንግሰት የሚሰጠን ጥቅም ካለ አስረዱን፡፡ በቀጣይ ሁለት ዓመት በመንግሰት ሥልጣን ውስጥ ለመካተት ከሆነ ይህ የግል ፍላጎት ብቻ ነው የሚመስለኝ እና ለዚህ ሃሣብ ድጋፍ አልሰጥም፡፡ የሸግግር ጊዜን ተጠቅመን ወደ ዴሞክራሲ የሚደረገውን ጉዞ እናፋጥን፡፡

አመሰግናለሁ

Filed in: Amharic