>

በሰላማዊ ሰልፉ የጨቋኞች ውድቀት ተረጋግጧል! የነፃነት ጮራ ፈንጥቋል! (ስዩም ተሾመ)

በሰላማዊ ሰልፉ የጨቋኞች ውድቀት ተረጋግጧል! የነፃነት ጮራ ፈንጥቋል!

ስዩም ተሾመ

ባለፉት አስር ቀናት የታዩት ለውጦች ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ከታዩት ለውጦች ይበልጥ የደመቁ፣ ለቀጣይ ብዙ አመታት የሚታወሱ፣ በማሳያነት የሚጠቀሱ ናቸው። በመሰረቱ ፍርሃት ፀረ-ዴሞክራሲ የሆነ የጨቋኞች መርህና መመሪያ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ደግሞ ሕዝቡ አደባባይ በመውጣት ይህን የፍርሃት ቆፈን ሰብሮታል። ከድሬዳዋ እስከ ጎንደር፣ ከሆሰዓና እስከ ደብረ ማርቆስ፣ ከአዲስ አበባ እስከ ባህር ዳር፣… ወዘተ በነቂስ ወጥቶ ዴሞክራሲያዊ መብቱን በተግባር አረጋግጧል። ለለውጥና ዴሞክራሲ ያለውን ድጋፍ በግልፅ አሳይቷል። ነገር ግን፣ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች “ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ!” በሚል መሪ ቃል ሰላማዊ ሰልፍ የሚካሄድበት ምክንያት ምንድነው? ለዚህ ጥያቄ የሰልፉ መሪ ቃል በራሱ ምላሽ ይሰጣል።

“ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ!”
በእርግጥ በመስቀል አደባባይ ስለሚካሄደው ሰልፍ እየተወያየን ሳለ የአስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጉደታ ገለልቻ “ሰልፉ የራሱ የሆነ መሪ ቃል ያስፈልገዋል” የሚል ሃሳብ አነሱ። ይህን ተከትሎ “የሰልፉ መሪ ቃል ምን ይሁን?” የሚል ጥያቄ ለኮሚቴው አባላት ቀረበ። እኔም ለጥያቄው “ሰልፉ የሚካሄደው ጠ/ሚ አብይን ወይም ኢህአዴግን ብቻ ለመደገፍ ሳይሆን ‘የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ለመደገፍ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማበረታታት ነው። ስለዚህ የሰልፉ መሪ ቃል “ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ!” የሚል መሆን አለበት” የሚል ምላሽ ሰጠሁ። በዚህ መልኩ እንደዋዛ ያቀረብኩት ሃሳብ ተቀባይነት አግኝቶ የሰላማዊ ሰልፉ መሪ ቃል ሆነ። ነገር ግን፣ የመሪ ቃሉ ትርጉምና ፋይዳ ምንድነው?

በመሰረቱ “ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ!” የሚለው በሁለት ፅንሰ-ሃሳቦች ላይ የተመሰረተ ነው። የመጀመሪያው ከቅርብ ግዜ ወዲህ በሀገራችን ጅምር የለውጥ እንቅስቃሴ መኖሩንና ይህንን ለውጥ መደገፍ አግባብ እንደሆነ የሚጠቁም ነው። ምክንያቱም የተጀመረው ለውጥ የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን በማስወገድ በእኩልነት መርህ ላይ የተመሰረተ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል ነው። ስለዚህ የተጀመረውን ለውጥ መደገፍ አምባገነናዊ ስርዓትን ለማስወገድ እና/ወይም ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ማበረታታት ነው። በመሆኑም “ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ!” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ዓላማና ፋይዳ ለውጥን በመደገፍ ጭቋኝ ስርዓትን ማውገዝ፥ ማስወገድ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ማበርታት፥ ማጠንከር ነው።

የጭቆና ማብቃት እና የጨቋኞች ውድቀት
ባለፉት አስር ቀናት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ አደባባይ በመውጣት በጠ/ሚ አብይ መሪነት ለሚወሰዱ የለውጥ እርምጃዎች ያለውን ድጋፍ በይፋ ገልጿል። ይህ የብዙሃኑ አመለካከት (Public Opinion) ከማን ጋር እንደሆነ በግልፅ ለመረዳት አስችሏል። ከዚህ በተጨማሪ፣ ለጠ/ሚ አብይ አህመድ የለውጥ እርምጃ ድጋፉን በገለፀበት ልክ ይህንን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ወገኖችን በግልፅ አውግዟል። በአጠቃላይ ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ ከፍተኛ ድጋፍ እንዳለው ሲገልፅ፣ ፀረ-ለውጥ አቋም ያላቸውን የፖለቲካ ቡድኖችን አምርሮ እንደሚቃወም በተግባር አሳይቷል።

በዚህ መሰረት፣ የጠ/ሚ አብይ ቡድን የጀመረውን የለውጥ ሂደት አጠናክሮ በመቀጠል ሀገሪቱና ሕዝቡን ወደ ዴሞክራሲና ብልፅግና በሚወስደው ጎዳና መምራትና ማስተዳደር እንደሚችል ተረጋግጧል። በአንፃሩ፣ የተጀመረውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ በተለይ ደግሞ ፀረ-ለውጥ አቋም የሚያራምዱ የህወሓት አመራሮችና የእነሱ ተላላኪዎች በብዙሃኑ የህብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው ተረጋግጧል። በመሆኑም እነዚህ ፀረ-ለውጥ ቡድኖችና አመራሮች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸው የፖለቲካ ስልጣንና ቅቡልነት ሙሉ በሙሉ አክትሟል።

ከዚህ በኋላ ፀረ-ለውጥ አቋም ያላቸው ወገኖች በሀገሪቱና ሕዝቡ የወደፊት እጣ-ፈንታ ላይ የመወሰን ስልጣን የላቸውም። በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ውስጥ ሆነ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚከተሉት አቋምና የሚያሳልፉት ውሳኔ ተቀባይነት የለውም። አንድ የተለየ ተዓምር ካልተፈጠረ በስተቀር እንደ ፖለቲካ ቡድን ወይም አመራር የነበራቸው ህልውና አክትሟል። ምክንያቱም በብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ዘንድ ተቀባይነትና ድጋፍ የሌላቸው የፖለቲካ ቡድኖችና አመራሮች ሀገርን መምራት አይችሉም። እንዲህ ያሉ ቡድኖችና አመራሮች ደግሞ ሕዝብን ማስተዳደር አይችሉም፡-

“Rule is the normal exercise of authority, and is always based on public opinion. Never has anyone ruled on this earth by basing his rule essentially on any other thing than public opinion. [It] is the basic force which produces the phenomenon of rule in human societies is as old, and as lasting, as mankind. In Newton’s physics gravitation is the force which produces movement. And the law of public opinion is the universal law of gravitation in political history.” The Revolt of the Masses, – Jose Ortega y Gassett, Page 74.

ከላይ በተጠቀሰው መሰረት፣ ብዙሃኑ የሕብረተሰብ ክፍል ለውጥን የሚደግፍ ከሆነ ፀረ-ለውጥ አቋም የሚያራምዱ የፖለቲካ ቡድኖችና አመራሮችን አምርሮ ይቃወማል፥ ይታገላል። አንድ የፖለቲካ ቡድን ወይም አመራር ፀረ-ለውጥ አቋም የሚያራምደው የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚንቀሳቀስ ከሆነ ነው። በተቃራኒው የብዙሃኑ ጥያቄ እኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ነው። አዲስ አበባና ባህር ዳርን ጨምሮ በተለያዩ የሀገሪቱ አከባቢዎች እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ ሰልፍ፤ በአንድ በኩል እኩልነትና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ፣ በሌላ በኩል የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነትን ለማስቀጠል የሚደረገውን ጥረት በመቃወም ነው።

ሰሞኑን በተካሄዱት ሰለማዊ ሰልፎች የተጀመረው ለውጥ ሕዝባዊ ድጋፍና ተቀባይነት እንዳለው ተረጋግጧል። በአንፃሩ የለውጡን እንቅስቃሴ በማደናቀፍ ላለፉት 27 ዓመታት የተዘረጋውን የአንድ ወገን የበላይነትና ተጠቃሚነት ለማስቀጠል የሚደረገው ጥረት በብዙሃኑ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌለው አረጋግጧል። ሰለዚህ “ለውጥን እንደግፍ፣ ዴሞክራሲን እናበርታ!” በሚል መሪ ቃል የተካሄደው ሰልፍ ሕዝቡ ለጭቆና እና ጨቋኞችን ቦታና ድጋፍ እንደሌለው በግልፅ አሳይቷል። ከዚህ በኋላ ሕዝቡ ጭቆናን ይጠየፋል፣ ጨቋኞችን መፍራት ያቆማል። በአጠቃላይ በሰላማዊ ሰልፉ የጭቆና ማብቃትና የጨቋኞች ውድቀት ተረጋግጧል፣ የእኩልነትና ነፃነት ጮራ ፈንጥቋል።

Seyoum Teshome

Filed in: Amharic